Saturday, March 25, 2017

የታሰርኩት ሃሳቤን በነፃነት በመግለጼ ብቻ ነው !

   



የታሰርኩት ሃሳቤን በነፃነት በመግለጼ ብቻ ነው !
— “ለአገሬ የተሻለውን ሁሉ እንዴት ቢደረግ እና ባደርግ ጥሩ ይሆናል ብዬ የማምነዉን ሃሳቤን፣ በነፃነት ከመግለጽ ወደኋላ ሊጎትተኝ የሚችል ማናቸውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ አይደለውም” —
አሁን ላይ በአገራችን የሚታየው የፖለቲካ ቀውስ እና አለመረጋጋት እንዳይከሰት፣እንዲሁም ዜጎችን በጅምላ ማሰር እና ማሰቃየት መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል በተደጋጋሚ የገለጽኩት ሃሳብ ነው። የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች፣ እስር ቤት እና ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ እነሱን በመጠይቅ የእነሱን ሃሳብ ምን እንደሆነ ለመግለጽ የቻልኩትን ሁሉ ጥረት አድርጊያለው። በአዘጋጅነት እና በተለያየ ደረጃ በስራዎባቸው ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ የተለያየ አመለካከቶች እና ሃሳቦች፣ የሌላውን መብት ሳይጋፉ በነፃነት እንዲስተናገዱ ፣ የራሴን ተፈጥሯዊ ነፃነቴን ተጠቅሜ ሃሳቤን ለመግለፅ፣ እስከ ታሰርኩበት ጊዜ ድረስ የቻልኩትን አድርጌያለሁ ። ሆኖም ግን የታሰርኩት የሌላውን መብት ጠብቄ ሃሳቤን በነፃነት በመግለጼ ብቻ ነው!
— አሁንም ቢሆን በዜጎች ላይ የሚደርስ በደል አጥብቄ እቃወማለው። ለአገሬ የተሻለውን ሁሉ እንዴት ቢደረግ እና ባደርግ ጥሩ ይሆናል ብዬ የማምነዉን ፣ ሃሳቤን በነፃነት ከመግለጽ ወደኋላ ሊጎትተኝ የሚችል ማናቸውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ አይደለውም።በመታሰሬ ቀድሞ የነበረኝ አቋም ሊቀየር አይችልም ። ይህን እምነቴን በእስር ቤት ሆኜ ለሚመለከተው አካል ቀርቤ ለመግለፅ ፈልጌ ነበር። ከታሰርኩበት ቀን ጀምሮ እስካሁን የአሰረኝ የትኛውም አካል ቀርቦ ሊያናግረኝ አልቻለም ። በእስር ቤት በነበረኝ ቆይታ ሙሉ ለሙሉ የማሽተት እና ሽታን የመለየት ችግር አጋጥሞኛል ። እክምና እንዳገኝ ለየካቲት 12 ሆስፒታል ሪፈር ቢፃፍልኝም እስካሁን እክምና እንዳላገኝ ተደርጓል ።
— ይህ ከላይ የቀረበው ሃሳብ ፣በዛሬው ዕለት ከጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ጋር በነበረኝ አጭር ቆይታ ያጋራኝ መልዕክት ነው ። ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ጨምሮ በግምት ወደ 15 የሚሆኑ እስረኞች ፣ቂርቆስ ክ/ከተማ ፖፑላሬ ማዘዣ ጣቢያ ፣ ወደ ቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንዲዘዋወሩ ተደርጓል ። በትላንትናው ዕለት የቀድሞ አንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺ ፣ ታስሮ ከነበረበት በቂርቆስ ክ/ከተማ ቄራ ማዘዣ ጣቢያ ቀድሞ ወደ ታሰረበት ቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተዘዋውሮ በእስር ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት ጋዜጤኛ ኤሊያስ ገብሩ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በሚገኘው እስር ቤት አንድ ላይ ታስረው ይገኛሉ። በተያያዘ መረጃ በአስቸኳይ አዋጁ ምክንያት ታስረው የነበሩ በተለያየ ፖሊሲ ጣቢያ የሚገኙ እስረኞች እየተፈቱ ነው። ይሁን እንጂ አስቸኳይ አዋጁ ይፋ ከሆነበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረሰ በተለያዩ ፖሊሲ ጣቢያ ታስረው የሚገኙ በርካቶች ናቸው። – (ይድነቃቸው ከበደ)

No comments:

Post a Comment