Thursday, March 9, 2017

የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራን አርበኞች ግንቦት ሰባትን ኢሳትንና ኦ ኤም ኤንን የተመለከተ አዲስ ዕቅድ እያዘጋጀ ነው

     



ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት “የደህንነት አደጋ ደቅነውብኛል በሀገሪቱ ስላምና መረጋጋትን አናግተዋል” ያላቸውን ሀይሎች ለመፋለም እየተዘጋጀ መሆኑን በገዥው ፓርቲ ዙሪያ ላሉ ቁልፍ ሹማምንትና ለደህንነት አካላት ሹክ ብሏል።
ኢህአዴግ በተለይ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች ተከስቶ የነበረው ህዝባዊ አመፅ እንዳይደገም ይረዱኛል ያላቸውን እርምጃዎች በሁለት ዘርፍ ከፍሎ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰናዳ መሆኑንም ለዋዜማ የደረሰ መረጃ ያመለክታል። ከእርምጃዎቹ አንዱ በኤርትራ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ መለወጥና በአስመራ ላይ ስልታዊ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም በውጪ ሀገር ያሉ ተቃዋሚዎችና ሚዲያዎችን በህግ ፊት ማቅረብና ማዘጋትን ያካትታል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ እንዲሁም ኢሳትና ኦ ኤም ኤን የአዲሱ የመንግስት ጥቃት ኢላማ መሆናቸውን የመንግስት የቅርብ ምንጮች አረጋግጠዋል። በኤርትራ ላይ የተዘጋጀው አዲስ ዕቅድ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ሲሆን በሌሎቹ ጉዳዮች ላይ አለማቀፍ አማካሪ ለመቅጠርና የምዕራባዉያንን ትብብር ለመጠየቅ ዕቅድ ተይዟል። [ይህን ጉዳይ በተመለከተ  ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ከታች በድምፅ ያገኛሉ]
ዋዜማ  ከተለያዩ ምንጮች እንዳረጋገጠችው በኤርትራ ላይ የተያዘው ዕቅድ በተወሰኑ የፓርቲ ሹማምንት ሰፊ ክርክር የተደረገበት ሲሆን በዕቅዱ ዙሪያ የሀሳብ ልዩነት አለን ያሉ ባለስልጣናት ዕቅዱ በድጋሚ ይከለስ የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በተደረገውና በቅርቡም በቅንጭብ ለካቢኔ አባላት እንደተነገራቸው፣ ዕቅዱ ተግባራዊ ሲሆን ከኤርትራ ጋር ወደ ለየለት ጦርነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
የአረብ ሀገራት የድርድር ጥያቄ በተደጋጋሚ አቅርበው የአስመራ መንግስት እንዳልተቀበለው የሚገልፁ አንድ ሹም ኤርትራን አስገድዶ ወደ ድርድር ማምጣት የዕቅዱ አንድ አካል ነው ይላሉ።
ይህ ካልሆነ በኤርትራ የሰርዓት ለውጥ እንዲመጣ በተለየ መልኩ ለመስራት መታሰቡንም ሹሙ ነግረውናል።
የአሜሪካ የኮንግረስ አባላትና ወታደራዊ አታሼዎች በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በሶማሊያ ጉዳይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚገኙና “አሸባሪ” ያለቻቸው ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት እንዲሁም በኢሳትና በኦ ኤም ኤን የሚዲያ ተቋማት ላይ ክስ መስርቶ እንዲዘጉ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ለማግባባት እንደተሞከረ ተሰምቷል።
“ይህን ጉዳይ በይፋ ስብሰባ ላይ አልተነሳም ይሁንና ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ለልዑካን አባላቱ እንደተነገራቸው አውቃለሁ” በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አንድ የአሜሪካ መንግስት ምንጭ እንደተናገሩት።
“ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሚኖራትን ትብብር ተቃዋሚዎችን ከመቅጣት ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል፣ ይህ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፣ አልተቀበልነውም። የፕሬዝዳንት ትራምፕ አዲሱ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም እስካሁን አልተናገረም፣ አዲስ ነገር ይኖራል ብዬ አልጠብቅም” ይላሉ ምንጩ።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ወታደሮቿን ወደ ድንበር በመሳብ በሶማሊያ ያላትን ተሳትፎ የቀነሰች ሲሆን አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ደግሞ በሶማሊያ በአልሸባብ ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት የኢትዮጵያን ተሳትፎ ይፈልጋል። ለኢትዮጵያና ለሌሎቹ በዘመቻው ለሚሳተፉ ሀገሮች ዳጎስ ያለ በጀት ከአሜሪካ በኩል መያዙም ተሰምቷል።

No comments:

Post a Comment