Monday, March 13, 2017

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የድንበር ግጭት ከ35 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል

   


Addis Admass :
የድንበር ግጭቱን ቀስቅሰዋል የተባሉ ባለሥልጣናት በህግ ይጠየቃሉ ተብሏል
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መካከል ባለው የድንበር ግጭት ከ35 ሺህ በላይ ዜጎች በመፈናቀላቸው አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል የተባለ ሲሆን በአካባቢው ካሉ የድርቅ ተጎጂዎች ጋር ተደማምሮ የእርዳታ አቅርቦቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡
በምስራቅ ሀረርጌ ከ14 ሺህ በላይ፣ በባሌ ከ15 ሺህ በላይ እንዲሁም በጉጂ 1500 አባወራዎችን ጨምሮ ግጭቶቹ ባሉባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉና በቂ ያልሆነ አስቸኳይ እርዳታ እየተደረገላቸው የሚገኙት ከ35 ሺህ ይበልጣሉ ብለዋል-የኦሮሚያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግርማ ወተሬ፡፡
Image result for oromia somali border
በአካባቢው ባለው ድርቅ አስቀድመው ለተጎዱ ወገኖች በመደበኛነት በሚሰጠው እርዳታ ላይ የግጭቱ ተፈናቃዮች መደመር የሰብአዊ ድጋፉን አስቸጋሪና የተሟላ እንዳይሆን አድርጎታል ያሉት አቶ ግርማ፤ በቀይ መስቀልና በሌሎች ለጋሾች የሚደረገው አስቸኳይ እርዳታ በቂ ስላልሆነ ሁሉም ወገን ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በድርቁ ምክንያት በአካባቢው ከፍተኛ የውሃ እጥረት መኖሩን የጠቆሙት ሃላፊው፤ በተለይ ለተፈናቃዮቹ ውሃ፣ መጠለያና የሌሊት ልብሶች በአስቸኳይ እየተዳረሱ ሲሆን በምግብ በኩል እስካሁን በቅድሚያ ለእናቶችና ህፃናት አልሚ ምግብ እየቀረበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለግጭት ተፈናቃዮች የሚደረገው አስቸኳይ እርዳታ ለድርቅ ተረጂዎች በሚሰጠው መደበኛ እርዳታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ በአካባቢዎቹ ህፃናትና ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት ገበታ መናጠባቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በሁለቱ ክልሎች መካከል የድንበር ግጭቱን አስነስተዋል የተባሉ ከፍተኛ አመራሮች ተለይተው መታወቃቸውንና ቀሪዎች ላይም የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የገለፁ ቢሆንም ታውቀዋል የተባሉትን ባለስልጣናት በስም ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡
ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው የሁለቱ ክልሎች የድንበር ግጭት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ከአካባቢው ምንጮች ያገኘነው መረጃ የሚጠቁም ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ም/ቤት (ጨፌ) ከሰሞኑ ባደረገው ስብሰባ ለግጭቱ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠውና በአስቸኳይ እንዲቆምም  እርምጃ ይወስድ ዘንድ አሳስቧል፡፡
የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ሃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል የተባለ ሲሆን ከሁለቱም ክልሎች ችግሩን ያባባሱ ባለስልጣናትም በህግ እንደሚጠየቁ ጨፌው ወስኗል፡፡

No comments:

Post a Comment