Friday, March 31, 2017

ትንቢታዊ መልእክት ከቆሼ – ያየያየ ይልማ



ከአውሮፓ ከተሞች ሁሉ ዝቅ ያለ ነው ደረጃዋ የተባለችውን፡  የአንዷን አውሮፓዊ ከተማ የቆሻሻ  አሰባሰብ ስርአቷን ፣ ቆሻሻ ስለሆነ ብቻ እንደው ባንድ ስም ቆሻሻ ተብሎ ወስዶ መጣል ሳይሆን፤ በሚገርም የቆሻሻ አይነትና ዝርዝር ብዛት እንዲወገድ ህብረተሰቡን ስለ እያንዳንዱ ቆሻሻ አወጋገድ የሚያስተባብሩበት መንገድንና ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የቆሻሻ አወጋገድ ዘይቤያቸውንና አስተዳደራቸውን ፣ በእንግድነት ሰሞኑን ሄጄ እንደታዘብኩ፡ እጄን ባፌ ላይ ጭኜ የእውነት አገሬን አሰብኳት፤ በተለይ አዲስ አበባን፡፡
ከዚያም እንዴ እረ ለመሆኑ ኢትዮጵያን እንመራለን ብለው የሚደናገሩት ሰዎች በሙሉ ለቁጥር ለሚያታክት ጊዜ ያክል በምእራባዊያኑ አገራት ሲዘዋወሩ፡ የልምድ ልውውጥ ትብብር ሲፈራረሙ መኖራቸውን ብሰማም ፣ እንደው ለምን ይሆን ለህዝባቸው እንደው እንደዚህ አይነት በጎ ተሞክሮዎችን የማይኮርጁት እያልኩ እና በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ክልል መሪዎች መካከል በተነሳው ውዝግብ ምክንያት አዲስ አበባ ለሳምንታት እንዴት ገምታ እንደነበር አስታውሼ አዝኜ ሳላበቃ፣ ሳምንት እንኳ ሳይቆይ፣ የቆሼን እልቂትን መርዶ ሰማሁ እና አረፍኩት፡፡ በዚህ ክፉ መርዶ ዜና ምክንያት ነበር ታዲያ ሁለት ነገሮችን፡ ከዚህ እልቂት ጋር ስለተያያዙ ነገሮች በግሌ ማስተዋል የቻልኩት፡፡
አንደኛ
…የወያኔ አንደበት የሆኑት የተለያዩ ሰዎች ፣ በተለይ ወያኔን በተለያዩ ሚዲያዎች የክፋቱ ተወካዮች ሆነው የሚቀርቡት ሰዎች ስሜታዊ ሁለንተና፤ የአንድ እናት ልጅ የሆኑ እስኪመስል ድረስ፡ በሚያደናግር መንገድ አንድ መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡
ለዚህ ማሳያ እንዲሆን፣ ከአመታት በፊት ስሙን የማላስታውሰው  ፣ አንድ እጅግ አስገራሚ ስብእና ያለው የሸገር ኤፍኤም ራድዮ ጣቢያ ዜና አንባቢ-
(ልቅሶና ሲቃ በሚተናነቀው ድምፅ)
“…እድለ ቢስ ሆኜ ይህንን ክፉ መርዶ አንባቢ እንድሆን ተፈረደብኝ እንጂ ፣ ለእንጀራ ቢቻ ቢሆን ይህንን ዜና ፈቅጄ ከማንበብስ እንጀራው ጥንቅር ብሎ ቀርቶ ሞቴን እመርጥ ነበር፤”… በማለት ነበር ይህ ስሙን ባላስታውሰውም ልረሳው የማልችለው ጋዜጠኛ፡ የታላቁን ፣ የኢትየጵያ የሙዚቃ ንጉስ ፡ የጥላሁን ገሰሰን ሞት ለአዲስ አበባና ዙሪያዋ ነዋሪ ህዝብ ፣ ድንገተኛ የሞቱን መርዶ  የተናገረው፡፡
እንዲሁ ታዲያ ከአመታት በኋላ ፤ ሌላ ክፉ ዱብዳ ፣ ቅዳሜ መጋቢት 02 – 2009 የብዙዎችን እስትንፋስ እስከወዲያኛው፡ አመድ አለበሳቸው ፡፡ በዚህ ጊዜ፤ “ቆሼ ተደርምሶ ነዋሪዎችን ገደለ”፡ የሚል ዜና በኢቲቪ ተነበበ፡፡ የውድቀታቸው ዜና እንዲሁ ይጠርላቸው ብያለሁ፣ የሚስማማ ካለ አሜን ብሎ ይቀበል፡፡
ግን ዜናውን ያረቀቀው ሰው፣ እንደ ሸገሩ አንባቢ ቆሽት ቢኖረው ኖሮ፣  በቆሼዎቹ ምንዱባን ሞት ያለጥርጥር እርር ቅጥል ስለሚል ጥርሱን ነክሶ፡ እንዲህ ይል ይመስለኛል፤
በጉድፍ መጣያው ቆሼ፡ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት ተነባብሮ ተከምሮ የኖረ የቆሻሻ እና ክርፋት ተራራ፡ እንደ ጉድፍ ተቆጥረው ተገፍተው፡ ከቆሻሻው እየበሉ ከጎኑ በድህነት ይኖሩ ከነበሩ ጭርቁስ ጎረቤቶቹ ፣ ይልቅ እርሱ ቆሻሻው ጉልበት ኖሮት፣ ጉልበቱ ከድሃ ኢትዮጵያዊ ፈፅሞ ልቆ ፡ ከጀግና እኩል ከመቶ ሃያ በላይ የሰው ነብስ ግዳይ ውጦ ልካችንን አሳየን፡፡ ብሎ ተናግሮ ለሟቾች ዘመዶች ውለታ ይውልላቸው ነበር!! ግን አልሆነም፡፡ የኢቲቪ ጋዜጠኞች አይናቸው ኩል የተኳለ እስኪመስል ድረስ ፡ ወር ሙሉ ዜና ባነበቡ ቁጥር የሚያለቅሱት፡ ኢትየጵያ አይታ የማታውቀው ነብሰ በላ – መለስ፡ በፈጣሪ ፍርድ እንደ ማንኪያ ተቀንጥሶ መሄዱን መቀበል ያቃታቸው ጊዜ ነበር፡፡
ሁለተኛ
በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ለአገር የሚበጅ ነገር  እንደሚመጣ ወያኔ ቢያውቅም ፣ እንዲህ አይነት መንገድን መከተል ቀድሞ የሚያጠፋው ወያኔን ስለሆነ፡ በእወቀት ላይ የሚመሰረት የአመራር ተሞክሮ ወያኔ ባቋቋማቸው የደደብነት ኢኒስቲዩቶች ውስጥ ገብተው እስካልተበረዙ ድረስ ጥቅም ላይ አይውሉም፡፡ 
ከታታላቆቹ አፍሪካዊ መሪዎች አናት ላይ የሚቀመጡት  አፄ ምንሊክ እና አፄ ኃይለስላሴ እጅግ በሚገርም ፈር ቀዳጅነታቸው እስከ ዛሬም ድረስ የምንጠቀምባቸውን ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎቶችን የሚከፈለውን ሁሉ መስዋእትነት ከፍለው ለህዝባቸው ጥቅም ላይ አዋሉ፡፡ በዚህ ረገድ፣ ከባቡር ትራንስፓርት፣ ፖስታ፣ ቴሌኮሞዩኒኬሽን እስከ ዘመናዊ ትምህርትና ተሸከርካሪዎች እስከ የአየር እና የባህር ትራንስፖርት ድረስ የሚዘረጋ ፤ ከዘርፈ ብዙ የከተማ ልማት የስነ ህንፃን የማስፋፋት ትጋት እስከ ፈር ቀዳጅ ፖለቲካዊ አመራር ድረስ ጭምር በተሰሩ ስራዎች፣ አሁን ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሚጠቀሙባቸው እና የሚኮሩባቸው ስራዎች፣ ከቀደምት መሪዎቻችን የወረስናቸው ህያው ውርሶቻችን ሆነው ዛሬ ድረስ አሉ፡፡
ወያኔ ለኢትዮጵያዊያን የሚበጅ ነገር ከተለያዩ የአለም ተሞክሮዎች ሳይመለከት ቀርቶ ሳይሆን፣ ከላይ እንደጠቀስኩት አይነት ባይፈጠሩም ሊቀዱ የሚገባቸው ተሞክሮዎችን ፤ በሚያስገርም ቁርጠኝነት እንደዚህ አይነት ከሌላ አለም ሊገኙ የሚችሉ እና  በእውቀት ላይ የሚመሰረት አመራር እና አስተዳደራዊ መዋቅርን የሚጠይቁ በጎ ተሞክሮዎችን ማጥፋት ዋነኛ ተልእኮው ስለሆነ ነው እንጂ፤
ወያኔ አድርጎት ከኮረጀም የሚኮርጀው እንደፈለገ ቀዶ መስፋት የሚችላቸውን፣ ተሞክሮዎችን ብቻ ይሆናል፡፡ እነዚህም ታዲያ ከራሱ እጅግ ክፉ የአገዛዝ ስርአት ጋር ሊሄዱ የሚችሉ አይነት፤ ለምሳሌ በዘርኝነት ላይ የተመረኮዘው የፌደራል አገዛዝ እና በፀረ-ሽብር ስም መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት በሰሚ ሰሚ የሚያመክንበት አይነት ፖሊሲና ህጎቹ ብቻ ናቸው፡፡
ታዲያ እዚህ ጋር ወያኔ ያላወቀው ነገር ምን መሰላችሁ፣ ቆሼ የሚታየው ቆሻሻ፣ የሚታየው ሻጋታ ተከምሮ ያገዘፈው ተራራ ነበር፡ ስለዚህ መፍረሱ አይቀሬ ነበር! ምክንያቱም ውስጡ በስብሷል፡ እንኳን አምነው ተጠግተው ከክርፋት የሚገኝ ዳቦ ለሚቃርሙ መኖሪያነት ምቹ ሊሆን ይቅርና ለራሱም ቀን የሚጠብቅ፡ የተጣሉ የሸተቱ፡ የሻገቱ ብስባሾች የቆለሉት ክምር ነበርና ተደረመሰ! ይህ ግን ለወያኔ መፃኢ እጣ-ፈንታው ፡ ስሪቱን እና አወዳደቁን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ አይቀሬ ሃቁ ነው፡፡ የቆሼው እልቂት፡ የላይ የውጪ ሻጋታና ክምር ድርምስ ነው ፤ የወያኔ አደረማመስ ግን ፡ አፅሙን የሚያንኮታኩት ታላቅ ነውጥ ነው!!!
… የሚናፍቀኝ የወያኔን ድንገተኛ የህልፈት መርዶ ፡ የዛ የታላቅ የሸገር ኤፍኤም ዜና አቅራቢ መንፈስ እና ኢትዮጵያዊ ቆሽት ባላቸው ሰዎች ሲነበብ ዜናው የሚደራጅባቸው ቃላቶች እና ድምፃቸው ነው፡፡ የዛ ሰው አርጎ ያገናኘን!!!

No comments:

Post a Comment