Sunday, March 19, 2017

እስቲ ዶሴው ይውጣ | አቻምየለህ ታምሩ



[ክፍል ፫]
አቻምየለህ ታምሩ
«ያ» ትልድ በኢትዮጵያ ላይ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ባዕድ አካላት የብሔር ጭቆና፣ የአማራ የበላይነት፣ ወዘተ በሚል የፈለፈሉትን የፈጠራ ታሪክ አንግቦ ኦነግ፣ ወያኔ፣ ኢሕአፓ፣ ወዘተ በሚሉ የተለያየ «ክፍለ ጦሮች» ስም ቢደራጀም የፖለቲካ አስኳሉ ግን ጀግኖች አያቶቻችን ወደፊት እያዩ የፈጠሯትን ታላቅ አገር ኢትዮጵያን ወደኋላ እያዩ በማፍረስ ትናንሽ የአካባቢ መንግስታትን የመመስረት ህልም ነበር።
የኦነጋውያን ፖለቲካ የመሰረት ድንጋይ «ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ባካሄዱት ዘመቻ ኦሮሞን ቅኝ ገዝተዋል» የሚለው የሁሉም የግራ ፖለቲከኞች ፍልስፍና ነው። ኦነግ የኦሮምያ ሪፑብሊክ ለመመስረት ዱር ቤቴ ያለውም በዚህ የግራ ፖለቲከኞች ፍልስፍና እየተመራ ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ነበር።
የጥንቱን ትተን የቅርቡን እንኳ ብንወስድ በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስቶች ይተዳደር የነበረው የኢትዮጵያ ክልል ከምድር ወገብ ሶስት ዲግሪ እስከ አስራ ስምንት ዲግሪ፤ ከግሪንዊች ሜሪዲያን አስራ ሶስት እስከ አርባ ስምንት በመለስ ሲሆን ይህም ክልል የኢትዮጵያ መሬት ሆኖ የተከለለው ኢትዮጵያን ከ1314-1344 ዓ.ም. በገዙት በአጼ አምደ ጺዮን ዘመን ነበር።
ዛሬ የምናቀርበው ዶሴ የሸውን ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ያስተዳድሯቸው የነበሩትን የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮችን የሚዘረዝር ነው።
የዳግማዊ አጤ ምኒልክ አያት ንጉስ ሣህለ ሥላሴ የሸዋ ንጉስ ነበሩ። ንጉስ ሣህለ ሥላሴ የነገሱት ከጥቅምት ፪ ቀን ፲፰፻፵ እስከ ጥቅምት ፴ ቀን ፲፰፻፵፰ ዓ.ም. ነው። ንጉስ ሣህለ ሥሳሌ በልጅ ልጃቸው በዳግማዊ ምኒልክ የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ዳግም ውህደት እውን ለማድረግ የተነሱት ገና የሸዋ መርድ አዝማች እያሉ ነበር። ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ኦሮምኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ ሲሆን የማይናቅ ቁጥር ያላቸው የጦር አዝማቾቻቸው የአብቹና የቱለማ ኦሮሞዎች ነበሩ።

ንጉስ ሣህለ ሥላሴ የልጅ ልጃቸው ዳግማዊ ምኒልክ ከመወለዳቸው ከአመታት በፊት በጥር 4 ቀን 1835 ዓ.ም. ለንግስት ቪክቶሪያ በፃፉት ደብዳቤ የሚያስተዳድሯቸውን ክፍለ ሀገሮች ስም ዘርዝረዋል። ከታች በታተመው የሣህለ ሥላሴ ደብዳቤ ግርጌ በስተቀኝ በኩል በቀይ ቀስት ባመለከትሁት አምድ በግልጽ እንደተቀመጠው ንጉስ ሣህለ ሥላሴ የሸዋ፣ የጉራጌ፣ የኦሮሞ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የሐረርና የከረዩ ንጉስ እንደነበሩ በግልጽ ይታያል።
ኅሩይ ወልደ ሥላሴ «የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል» በሚል በጻፉት የታሪክ ድርሳን እንዳሰፈሩት ንጉስ ሣህለ ሥላሴ በተወለዱ በ፲፰ ዓመታቸው በአባታቸው ዙፋን አልጋ ወራሽ ሆኖው የተቀመጡት «ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሁሉ ንጉሰ ነገስት እንዲሆን» ቃል ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም ይህ የተፈጸመው በልጅ ልጃቸው በዳግማዊ አጤ ምኒልክ ነበር።
እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከመወለዳቸው አስርት አመታት በፊት አያታቸው ሣህለ ሥላሴ ያስተዳድሯቸው የነበሩትን የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮች ማስተዳደራቸው እንዴት ሆኖ እንደ አዲስ ቅናት ዘመቻና ቅኝ ግዛት ሊሆን ይችላል? እስቲ መልስ ያለህ እስቲ ወዲህ በል! ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የኦሮሞ ቅኝ ገዢ የሚሆኑት ከመወለዳቸው በፊት አያታቸው ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ለ34 ዓመታት ያስተዳድሯቸው የነበሩትን ክፍላተ አገራት በማስተዳደራቸው ነውን?
እነ ጸጋዬ አራርሳ ዛሬ «አዲስ አበባ የኦሮሞ ብቻ ነው»፤ «ዐማራ ለአዲስ አበባ መጤ ነው»፤ ወዘተ የሚለውን ዝባዝንኬ የሚያስተጋቡት የዳግማዊ ምኒልክ አያት ንጉስ ሣህለ ሥላሴ፣ የንጉስ ሣህለ ሥላሴ አያት መርድ አዝማች አስፋው ወሰን ያስተዳድሩት በነበረው ክፍለ ሀገርና ግራኝ አህመድ ያቃጠላቸው ቤተ ክርስቲያኖች ፍርስራሽ ላይ እንደገና በተገነቡት በነ እንዶጥና [የዛሬው እንጦጦ] ማርያም ቤተክርስቲያን ዙሪያ ዐማራ እንዳይኖርና ዐማራውን ለአያት ቅድመ አያቶቹ ምድር ለዋና ከተማችን ለአዲስ አበባ ባዕድ ለማድረግ ነው። ወደፊት በምናቀርባቸው ታሪካዊ ማስረጃዎች በዚህ ጉዳይ በሰፊው እንመለስበታለን።
ወደፊት በምናትመው ሌላ የሳህለ ሥላሴ ደብዳቤ ንጉሱ በሐረርና አካባቢው «አልገብርም ብለው አመጹ» ካሏቸው አመጸኞች ጋር እርሳቸውም ሆነ የልጅ ልጃቸው ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ሁከት ተነስቶ ጦርነት ተካሂዶ ነበር። ይህ ግን የከፋው ንጉስ ከዳግማዊ ምኒልክ ጦር ጋር ለመዋጋት በተቃረቡበት ወቅት በዘመኑ በምስራቅ አፍሪካ ኡጋንዳ ተቀማጭነት የነበረው የእንግሊዝ ወታደሮች አዛዥ ለከፋው ንጉስ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ሲጠይቋቸው እርዳታ እንደማይፈልጉ በመግለጽ በሰጧቸው መልስ እንደገለጹት «ካሸነፈኝ ሀገሩን ጠቅልሎ ይገዛል፤ ካሸነፍኩት ደግሞ እኔ ጠቅልየ አገሩን አገዛለሁ፤ ባይሆን ከውጭ ከባህር ማዶ ለሚመጡት መዋጊያ ትረዳናለህ» እንዳሉት እንጂ ቅኝ ለመግዛት የተደረገ ጦርነት አልነበረም።
መልካም ቅዳሜ!

No comments:

Post a Comment