Saturday, March 18, 2017

ሕወሃቶች የአስተሳሰብ ድሃ ስለሆኑ አሰሯቸው #ግርማ_ካሳ

    


13435525_1729570653968996_4208997778222517402_n 10420347_376346742541562_1054234850276790202_n
ለገሰ ወልደሃናን እንደ ወንበዴ አፍነው ወደ ወህኒ ወሰደዉታል። የወሰዱትም ኢሰብአዊና አሰቃቂ የሆኑ ቶርቸሮችን ፣ በነጌታቸው አሰፋ ቀጥተኛ ትእዛዝ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጽሙ ጨካኝ የሕወሃት መርማሪዎች በሞሉበት በማእከላዊ እሥር ቤት ነው።
ለገሰ ወልደሃና አገሩን እና ሕዝቡን የሚወዱ በኢትዮጵያ ካሉ ደፋርና ሰላማዊ የዴሞክራሲ ታጋዮች አንዱ ነው። በተለይም በመኢአድ ዉስጥ በአመራሮች መካከል ( አቶ አበባው መሐሪና አቶ ማሙሸት አማረ) በነበረው ችግር ምክንያት፣ መኢአድ ችግር ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜና ፓርቲው ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ በማያደርገበት ጊዜ፣ ለገሰ ወልደሃና ደከመኝ ሳይል ለትግሉ ደፋ ቀና ሲል የነበረ ታታሪ ወጣት ነው።
በተለይም ፣ ከሌላ የመኢአድ አባልና ቁርጠኛ ታጋይ አወቀ አባተ ጋር በመሆን፣ የመኢአድ እስረኞችን የሚጎበኝ፣ ያሉበትን ሁኔታ ተከታትሎ ለሕዝብ የሚያቀርብ፣ የትግል አጋራቹን ያልረሳ፣ የሕሊና እስረኞች ተቋርቋሪነቱ የሆነ ታጋይ ነው። ብዙ ጊዜ ከታዋቂ ፖለቲከኞች ጋር ደፋ ቀና ማለት እንወዳለን። ለታወቁ እስረኞች ሁላችንም እንጮሃለን። ግን ያልተዘመረላቸው፣ ለትግሉ ዋጋ እየከፈሉ እየተሰቃዩ ያሉ፣ የተረሱትን ግን ማስታወስ ብዙዎቻችን አይሆንልንም። ለገሰና አወቀ ግን በየጊዜው ነበር ኢትዮጵያዉይን የተረሱ እስረኞችን እንዲያስታወሱ ሲደክሙ የነበሩት።
አወቀ አባተ ከታሰረ ወራት አልፎታል። ምንም መረጃ ሳያቀርቡ፣ ሳይከሱት ይኸው እያንገላቱት ነው። አሁን ደግሞ የትግል ጓደኛው ለገሰ ወልደሃና አወቀ አባተን ተቀላቅሏል።
ለገሰም ሆነ አወቀ፣ መታሰራቸውን እንደ ክብር ነው የሚቆጥሩት። የፕሮፌሰር አስራት ልጆች ናቸዉና። እነዚህ ሁለት ወጣቶች ነፍጥ አላነሱም። ቦምብ አልያዙም። አንድ ጠጠር አልወረወሩም። ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸዉን ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠቅመው ጻፉ፣ ጦመሩ። በአገዛዙ የሚፈጸመውን ግፍና ሰቆቃ ለሕዝብ አጋለጡ። ሆኖም ኢትዮጵያ ዉስጥ መጦመር፣ ሽብርተኝኘትና ወንጀል በመሆኑ ፣ አሰራቸው።
ዜጎችን ስለጻፉ ማሰር፣ የተሸናፊዎች ተግባር ነው። ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ሲያቅታቸው የሚጽፉትን ማሰራቸው ሕወሃቶች የሐሳብ ድሃ መሆናቸውን ነው በግልጽ ያመላከቱት።
ሁለተኛ እነ እስክንድር ነጋን ካሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ፣ አሥር ሺህ እስክንደር ነጋዎች እንደተወለዱት፣ አሁን እነ ለገሰን ማሰሩ፣ የዜጎችን አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን የበለጠ ለትግል እንዲነሳኡ የሚያደረግ ነው። አንዱ ቀዳዳ ዘጋን ሲሉ ሌላ አስር ይከፈታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደው ቆርጧል። ጨክኗል። ፈረንጆች እንደሚሉትሀ ” the Gini is out of the bottle” ። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነቱን እስካላገኘ ድረስ ወደ ኋላ አይመለስም።
ሶስተኛ አገዛዙ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር እያደረኩ ነው እያለ በዚህ መልኩም ዜጎችን ማሰሩ፣ ድርድሩን እንዲከሽፍ ዉስጡ ዉስጡን እየሰራ መሆኑንም የሚያሳይ ነው።፡
በግሌ በጣም ተስፈኛ በተቻለ መጠን ነገሮች በሰላም በዉይይት እንዲፈቱ እስከ ጫፍ መሄድ የምፈልግ ሰው ነኝ።፡ግን እዉነቱን ልናገርና ተስፋ ላለመቁረጥም ከዉስጤ ጋር በጣም እየታገልኩ፣ ተስፋ ወደ መቂረጡ እየተጠጋሁ ነው።

No comments:

Post a Comment