ዛሬ በኢትዮጵያ ታትሞ የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያስነበበው ዜና እጅግ የሚያስገርም ሆኖ አግኝተነዋል:: መንግሥት በሽያጭ ካዘዋወራቸው የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ እንዳልተከፈለው የመንግሥት የልማት ደርጅቶች ሚኒስቴር ማስታወቁን የሚዘግበው አዲስ ዘመን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ባለዕዳ የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ «አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብሩን ልክፈል ብልም መንግሥት ገንዘቡን ሊረከበኝ አልቻለም» ሲል ገልጿል ሲል አስነብቧል:: ዘገባውን እንደወረደ ያንብቡትና በዚህች ሃገር ውስጥ የሚሰራውን ውንብድና ታዝበው አስተያየትዎን ይስጡበት::
የአዲስ ዘመን ዘገባ እንደወረደ:-
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቲ እንዳስታወቁት፤ ድርጅቶች ከመንግሥት ወደ ግል ሲዛወሩ ከመሸጫ ዋጋቸው ውስጥ 35 በመቶ በመክፈል ቀሪውን ክፍያ በአምስት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን እስከአሁን ድረስ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዕዳቸውን ያልከፈሉ ድርጅቶች አሉ። ጠቅላላ እዳቸውም ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ይደርሳል።
በዘንድሮ የግማሽ ዓመት ላይ በተደረገው ግምገማ ዕዳቸውን ካልከፈሉ ድርጅቶች መካከል ሚድሮክ ኢትዮጵያ ሁለት ቢሊዮን ብር ባለመክፈል ከፍተኛው ባለዕዳ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሌሎችም ድርጅቶችም ቢሆኑ በውሉ መሠረት ዕዳቸውን ባለመክፈላቸው ወለዱና ቅጣቱ በየቀኑ እየጨመረባቸው ነው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻም፤ ዕዳ ያለባቸውን ድርጅቶች በአካል በመጥራት ተቋማቸው አነጋግሯቸዋል። በዚህም ድርጅቶቹ ከምርትና ምርታማነት እንዲሁም ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ ችግር እንዳለባቸው መገንዘብ ተችሏል። ይሄንኑ ችግራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ድርጅቶቹ የተከለሰ ዕቅድ እንዲያቀርቡ በማድረግ ዕዳቸውን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲከፍሉ ድርድር እየተደረገ ይገኛል።
መንግሥት በውሉ መሠረት በህግ አግባብ ድርጅቶቹን ወርሶ በመሸጥ ዕዳውን መውሰድ ቢችልም፤ በድርጅቶቹ የሚሠሩ ሠራተኞችን ስለሚበትንና በሂደቱም አገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ስለሚያጓድል የድርጅቶቹ ዕዳ መክፈያ ጊዜ ቢያልፍም በድርድር እንዲከፍሉ ለማድረግ ወደ ድርድር መግባቱን እንደመረጡ ነው ዶክተር ግርማ ያስታወቁት። በድርድሩ መሠረት ዕዳቸውን፣ ወለዱንና ቅጣቱን በማይከፍሉ ድርጅቶች ላይ ግን መንግሥት በህግ አግባብ እንዲከፍሉ ያደርጋልም ነው ያሉት።
በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮንንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ፤ በበኩላቸው ከመንግሥት ወደ ግል የተዛወሩ 29 ድርጅቶች ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ያልከፈሉት ዕዳ አለባቸው ብለዋል።
እንደ አቶ ወንዳፍራሽ ገለጻም፤ ከእዳው ውስጥም ሁለት ቢሊዮን ብሩ በሚድሮክ ኢትዮጵያ በተያዙ ስድስት ድርጅቶች ላይ ያለ ነው። አንድ ቢሊዮን ብር የሚሆነው ገንዘብ ደግሞ የሌሎች 23 ድርጅቶች ዕዳ ሲሆን፤ በተደረገው ድርድር መሠረት ዕዳቸውን ለሚከፍሉ ድርጅቶች የባለቤትነት ማረጋጋጫ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል።
ሚድሮክ አለበት የተባለውን ዕዳ አስመልክቶ ምላሽ የሰጡን የሚድሮክ እህት ኩባንያ የሆነው የሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ስትራቴጅና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንትና ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይበልጣል ሽመልስ፤ «ድርጅቶቹ ስንረከባቸው የምርታማነት ችግር ነበረባቸው። ምርታማነታቸውን ሳንጨምርና አቅማችንን ሳናጠናክር ወደ ክፍያ ብንገባ የበለጠ ስለምንዳከም የገንዘብ ክፍያው ሊዘገይ ችሏል። የክፍያው መዘግየት ድርጅቱን ቢጎዳውም መንግሥት ግን ተጨማሪ ገንዘብ በወለድና በዕዳ እያገኘ ነው» ብለዋል።
ሚድሮክ በላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪና የቡና ማዘጋጃ ስም ያለበትን አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ዕዳውን ሙሉ በሙሉ ለመክፈል ከመስከርም 2009 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጁ ቢሆንም፤ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ገንዘቡን ሊቀበልና የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አሟልቶ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ የጠቆሙት አቶ ይበልጣል፤ በዚህ ምክንያት በድርጅቱ ላይ በየቀኑ ተጨማሪ ገንዘብ እየወለደባቸው መሆኑን ነው ያስታወቁት።
የሌሎቹን ድርጅቶች ዕዳም እስከ ሰኔ 2009 ዓ.ም ድረስ ለመክፈል የጊዜ ሰሌዳ ማውጣታቸውንና ዝግጁ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ይበልጣል፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለዚህ ዝግጁ ሊሆንና ችግሮቹን አስተካክሎ ማስረከብ እንዳለባት አሳስበዋል።
አጎናፍር ገዛኸኝ
No comments:
Post a Comment