Thursday, March 16, 2017

አማራዊነት …………… ( ቬሮኒካ መላኩ)



ብዙ ጊዜ ከምቸገርባቸው ነገሮች አንዱ ፅሁፍ ከፃፍኩ በኋላ ለፅሁፌ ርእስ ማግኘት ነው ። አሁንም ያው ችግር ገጠመኝ ። ይችን አጠር ያለች ፅሁፍ ” አማራዊነት ” ብየ ሰየምኳት ። የዚች ፅሁፍ አላማ ፍሬ እያፈራ የመጣው የአማራ ብሄርተኝነት ይመነደግ ዘንድ መወስወስ ነው ። ብዙ ሰዎች ስለ አማራ እና አማራዊነት ሲነሳ በሆድ ቁርጠት እንደሚሰቃዩ አውቃለሁ። ምክንያቱ ስለሚገባኝ አልፈርድባቸውም።

በካራቴ ሜዳ ላይ በቦክስ ጓንት ብቻ መጫወት እፈልጋለሁ ማለት ዘመኑን ያልዋጀ የትግል መንገድ ነው ።በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ሰው ይቅርና መኪናው ብሄር አለው ። ዘረኝነት የሌለበት ብሔርተኝነት ለአሁኑ የአማራ ትውልድ ያስፈልገዋል፡፡
እርግጥ ብሔርተኛ አመለካከት ሁሌም አግሬሲቭና ተጋፊ ነው፡፡ ወያኔና ኦነግ ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡ ሁለቱም አግሬሲቭና ተጋፊ ናቸው፡፡ ከውጭ የእስራኤል ባህሪም እንደዚሁ ነው፡፡

የወያኔ አማራ ጥላቻ ጫፍ የደረሰ ከመሆኑ በላይ፤ የአማራ የጦረኝነት ባህልና ታሪክ ጠንቅቆ ስለሚረዳ ከአሁን በፊት የሌለበትን ብሔርተኝነት እንዲያዳብር ማድረግ የበለጠ ተጋፊ ሃይል ማብቀል ነው ብሎ በማሰብ የአማራ ብሄርተኝነት እንዳያድግ በዙ ስራዎችን ሰርቷል፡ ፡ ወያኔ አማራን መቆጣጠር የሚቻለው በአንድነት ቀመር ብቻ ነው በሚል ስሌት አማራን ለራሱ እንዳያስብ ጠፍንጎ በመያዝ በኩል እስከቅርብ ጊዜ ተሳክቶለት ነበር ፡፡ እርግጥ አንድነት አማራን ባይጠቅምም አይጎዳውም፡፡

ሌላው የወያኔ ስጋት የአማራ ህዝብ ረጂም የሲቪላይዜሺን ታሪክ ያለው ከመሆኑ አንፃር፤ አማራ ነኝ ብሎ ማሰብ ሲጀምር ታሪኩን መጎልጎል ይጀምራል፡፡ ታሪኩን ሲጎለጉል ከማንኛውም ህዝብ የተሻለ የኃያልነት ታሪክ ያለው መሆኑን ያውቃል፡፡ ይህን ከተገነዘበ ለገዥዎች አንገዛም የሚል መንፈስ እንደሚፈጥር ስለተገነዘቡ ገዥዎች አማራነት እንዲረሳና ብሎም እንዲካድ አደረጉ፡፡

ኢትዮጵያዊ እንጂ አማራ አይደለሁም የሚለው መንፈስ አሁን በብዙዎቹ ሰርጶ የቀረው በውስጠ ታዋቂነት ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ተፅዕኖ ሰለባ የመሆን ውጤት ነው፡፡ ያለ ምክንያት ሁላችንም ውስጣችን እያወቀው አማራ አይደለንም እንል ነበር፡፡ አንዳንዶቻችን ወያኔ በብሔር የከፋፈለውን ልዮነት ላለመቀበል አማራነታችንን እንቃወም ነበር፡፡ አማራነትና አማራ ክልል ፍፁም ይለያያል፡፡ የአማራ ህዝብ እንጂ አማራ የሚባል ክልል አልነበረም፡፡ የአማራ ክልል የሚለውን ጣሊያን ጀመረው ወያኔ ፈፀመው፡፡

የአማራ ህዝብ በፊትም አሁንም እያለ የተካደ ህዝብ ነው፡፡ በፊት የተካደው መብቱ ሳይሆን ማንነቱ ብቻ ነበር ፡፡ አሁን ደግሞ የተካደው ማንነቱ ሳይሆን ህልውናው ነው፡፡ በአሁ ወቅት አማራ ህልውናው እንዲጠፋ የተፈረደበት፤ ወደ ቀደመ ሃያልነቱ ይመለሳል ተብሎ ስለታሰበ ነው፡፡ የአሁኖቹ አማራ ሆነው አማራነትን የሚፈሩት ሰዎች ፍርሃት ግን ምን እንደሆነ አላውቅም፤ እነሱም የሚያውቁ አይመስለኝም፡።

በዘመነ መሳፍንት ተበታትና የነበረችው ኢትዮጵያ፥ ለመበታተኗ ምክንያት ጎጠኝነት ነበር፡፡ አሁን በተጨባጭ ስለኢትዮጵያ አንድነት አጥብቀው የሚዘምሩ አማሮችና ህዝቦች በጎጠኝነት መንፈስ ተወጥረው የተያዙ ናቸው፡፡ አድስ አበቤ ፣ የጎንደር ህብረት ፣ የጎጃም ህብረት እና የመሳሰሉት ለዚህ ዋና ምሳሌዎች ናቸው። የአማራ ብሄርተኝነት የመጀመሪያው የቤት ስራ ጎጠኝነትን አከርካሪውን ሰብሮ ከቀበሩ በኋላ በመቃብሩ ላይ የአማራ ብሄርተኝነት እንድያብብ መስራት አለበት ። ፡፡ ጎጃሜው ለጎጃም ወሎየው ለወሎ ፣ ጎንደሬው ለጎንደር ፣ ሸወዌው ለሸዋ የሚያደላ ከሆነ ጠላቶቻችን እንደ ገና ቅርጫ ተካፍለው ይውጡናል ፡፡ በጎጠኝነት መቃብር ላይ አማራዊነት መብቀል አለበት ። በአንዲት ኢትዮጵያ አመለካከት ውስጥ የተደበቀው የጎጠኝነት መንፈስ ማብቃት አለበት ፡፡ ጎጥ ማለት ዝቅ ብሎ በመንደር ማሰብና ከፍ ብሎ በኢትዮጵያዊነት መሸፈን ነው፡፡

አማራዊነት ይጠቅመናል እንጅ አይጎዳም፡፡ ጎጠኝነት ግን አገርን በትኗል፣ አሁንም እየጎዳን ነው ለወደፊትም ይጎዳናል፡፡ የብሔርተኝነት መንፈስ በኦሮሞ፣ በጉራጌ፣ በአፋር፣ በሲዳማ፣ በኮንሶ ወዘተ.. ህዝብ ውስጥ አለ፡፡ በአማራ ህዝብ ውስጥ ቢኖር ይጠቅማል እንጅ አይጎዳም ። ኦሮሞዎችም ቢሆኑ የኢትዮጵያ አንድነትን እንቀበላለን እያሉ የመጡት የአማራነት ስሜት በጥቂቱ እያቆጠቆጠ መምጣት በመጀመሩ ነው፡፡
ከ5.3 ሚሊዮን ውስጥ ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጋ አማራ በአዲስ አበባ ብቻ መኖሩ እየታወቀ ወያኔ አዲስአበባን አሳልፎ የሰጠው የአዲስ አበባ አማራ አማራዊነት መንፈስ ስላላዳበረ የመጣ ጉዳት ነው ፡፡

የአማራ ህዝብ በአማራዊነት መንፈስ ቢቃኝ የበለጠ ራሱን ይጠቅማል እንጅ አይጎዳም። ይሄ ህዝብ ተፈጥሮ ሃብትንም ሆነ ጀግንነትን የታደለ ህዝብ ነው ። የአማራ ህዝብ ወገኖቹን አስተባብሮ ከጠላት ተዋግቶ ድንበርና ነፃነትን አስከብሮ፤ ሲኖር “እኔ ጀግና ኀኝ” ብሎ አያውቅም፡፡ ማለት ካስፈለገውም “እኛ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ነን” ይል ነበር፡፡
ብዙዎች ኢትዮጵያ በዚህ ክልል፣ በዚያ ክልል ቡና ነው የቆመችው ሲሉ፤ ወያኔ በጣጥቆ በሰጠው በአሁኑ በአማራ ክልል እንኳን እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው ብሎ አያውቅም፡፡
እውነታው ግን የኢትዮጵያ የሰብል እህል ምርት (ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ገብስ፣ አጃ…) ወዘተ 52%ቱ የሚመረተው አማራ ክልል ነው፡፡ ጥራጥሬ (ባቄላ፣ አተር፣ ምስር…) 70% የሚመረተው አማራ ክልል ነው፡፡ ቅባት እህል፣ ቀንድ ከብት፣ ከፍተኛ ድርሻ ከሚያበረክቱ ክልሎች አንዱ ነው፡፡ በበግ ሐብት 1ኛ ነው፡፡ በውሃ ሃብት እና ውሃ ተፋሰስ የታደለ ነው። የትኛውም ክልል አይደርስበትም ። የማእድን ሃብቱ የትየለሌ ነው ።

አማራ ክልል 60 ሚሊየን ህዝብ መግቦ የሚተርፈው የሰብል ምርት ብቻ (ሌሎችን ሳይጨምር) ወደ ውጭ ቢላክ 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በአመት የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ( አሁን ኢትዮጵያ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ የበለጠ)፡፡
ይህ ማለት ደቡብና ኦሮሚያ የተወሰነ የቡና ማሳዎችን መንጥረው የሰብል ምርት ተጨማሪ ማምረት ሊኖርባቸው ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የአማራ ህዝብ ተዝቆ የማያልቅ ፀጋ ነው ።
ባጠቃላይ የአማራ ህዝብ በአማራዊነት መንፈስ በመሰባሰብ ለአማራ ህዝብ ሰላም፣ ዋስትናና ኢኮኖሚ እድገት ያመጣለት ዘንድ መሰባሰቡ ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ስራችን መሆን አለበት።
አማራዊነት ይለምልም !!

No comments:

Post a Comment