|
* ሟች – ሊደፍራቸው የመጣ ሳውዲ ወጣት
* ገዳይ – ሚስትና ቤቱን የተከላከለ ጎልማሳ
* ፍርድ ሰጭ – ከፍተኛው የሸሪአ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት
* እነ ሁሴን እንደገና አልተወለዱ ይሆን ?
ልክ የዛሬ 3 ዓመት ገደማ ሳውዲ አረቢያ ጅዳ “ሀበሾች ሳውዲ ገደሉ!” ተባለ ፣ መረጃውን የሰማሁት እኔም በእስር ላይ እያለሁ ነበር ። እንዴት ገደሉ ብየ ስጠይቅ ቤታቸውን ሊዘርፉና የሀበሻውን አባወራ ቤት ሊዘርፉ የገቡ ሳውዲ ወጣቶች ሴቶችን ሊደፍሩ በተነሳ አምባጓሮ መሆኑን በደፈናው ሰማሁ ። ከዚያም የቀረውን ተባራሪ የእስር ቤት መረጃ የማጣራበት መንገዱ ዝግ በሆነበት የጨለማ ወቅት ገደሉ የተባሉት ወደሚታጎሩበትና እኔ ወዳለሁበት ወህኒ እስኪመጡ የታሳሪውን ተባራሪ የማያጠግብ መረጃ ሳነፈንፍና ስኮመኩም ከረምኩ ። ከሶስት ወር በኋላ እኔ ከወህኒ እስክወጣ ወደ ማዕከላዊው የብሪማን እስር ቤት ሳይመጡ ቀሩ ፣ እኔም ጉዳይ ተጣርቶ ለእስር ወጣሁ …
ከእስር ከወጣሁ በኋላ ጉዳዩን ከገዳዮች አንደበት የመስማት እድሉ ገጠመኝ ” ከንጋቱ ላይ የኢድ በዓልን ልናከብር ስንዘገጃጅ ቤታችን ተንኳኳ ፣ ማነው ? ስል ፖሊሶች ነን አሉኝ ፣ ከፈትኩላቸው ። ግብተው ሴትና ወንድ ብለው ለያይተው አስቀመጡን ፣ ዘረፋ ጀመሩ ፣ ዝም አልን ፣ ቆዩና ሴቶቻችን ለመድፈር ሲሞክሩ የባለቤቴን ጩኸት ሰማሁ ፣ ዘልዬ ከተዘጋው ክፍል ወጣሁና ከወጣቶች ጋር ግብግብ ያዝን ፣ …ሟች ሳውዲ ስለት ይዞ ሊወጋኝ ሲሰነዝር የያዘውን ስለት ቀኝቸ ደረቱ ላይ ወጋሁትና ከቤቴ በር ገፍቸ አስወጣሁት ፣ ጓደኞቹ ተረባርበው ወሰዱት ፣ ፖሊስ ጠርተው ነበርና በፖሊስ ተከበን ተያዝን …ሚስቴን ሊደፍር ስከላከል ብወጋውም ይሞታል አላልኩም ነበር ፣ መሞቱን ሰማሁ ፣ አዘንኩ …” ይህን ምስክርነት የሰጠኝ የወንጀሉ ተጠያቂ ገዳይ ወንድም ሁሴን ሃሰን ነበር ! ታዲያ ያኔ በሞት ፍርደኞች መካከል የጨለማ ህይወትን ሲገፋ በነበረበት በጭንቋ ሰአት ሆን ብየ ነፍስ አላጠፋሁምና ስለፍርህ ድምጻችን አሰማልን ብሎ ተማጽኖኝ ነበር !
ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት የወንደም ሁሴንን ወንድምና የሁለት ጓደኞቹን የፍርድ ሂደት በቅርብ ተከታትተዋለሁ ፣ መረጃም በሰፊው አቀርብበት ነበር ። ሳውዲ መተዳደሪያ ባደባደረጋቸው የሸሪአው ህግ ” የገደለ ይገድላል” ቢባልም እንኳ የራሱ ስርአትና ደንብ ስለመኖሩ ይህ ውሳኔ ማሳያ ይመስለኛል ፣ ግፍ ሲፈጸምበት ራሱን ሲል ገደለ ትበሎ ይገደል እንደማይባል ትልቅ ማሳያ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በስራ ላይ ውሎ በእኛ ዜጎች ላይ ስላየሁት ደስ ብሎኛል ። ለዜጎች መብት የምናስብ ከሆነም ይህ አስተማሪ ነው ።
የደስታየ ምንጩና ተወካዮቻችን የምመክረው !
=============================
የሳውዲ ህግ አያሰራንም ከሚለው ተራ ቱማታ መውጣት ከቻልን ብዙዎችን መታደግ እንደምንችል ምልክት ነው ። ይህን እውነት ተከትለን በህግ አግባብ ፍትህ ማግኘት ስላለባቸው የሞት ፍርደኞች መብት ማስከበር ዙሪያ ተወካዮቻችን እንዳለባቸው ጠቋሚ ነው ።
እንደ ቀደሙት አመታት በየስብስባው ” የሳውዲ ህግ ለመብት ጥበቃው አይመችም ” የሚል ስንካላ ምክንያት ከተወካዮቻችን ሲቀርብ መስማት አንሻም ። በተለይ በአረብ ሃገራት ያሉ የመንግሰት ተወካዮቻችን ከዚህ ፍርድ ተነስተው ምን እየሰራን ነው ብለው ራሳቸውን መመርመር ይገባቸዋል ! ልብ ያለው ልብ ይበል ! የጎዳን የሳውዲ ህግ ሳይሆን ህጉን ተከትሎ መብታችን የሚያስከብር ሁነኛ የመንግሰት ተወካይ ነው ፣ ደረቅ እውነቱ ይህ ነው ። ዛሬ ከምንም በላይ የዘገየው ፍትህ ርትዕ እንዲህ ተከብሮ በማየት ደስ ብሎኛል ፣ ነገም ግፍ ተፈጽሞባቸው የታሰሩት ዜጎቻችን ነጻ የሚወጡበት ተስፋ እንዳለ በሚያነላክተው የፍርድ ውሳኔ እርካታ ተስምቶኛል ፣ ተደስቻለሁ !
ሁሉንም በወጉ ከነጻ ከተፈቱት ከእነ ሁሴን ጋር ቁጭ ብለን እናዎጋለን ፣ ደስታቸውን እንጋራለን ፣ የሞት ፍርደኞችን ህይወት ያለ ተስፋ የሚገፋበትን የጨለማውን የእስር ቤት የአመታት ውሎ አዳር በጨረፍታ ማውጋታችን አይቀርም ! በእነ ሁሴን ዙሪያ መረጃ ስንለዋወጥ ትብብራችሁ ላልተለየኝ ፣ በጸሎት ለረዳችኋቸው ሁሉ እኔም እነሆ Mission Accomplished እያልኩ በደስታ ምስጋናዬን አቀርባለሁ !
በዝርዝር እስክመለስ ወንድም ሁሴንና ጓደኛ ፣ ቤተሰቦቹ እንኳን ደስ አላችሁ ፣ እንኳን ደስ አለን !
ዛሬም ዜጎቻችን በደል ደርሶባቸው በየወህኒው ይገኛሉ ፣ ስለተበደሉት ድምጻችን እናሰማ !
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓም
No comments:
Post a Comment