Thursday, March 30, 2017

“ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች አሁንም ጸረ ሰላም ሃይሎች ይንቀሳቀሳሉ” ብለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አራዘሙት | ዜና ትንታኔ

    

ከፋሲል የኔዓለም | የኢሳት ጋዜጠኛ
ዛሬ የኢህአዴግ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ 4 ወራት እንዲራዘም ወስኗል። አቶ ሲራጅ ለአዋጁ መራዘም እንደ ምክንያት ያቀረቡት “ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች አሁንም ጸረ ሰላም ሃይሎች ይንቀሳቀሳሉ” የሚል ነው። በመላ አገሪቱ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ህዝቡ አዋጁ እንዲራዘም መጠየቁና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም “አዋጁ ቢራዘም መልካም ነው” የሚል አስተያየት መስጠቱ ተገልጿል።

ህወሃታውያን በሚቀጥሉት 4 ወራት ውስጥ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ “ ጸረ-ሰላም ሃይሎችን” በቁጥጥር ስር ማዋል ይችሉ እንደሆን እናያለን። ግን የገረመኝ የአርበኞች ግንቦት7 ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሚቀጥሉት 4 ወራት ውስጥ የሚሰሩ ስራዎችን ለይቶ ውሳኔ ማሰለፉን በሰማሁ በሰዓታት ውስጥ አዋጁ ለ4 ወራት የመራዘሙን ዜና መስማቴ ነው። ያጋጣሚ ነገር ይሆን ወይስ …?
ለማንኛውም ህወሃት/ኢህአዴግ አካሄድኩ የሚለውን የዳሰሳ ጥናት በተመለከተ ኢሳት የካቲት 14 ቀን 2009 ዓም ባወጣው ዜና እንዲህ ብሎ ነበር- “ በተለያዩ የጎንደር ቀበሌዎች በተካሄዱ የህዝብ ስብሰባዎች፣ የአገዛዙ ካድሬዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት በኩል የህዝቡ አስተያየት ምንድነው በሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ህዝቡ ግን በቀጥታ ከመናገር ይልቅ በጽሁፍ ፣ “ እናንተን አንቀበላችሁም፣ አናውቃችሁም፣ ከህዝብ ውጭ ሆናችሁዋል” የሚል መልስ በብዛት መስጠቱ ካድሬዎችን አስደንግጧል። አንዳንድ ሰዎች “ አዋጁን ስታውጁ እኛን አላማከራችሁንም፣ ሁሌም በራሳችሁ ከላይ ወስናችሁ ከጨረሳችሁ በሁዋላ ነው እኛን የምትጠይቁን፣ እኛ ደግሞ ኮማንድ ፖስት ተነሳ አልተነሳ ከግድያና አፈና አትታቀቡም፣ ብትፈልጉ አንሱት ባትፈልጉ ተውት፣ ጥቅሙን መጨረሻ ላይ ታገኛላችሁ” የሚሉ አስተያየቶችም በብዛት ተሰጥተዋል።”
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቡድን አዋጁ እንዳይነሳ አስተያየት መስጠቱን በተመለከተም ኢሳት በጥር 30 ዘገባው ላይ እንዲህ ብሎ ነበር – “በአማራ ክልል የሚታየውን የጸጥታ ሁኔታ ለመገምገም ከፌደራል የተላከው የኮማንድ ፖስቱ አጣሪ ቡድን ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳ ህዝቡ በቀጥታ በመንግስት ላይ ከእስካሁኑ የከፋ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል ሲል አስጠንቅቋል። ኮማንድ ፖስቱ “ የክልሉን ህዝብ ገትቶ የያዘው መሳሪያ ነው” ያለ ሲሆን፣ አዋጁ ቢነሳ ከእስካሁኑ በከፋ ሁኔታ አመፁን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል” ብሎአል፡፡ለአንድ ወር ያክል በጎንደር፣ በባህርዳር እና በአዊ ዞን የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ የህዝቡን ሁኔታ ማጥናቱን የሚገልጸው የፌደራል ኮማንድ ፖስት ቡድን፣ በአማራ ክልል የተካሄደው ተሃድሶ የይምሰል እና ስር ያልስደደ ነው ሲል አጣጥሎታል።”
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተራዘመው በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎችን ለመደምሰስ አይመስለኝም። ይህ እንደማይሆን እነሱም ያውቁታል፤ ባለፉት 6 ወራት ታጋዮቹ ራሳቸውን በማጠናከር በኩል ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል፤ “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚባልበት ጊዜ አልፏል። አዋጁን ለማራዘም የተገደዱት በተለይ በ2 ምክንያቶች መሆኑን አምናለሁ። ጥልቅ ተሃድሶ ብለው ባዘጋጁዋቸው መድረኮች ላይ የህዝቡ ቁጣ በቀላሉ እንደማይበርድ አረጋግጠዋል። በመድረኮች ላይ የተሰጡት አስተያየቶች ፍርሃት ለቆባቸዋል። አንድም ሰው እነሱን የሚደግፍ አስተያየት አለመስጠቱ ግራ አጋብቷቸዋል። በእኔ እምነት ህወሃታውያናንን እያስፈራቸው ያለው በድንበር አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በበለጠ የመሃል አገሩ ህዝብ ቁጣ ነው። ሰሞኑን በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ፣ “መሃሉ ዳግም ከተነሳ ከእንግዲህ በመሳሪያ አናቆመውም” የሚል አስተያየት በከፍተኛ ባለስልጣን ተነግሯል። በጎንደር አንድ የመኮንኖች ስብሰባ ላይም እንዲሁ መኮንኖች ” ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልተገኘ በስተቀር የህዝቡ ተቃውሞ በጉልበት የሚቆም አይሆንም” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ወታደሩ ሰልችቷል።
ሌላው ምክንያት ደግሞ በድርጅቶች ውስጥ ያለው መከፋፈል እየጨመረ መሄዱ ነው። በተለይ ኢህአዴግን ከመሰረቱት 4 ድርጅቶች ውስጥ የሁለቱ ህልውና አዳጋ ላይ ወድቋል። በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ በማንኛውም ጊዜ “ውስጣዊ ፍንዳታ” ሊከሰት ይችላል። አዋጁ በሚቀጥሉት 4 ወራት ውስጥ እነዚህን ድርጅቶች ከውስጣዊ ፍንዳታ ይታደጋቸው አይታደጋቸው የምናየው ይሆናል።
ለማንኛውም ግን አዋጁ፣ በአንድም ይሁን በሌላ፣ አገዛዙን ዋጋ እያስከፈለው ነው። የገጽታ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የአመኔታ ወዘተ።

No comments:

Post a Comment