Monday, March 27, 2017

102 የመንግስት ተቋማት እና የስርዓቱ ድርጅቶች የመብራት ዕዳቸውን አንከፍልም አሉ


 1  128  129

BBN News – የተጠቀሙበትን የመብራት ክፍያ ያልከፈሉ 90 የመንግስት ተቋማት መኖራቸው ተጠቆመ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደገለጸው ከሆነ፣ ባጠቃላይ የስድስት ወራት የመብራት ክፍያ ያልከፈሉ ተቋማት 102 ሲሆኑ፣ ከነዚህም ውስጥ 90 የሚሆኑት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ 102 የሚሆኑት ተቋማት በአጠቃላይ ከ77 ሚሊየን ብር በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ውዝፍ ክፍያ እንዳለባቸውም ተነግሯል፡፡ ሆኖም ክፍያውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአዲሱ ስሙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚባለው እና የቀድሞው መብራት ኃይል፣ የመብራት አገልግሎት ክፍያ በማይከፍሉ ማንኛውም ተቋማት ላይ አገልግሎቱን የማቋረጥ ስልጣን ቢኖረውም እስካሁን ድረስ ግን በ102ቱ ተቋማት ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱ ታውቋል፡፡ አንድ የክፍያ ቀን አለፈ ብሎ የግለሰቦችን ቤት መብራት ለመቁረጥ ማንም የማይቀድመው ይኸው ተቋም፣ ከ77 ሚሊዬን ብር በላይ ዕዳ ያለባቸውን እና ለሁለት ዓመት ያህል ከፍያ ያልፈጸሙ 102 ተቋማትን በዝምታ ማለፉም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሔር ታፈረ እንደገለጹት ከሆነ፣ የተገለገሉበትን ክፍያ ያለመፈጸም ችግር በብዛት የሚስተዋለው በስኳር እና በብረታ ብረት ድርጅቶች ላይ እና በአብዛኛው በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ነው፡፡ ክፍያን ያለመፈጸም ችግር በመንግስት ተቋማት ላይ መስተዋሉን የሚገልጹት ኃላፊው፣ በዚህ ሂደት እስከ ሁለት አመት ለሚሆን ጊዜና እስከ 17 ሚሊየን ብር የአገልግሎት ክፍያን ያልከፈሉ ተቋማት ተለይተው መታወቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ ከሆነው 17 ሚሊየን ብርና ከዛ በታች ውዝፍ እዳ ያለባቸው ተቋማት በድምሩ 102 ሲሆኑ፣ ከዚህ ውስጥ 90 ያህሉ የመንግስት ተቋማት መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡ በአማካይ ለስድስት ወራት ያህል ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ ያልፈጸሙት ተቋማት ውዝፍ ዕዳቸው ተጠራቅሞ አሁን ላይ 77 ሚሊዬን 965 ሺህ 298 ብር ደርሷል፡፡
ዕዳ ያለባቸው ተቋማት የተጠቀሙበትን የኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያ እንዲከፍሉ በተደጋጋሚ በደብዳቤ እና በአካል ከተቋማቱ ጋር ንግግር ቢደረግም፣ ተቋማቱ ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆናቸውም ተነግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገለግሎት በሚሊዬን የሚቆጠር ዕዳቸውን አልከፈሉም ያላቸውን የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ስም በይፋ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡ ሆኖም በቅርቡ ስማቸውን ይፋ እንደሚደርግ አስታውቋል፡፡
ዕዳቸውን ካልከፈሉት 90 የመንግስት ተቋማት ወጭ የተቀሩት የግል ተቋማት ሲሆኑ፣ እነዚህ ተቋማት የስርዓቱ ሰዎች ድርጅቶች ሳይሆኑ እንደማይቀር ተጠርጥሯል፡፡ የተጠቀሙበትን የአገልግሎት ክፍያ በድፍረት ‹‹አንከፍልም›› ሊሉ የሚችሉት በስርዓቱ ሰዎች ባለቤትነት የሚተዳደሩ ድርጅቶች ብቻ መሆናቸውን የሚገልጹ ታዛቢዎች፣ ስራቸውን በገለልተኛነት የሚሰሩ የግል ባለሀብቶች እንዲህ ዓይነት ድፍረት ውስጥ እንደማይገቡም ታዛቢዎቹ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጫን ያለ እርምጃ ለመውሰድ የፈራውም፣ ዕዳቸውን ያልከፈሉት የግል ተቋማት በስርዓቱ ሰዎች የሚተዳደሩ ቢሆኑ ነው ሲሉም ታዛቢዎቹ ያክላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment