Tuesday, March 21, 2017

እምዬ ምኒልክ ወላዋይ ነበሩ ወይ? – ወለላዬ ከስዊድን



የአድዋን በዓል አከብራለሁ ብዬ ሄጄ፤ አፄ ምኒልክ ሲሰደቡ ሰምቼ ተመለስኩ
ወለላዬ ከስዊድን
ምሁር ባልባልም በቃ! አልጸጸትም፣
ፊደል ቢሸከሙት አያደርስም የትም።
አሮጌ ልብስ ነው አስቀያሚ ኮተት፣
ማስተዋል ካነሰው ቢከመርም ዕውቀት።
(የረቡዕ ግጥም ፫ኛ ዓመት፣ ወለላዬ)

የስዊድን ሶሻል ዴሞክራት ተቀጥላ የሆነው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ማኅበር የአድዋን ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ዝግጅት አድርጎ ነበር፤ እሁድ ማርች 5 ቀን 2017። በዝግጅቱ ላይ እንድገኝ ጥሪ ደርሶኝ ከተካፈሉት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። ዝግጅቱ በቪድዮ ክሊፕ እንድናዳምጣቸው የተመረጡልን ሰዎች ሲኖሩት፣ በአካል የተገኙ እንግዳም ነበሩ። ክሊፑን በስክሪን እያየን ካዳመጥናቸው አንዱ “The Battle of Adwa” የተባለውን መጽሐፍ የጻፉት ፕሮፌሰር ዮናስ ሬይሞንድ ሲሆኑ፣ ስለ መጽሐፋቸው ከኢጣሊያ የታሪክ ተመራማሪ ከጆን ዌልሽ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ይገኝበታል። ሁለተኛው ደግሞ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሚስተር ታቦ ምቤኪ፣ በስድስተኛው የዓለም አቀፍ አፍሪካ ኮንግሬስ ላይ ስለ አድዋ ያሰሙት ንግግር ነበር።

የፕሮፌሰር ዮናስ ቃለምልልስም ሆነ የፕሬዝዳንት ምቤኪ ንግግር የአድዋ ድል በዓልን በሚያረካ ሁኔታ ያንጸባረቀና የታሪክ ምስክርነትም የሰጠ ነበር። ዮናስ ሬድሞንድ ምን ያህል መጽሐፉን ለመጻፍ በምርምር እንደደከሙ ለማወቅ ስንችል፤ በሰጡትም ትንታኔ እጅግ የሚያረካ ሆኖ አግኝተነዋል። ምቤኪም የአድዋ ድል አፍሪካዊ ክብር ሆኗቸው፣ ድሉን በተመለከተ ንግግር ማድረግ መቻላቸው ሌላው ልባችንን በኢትዮጵያዊነት ኩራት የሞላን አጋጣሚ ሲሆን፣ ንግግራቸውም እውነተኛ የጀግኖች አባቶቻችንን ተጋድሎ የሚያስታውስ ነበር።

ጉድ የፈላው በአካል የተገኙት ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ መናገሪያውን ከጨበጡ በኋላ ነበር። ፕሮፌሰሩ በስክሪን የቀረቡትን የሁለቱን ሰዎች ንግግር ማዳመጣቸውን ገልጸው፤ “እኔ ከነሱ በኋላ እንድናገር መቅረቤ ግራ አጋብቶኛል” በማለት ነበር ወደ ዋናው ንግግራቸው የገቡት። ስለሁኔታውም ሲያብራሩ፤ “እኔ ያለኝ ወይም የማውቀው የአድዋ በዓል ታሪክ ከነሱ የተለየ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ምቤኪ ከኔ ጓደኛ ከማሞ ሙጨ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያጠናውን ይዞ ነው የቀረበው” ብለዋል። “ምቤኪ ከማሞ ሙጨ የተማረውን በትክክክል ይዞ ማስተላለፍ ችሏል፤ ከኔ ቢማር ደግሞ የበለጠ እውነተኛ ታሪክ ማወቅ በቻለ ነበር” በማለት ሁለቱንም ተናጋሪዎች እና ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨን አጣጥለዋል።

እሳቸው ወደሚያውቁት የአድዋ ድል ታሪክ ሲገቡም፣ አንኳር አድርገው ያቀረቧቸው ነጥቦች አጠር ባለ መልክ የሚከተሉት ናቸው፤

  • የአፄ ምኒልክን የአመራር ደካማነት፣ የተላበሱትም ዝና ከሠሩት በላይ የተጋነነ ስለመሆኑ፤
  • ራስ መኮንንም ከአፄ ምኒልክ የተሻሉ እንዳልነበሩ፤
  • እቴጌ ጣይቱ አርቆ አስተዋይ እንደነበሩ፣ ነገሮችን የመፍታት ብቃታቸው ጠንካራ እንደነበር፤
  • በጦርነቱም ጊዜ የሳቸው (የቴጌ ጣይቱ) ብልህ አመራር ባይኖር የጦርነቱ ሁኔታ አሁን የያዘውን መልክ ይለወጥ እንደነበር፣ ይህንንም ሊረዱ የቻሉት ከኢትዮጵያ ወደጣሊያን በዚሁ ጉዳይ የተላለፉ መልክቶች በመኖራቸውና ያም አስተማማኝ መረጃ ስለመሆኑ፤
  • የአድዋ ድል በዕድል ወይም በአጋጣሚ የተገኘ ድል ስለሆነ፤ ይሄን ያህል መጋነን እንደማይገባው፤
  • የተገኘው የድል ትርፍም እጅግ ጎልቶና ተጋኖ የተነገረለት እንደሆነ፤
  • በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ጸሐፊዎች ይልቅ እውነተኛውና ትክክለኛው ታሪክ ሰፍሮ የሚገኘው በጣሊያን ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሆነ፤ የነሱን ጽሁፍ ያላካተተ ታሪክ ዕውነተኛነቱ የሚያጠራጥር እንደሆነ፣ በአበሻው የሚነገረው ታሪክ በቃል ካንዱ ወዳንዱ የተላለፉ መረጃ የጎደላቸው ናቸው የሚሉ ነበሩ።

ይኽንን በስፋት ሲያስረዱ አስተማሪዬም ወዳጄም የነበረው ሮቢንሰን የተባለ የታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ በአድዋ ጉዳይ መጽሐፍ የፃፈ ቢሆንም፤ የመጽሐፉ ገጽ አብዛኛው የያዘው ስለ ምኒልክ ብቻ ሲሆን፤ ስለ እቴጌ ጣይቱ የጻፈው ምንም ነገር የለም። ፀሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴም እዛው ሆነው ያዩትንና የሰሙትን ብቻ የጻፉ ስለሆነ፤ የሁለቱም ጽሁፍ ሁሉን ጉዳይ ያላሟላ ውስን ታሪክ የያዘ ነው ብለዋል።

አፄ ምኒልክን ሲወቅሱ ደግሞ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣልያን ኢትዮጵያ ላይ አንድ ሁኔታ ከደረሰ የሚይዙትን የኢትዮጵያ ግዛት በመከፋፈል ሲስማሙ አፄ ምኒልክ ይሄን እያወቁ ዝም ብለው አልፈዋል። አፄ ዮሐንስ ጣሊያንን አናስገባም ሲሉ፤ ምኒልክ ግን ከጣሊያን መሳሪያ ለመቀበል አፄ ዮሐንስን ላለመርዳት ውል ተዋውለው መሳሪያ ወስደዋል። ይህ ሁኔታ ሲታይ ከሁሉ ነገር ይልቅ ለሥልጣናቸው ይጓጉ እንደ ነበር ማስረጃ ነው ብለዋል።

“አፄ ዮሐንስ ሲሞቱም ጣሊያኖች ኤርትራ እንዲገቡ ፈቅደው ለጣሊያን አስመራን የሰጡ ናቸው። ስለዚህ በትግሬ ዓይን ሲታይ ጣሊያንን ያስገቡ እሳቸው ሲሆኑ፤ የውጫሌን ውልም በተመለከተም የአንቀጽ 17ን ጉዳይን ሲወላውሉ የቆዩና ምንም ማድረግ ያልቻሉ መሪ” በማለት የምኒልክን ደካማ መሆን አጉልተው ለማሳየት ሞክረዋል።

አፄ ምኒልክ ደካማና ወላዋይ ነበሩ የሚለው አባባላቸውን በዚህ ብቻ አላቆሙም። ጣሊያን ምሽግ ለመሥራት በማሰብ ጊዜ ለመግዛት ስምምነት ለማድረግ ሲጠይቅ ስምምነት አድርገው ምሽግ እንዲሠራ ጊዜ ሰጥተዋል። በኋላም ማስለቀቅ ሲያቅታቸው ራስ መኮንን ይሄንን ያደረከው አንተ ነህና ተወጣው በማለት ብዙ ሰው እንዲገደል ምክንያት ሆነዋል። ጦርነቱም ይጀመር ብለው አዋጅ አውጥተው ከዘመቱ በኋላ ያስከተሉት አንድ መቶ ሺህ ጦር ትግራይ ውስጥ ብዙ በመቆየቱ ጦሩ እንዲመለስ ፈልገው ነበር ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ጣልያን ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲንቀሳቀስ በሦስት ቦታ ሠራዊቱን ከፍሎ በኋላ ለመገናኘት እቅድ ያወጣ ሲሆን፣ ያ እቅድ ሳይሳካለት በመቅረቱ ኢትዮጵያ ልታሸንፍ የቻለችው በዚህ ዕድል በመጠቀም ነው። ይህ ዕድል ባይገኝ ኖሮ የጦርነቱ መልክ ሌላ ይሆን ነበር፤ እንደውም ማኽል የነበረው ጦር ገፍቶ በመሄድ ጥቃት ሰንዝሮ ስለነበር፣ የኢትዮጵያ ጦር ማፈግፈግ ጀምሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ምኒልክ የት እንደገቡ አይታወቅም፤ ጣይቱ ጦሩን አበረታተው እንደገና የመጣውን ጦር እንደመለሱት ማሸነፍም እንደቻሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ንግግራቸውን ያጠቃለሉት፣ “ጦርነቱን ኢትዮጵያ ያሸነፈችው በዕድል ነው። የተገኘውም ዕድል አንዱ የጣይቱ በዛን ዘመን ላይ መገኘት፤ ሁለተኛው ደግሞ የጣሊያን ሠራዊት ባወጣው እቅድ መሰረት አለመገናኘቱ ነው” በማለት ነበር።

ይህ ከብዙ በጥቂቱ ከትንተናቸው የተቀነጨበ ሲሆን፣ ንግግራቸው የአድዋን በዓል የድል ብስራት እንዲያንጸባርቅ የተጋበዘ የአበሻ ደም ያለው ሰው ንግግር ሳይሆን፤ በመሸነፉ የተበሳጨ የጣሊያን ሠራዊት አዛዥ ቁጭትና ንዴቱን የገለጸበት አይነት መስሎ የሚታይበት ነበር። ይህም በመሆኑ ንግግራቸው ተቀባይነት ከማጣቱም በላይ ቁጣን ቀስቃሽም ሆኗል። ዕድሉን ያገኙ ተናጋሪዎችም በንግግራቸው የታሪክ መዛባት እንዳለበት፣ ድሉም የተገኘው በዕድል ሳይሆን እቅድ ባለው አመራር እንደሆነ አስረድተዋል። በዚሁ ዙሪያም ለፕሮፌሰሩ ጥያቄዎች ቢቀርብላቸውም በጣሊያን መዛግብት ሰፍሮ እንደሚገኝ ከመግለጽ ውጪ አጥጋቢ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም።

በበኩሌ በዚህ በአድዋ የድል ቀን አከባበር ላይ እንድገኝ ተጠርቼ የሰማሁት ስድብና ማንቋሸሸ ያልጠበኩት በመሆኑ አስደንግጦኛል። የተዋረድኩና የቀለልኩም አይነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል። በሌላ በኩል ደግሞ መማር ያውም ፕሮፌሰርነት ደረጃ መድረስ እንደዚህ ታሪክን የሚያዛባና የሚናገሩትን እንኳን አስተካክሎ ማስቀመጥ ካላስቻለ፣ ሕዝብን ካስናቀ፤ መሪን ካዋረደ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? የሚል ትዝብትም ፈጥሮብኛል። እንደማስበው ከሆነ ፕሮፌሰሩ ወይ የመጡበትን ዓላማ አያውቁም፤ አልያም እሳቸው የሚፈልጉትን ለመናገር ብቻ የፈለጉ እንጂ ስለ አድዋም ሆነ ስለ ታሪክ የተጨነቁ አይመስሉም።

በሌላ አነጋገር የሳቸውን ሁኔታና አባባል ስናየው፤ አንድ ሰው እቤቱ የአቅሙን ድግስ አድርጎ የኔ የሚላቸውንም እንግዶች ጠርቶ፤ የዛሬው ቀን አባቴ ከጠላት ጋር ገጥመው ያሸነፉበት ቀን ነውና ደስታዬን አብረን እንድናሳልፍ ነው የጠራኋችሁ ብሎ ለተሰበሰበው ሲናገር፤ ከተጠሩት ማኽል አንዱ ተነስቶ “ኤዲያ የአባትህን ድል እንደ ድል ቆጥረህ ይሄን ሁሉ ማድረግ ባልተገባህ ነበር፤ ድሉ እስከዚህ መጋነን የሚገባው አይደለም። እንደውም እንደ አባትህ ወላዋይነትና ደካማነት ቢሆን ኖሮ ዕድሉ ሽንፈት ነበር። እናትህ ብልህ ስለሆኑ ዕድልም ስለቀናቸው ነው ያሸነፉት። ይህንንም ካንተ አባት ጠላቶች ከጻፉት ልረዳ ችያለሁ” ብሎ እንደማለት የሚቆጠር ፈር የለቀቀ ዘለፋ ነው።

ያገሬ ሰው በጨዋታ ማኽል ከአርዕስቱ ውጪ ወጥቶ ሰው ሲዘላብድበት አቶ እከሌ ኧረ ይበቃሃል “ምንድነው አፍ እንዳመጣ መናገር እጅ እንደቆረሰ መጉረስ” ብሎ ያስቆም ነበር። እኛ ግን ይሄን ለማለት እንኳን ዕድል እንዳናገኝ ያለንበት ሁኔታና አጋጣሚው ሳይፈቅድልን ቀርቶ እንደተሸማቀቅን አድምጠን እንደተሸማቀቅን ወጥተናል። ፕሮፌሰሩ በደስታ ሲፍነከነኩ እኛ አንጀታችን ተቃጥሎ ውሎ እንደተቃጠልን አድረናል።

በመሰረቱ ስለ አድዋ ድል ለመናገር ምኒልክን መስደብ ምን አመጣው? ለእቴጌ እርስዎ መጽሐፍ ስለጻፉላቸው እሳቸውን ለማመስገን ምኒልክ መበሻቀጥ ይገባቸዋል ወይ? የአድዋ ድልም እስከዚህ የሚያኮራ አይደለም በዕድል የተገኘ ድል ነው ማለትስ ብልህነት ነው? እዚች ጋ ሽቅብም ቢሆን እያየሁ ምክር ቢጤ ልስጥዎት፤ ምንም አድርገው ሆነ የገቡበት ገብተው አለስልሰውም ሆነ አቃንተው ምኒልክን ያዋረዱ ፕሮፌሰር ከመባል ይዳኑ! አለበለዚያ ግን ዛሬ የተናገሩት ንግግር እንዲሁ ተሰምቶ የሚቀር አይሆንም፤ ነገ ምኒልክ በተነሱ ቁጥር ስምዎ እየተነሳ መዘባበቻ መሆንዎ አይቀርምና አስቡበት።

እቴጌ ጣይቱ የፈጣን አዕምሮ ባለቤት እንደነበሩ እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ ጸሐፊዎችና በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ሁሉ የመሰከሩላቸው መሆኑን ማንም አይክድም። በዚህም እንኮራባቸዋለን። እቴጌ የነበሩበት ደረጃ፣ የታሪክ አጋጣሚውም ስማቸው እንዲገን ማድረጉ አልቀረም እንጂ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ብልህ ሴቶች ያፈራች አገር ናት። ሴቶች ደግሞ በተፈጥሮ ለመላ እና ለዘዴ ከወንድ ይልቅ ፈጣን እንደሆኑ በማያጠራጥር ሁናቴ የታወቀ ነው። እርስዎም ተሳሳቱ እንጂ ባለቤትዎን (ካለዎት) የተጠሩበትን ሁኔታ ገልጸው ምን እንደሚናገሩ ቢጠይቁ ኖሮ ከዚህ የተሻለ አቀራረብ ይዘው እንዲገኙ በመከርዎት ነበር።

ለማንኛውም የተናገሩትን በዝርዝር ከላይ ስላቀረብኩት እኔ ሳልሆን የታሪክ አዋቂዎች፣ በተለይም ስለ አድዋ ጠንቅቀው የሚያቁ ምሁራን ታሪኩን አስተካክለው በማቅረብ እንደሚያርምዎት አልጠራጠርም። ሌላም ጥሪ አለኝ፤ የፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/ሥላሴን መጽሐፍ ያነበብክ፣ የተማርክ፤ የፀሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴን የአድዋ ታሪክን ሰነድ የመረመርክ፤ የፕሮፌሰር የባህሩ ዘውዴን፣ የጳውሎስ ኞኞን፣ የተክለ ፃዲቅ መኩሪያ፣ የብላቴን ጌታ ህሩይ ወ/ሥላሴን መጻሕፍት አብጠርጥረህ የምታውቅ ሁሉ፤ “የፈጠራ ወሬ፣ የውሸት ታሪክ ነው የምታውቀው” ተብለልሃል፤ ታሪክ ተለውጦ ቀርቧል። ንጉሥ ምኒልክ ወላዋይ ተብለውልሃልና ውለህ ሳታድር መልስ ስጥ። ጥቁር ሆኖ ምኒልክን የሚያንቋሽሽ፤ ባርነት የመረጠ ብቻ መሆኑን ያላወቀ ምሁር ተነስቷልና ዝም አትበል። ፀሐፌና ጋዜጠኛ ከያለህበት ውጣ! ብዕርህንም ምዘዝ! እቴጌ ጣይቱን ለማጉላት ምኒልክ የሚሰደቡበት ምክንያት እንደሌለ ተናገር።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሪቦ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ዶክቶር ሹመት ሲሻኝ ምስክርነታችሁን ስጡ! ራስ መንገሻ ዮሐንስ እቴጌ ጣይቱ ብቻቸውን ሲታገሉ የት ነበሩ? ራስ ሚካኤል አሊ በጦርነቱ ጊዜ የት እንደገቡ አይታወቅም ወይ? ራስ ወሌ ብጡል ጦራቸውን የት ይዘው ጠፍተው ነው ጦርነቱ በዕድል የተገኘው? ራስ አባተ ቧ ያለው የሚነግርላቸው ሁሉ ውሸት ነው ወይ? ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ያ ሁሉ ግጥም ያ ሁሉ ዘፈን ከምኒልክ ስም ጋር እየተነሱ የሚወደሱት ተጋኖ እንጂ አልተዋጉም ወይ? እነ ባራቶሪ እነ ደቦር ሜዳ እነ አሪሞንዲ እነ ማቲዎስ … የተባሉ የጣሊያን ጦር አዛዦች በዕድል ነው ወይ የተሸነፉት? በድል ነው ወይ የተማረኩና የፈረጠጡት? እውነቱን ንገሩን! ታሪክ ተወላግዷልና አቃኑ! ይቺ ብረዛ፣ ይቺ ድለዛ፣ ይቺ የታሪክ ቡርቦራ እንዳትሰፋ ኃላፊነት አለባችሁና ዝም አትበሉ።

ፕሮፌሰር ሆይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህንን ያጣመሙትን ታሪክ አቀርቅሮ እንደማያልፍ እወቁ። እፊት ለፊታችን ታሪካችን ሲታጠፍ ዝም ብንል ከርስዎ በላይ ተወቃሾች ያደርገናል። የህሊና ወቀሳ ተሸካሚዎች አስኹኖም ያስቀረናል። ስለ አፄ ምኒልክና ስለአድዋ ድል የሚያትቱ ብዙ የታሪክ መረጃዎችና አሁንም ታሪክ አዋቂዎች እንዳሉ አይዘንጉ። “ወርቁ ቢጠፋ እንኳን ሚዛኑ አልጠፋም” የታሪክ ፍቅፈቃ ሙከራዎችዎን ያቁሙ። ለመሆኑ አፄ ምኒልክ በአድዋ በተቀናጁት ድል የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ፣ ምኒልክ በሌሉበት የአፍሪካና የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ መሪ አድርጎ መምረጡን ያውቃሉ? ወይስ አያውቁም? ይሄንንስ ያገኙት በዕድል ይሆን?

እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ጆርጅ በርክሌይ “የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፋቸው የአድዋ ጦርነትን ሀቅ ከሙሉ መረጃው ጋር ጽፈውት ይገኛል። ያንን ማንም ሊሰርዘውና ሊደልዘው አይችልም። ጀኔራል አርቤርቶ የተባለው የጦር አዛዥ መማረኩ፣ ጀኔራል ባራቶኒ ሸሽቶ ማምለጡ በዕድል የተገኘ ድል ላለመሆኑ ምስክር ነው። ጦርነቱ የተካሄደው በተቀነባበረ የጦር እቅድ፣ በወታደራዊ መረጃ፣ በዲፕሎማሲ ሥራና በፖለቲካ ጥበብ ነበር።

በወቅቱ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን አገራዊ ክብርና ጥቅም ህልውናና ልዕልና በውድ ካልሆነ ደግሞ በግድ ማስጠበቅ ይገባቸው ስለነበር፤ ይሄም የአንድ መንግሥት ዋንኛ ግዴታና ኃላፊነት በመሆኑ በድፍረት የመጣባቸውን የጠላት ጦር በጦርነት ከመግጠም ውጪ አማራጭ እንደሌለው አውቀው አስፈላጊውን ጊዜ በመምረጥ ጦርነት መግጠማቸው በፖለቲካ ጥበብ ብልጫ ወይም ድል ነው።

በወታደራዊ መረጃ (Military Security intellegence) በኩል ደግሞ በባሻዬ አዋሎም ሀረጎት አማካኝነት በተገኘ መረጃ በመታገዝ ሠለጠነ የተባለውን የአውሮፓ ኃይል ለማሸነፍ አስችሏል። ጣልያኖች ከመሸጉበት እንዲወጡ በማድረግ ባልፈለጉት ቦታና ባልመረጡት ጊዜ ወደ ጦርነት እንዲገቡ ተደርጎ ለሽንፈት እንዲበቁ ያደረጋቸው ወታደራዊ መረጃ በመኖሩ ነው።

ወታደራዊ ሳይንስ (Military Science) በተመለከተም ለጦርነት የተንቀሳቀሰ ሠራዊት በአንድ ቦታ ሰፍሮ ጦርነቱ እስኪጀመር ብዙ ጊዜ መቆየት ወታደራዊ ሥነልቦናውን (Military Psychology) እንደሚጎዳው በማወቅ፣ ስሜቱ እንዳይቀዘቅዝና በሎጆስቲክ አኳያ እንዳይጎዳ፣ የውጊያ ዝግጅቱም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ ስንቅም ጨርሶ እንዳይፈታ፤ ቶሎ ወደ ጦርነት መግባት እንደሚገባ በማሰብ ጦርነቱን ለመጀመር ጣሊያኖች ወደ መሸጉበት ከመሄድ ይልቅ እነሱ እንዲመጡ የተሳሳተ መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረግ፤ ጠላት በወታደራዊ ሳይንስ በመበለጡ ለሽንፈት ሊጋለጥ ችሏል።

በዲፕሎማሲ በኩል ደግሞ አውሮፓ ውስጥ በተቀመጡት በራስ መኮንንና በግራዝማች ዮሴፍ በኩል ይሠራ ስለነበር፤ እጅግ አኩሪ ድል ተገኝቷል። ኢትዮጵያውያን ያልሠለጠኑ በመሆናቸው በያዟቸው ምርኮኞች ላይ ሰብዓዊነት የጎደለው ደርጊት ይፈጽማሉ ብለው የአውሮፓ ጋዜጦች ይጽፉ ስለነበር፤ ግራዝማች ዮሴፍ ይሄን በማስተባበል ምርኮኞቹ ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆላቸው እንደተያዙ በመጻፍ ይገልጹ ነበር። እንደውም አውሮፓውያን እንደፈሩት ሳይሆን፤ ምናቸውም ሳይነካና ሳይጎድል ወደ አገራቸው እንዲገቡ በመደረጉ፤ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥልጣኔ እንዳላት ልታስመሰክር ችላለች። ከአንድ መቶ ዓመታትም በላይ ከብዙ አገሮች ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች ይታወቃል።

ይህን የመሰለ የሚያኮራ ታሪክ ያለው ድልና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አንጸባራቂ የነጻነት ብርሃን የሆኑትን የአፄ ምኒልክን ታሪክ የሚያውቅ፤ የነጻነትን ጥቅምም የተረዳ ሰው የድሉን ትንሽነት፣ የምኒልክን ወላዋይነት ሲነገረው ምን ያህል እንደሚያዝን፣ እንደሚቆጣና እንደሚበሳጭ ለማንም ግልጽ ነው። እኔም የአድዋን የድል በዓል ለማክበር ሄጄ የደረሰብኝ ይሄ ነው። ከሁሉም ከሁሉም የከነከነኝን በድጋሚ ጠይቄ እንለያይ። እንደው እውነት! ኧረ ስለእውነት! እምዬ ምኒልክ ወላዋይ ነበሩ ወይ?

No comments:

Post a Comment