Monday, March 20, 2017

አደጋው ከመከሰቱ ቀደም ብሎ በአካባቢው የተሰማው የፍንዳታ ድምጽ፣ ከአደጋው በኋላ እየተደረገ ስላለው እርዳታ….. እና ሌሎች በጆሲ ኢን ዘ ሀውስ




ከይድነቃቸው ከበደ
“ኢትዮጵያዊነት መልካምነት!”
(ይድነቃቸው ከበደ)
“እኔ ትናንት መኖር የምፈልገውን ዓይነት ህይወት ነው ዛሬ የምኖረው፡፡ በአብዛኛው እኛ አገር እውቅናን ተጠቅሞ ወገንን መደገፍ አልተለመደም፡፡ ያ ሁልጊዜ ያናድደኝ ነበር፡፡ አርአያህ (ሮል ሞዴልህ) ማነው ስባል እንኳን አንጀሊና ጆሊንና ብራድ ፒትን ነው የምጠራው፡፡እነሱ ለኛ ሩቅ ናቸው፤ሆኖም ግን እውቅናቸውን ተጠቅመው የተቸገረ ይረዳሉ፡፡ የኔ እውቅናም እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እንጂ “አየኸው አየሽው” የሚል መጠቋቆሚያ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ቴሌቪዥን ላይ መስራት በጣም ከባድ ነው፡፡ ቤተሰብ አንድ ላይ ተቀምጦ የሚያየው ፕሮግራም ነው፡፡ ኃላፊነቱ ከባድ ነው ግን መሸከም መቻል አለለብኝ፡፡ ማህበረሰቡንና ትውልዱን የሚቀርፁ፣ ክፍተቶችን የሚደፍኑ ስራዎች መስራት አለብኝ ፡፡”
– ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ( ጆሲ ) ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ከ3 ዓመት በፊት በተደረገለት ቃለ መጠይቅ የሰጠው ምላሽ ነበር።

“ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ” ወይም ዮሴፍ ገብሬ፤ በሚያዘጋጀው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ፣ በተለያየ የሙይ ዘርፍ እውቅና ያተረፉ ግለሰቦችን፣ በፕሮግራሙ ዝግጅቱ ላይ እያቀረበ ፣ ለተመልካቾች በተለየ አቀራረብ አዝናኝ እና አሰተማሪ ዝግጅቶችን
ሲያቀርብ ቆይቷል ፤ አሁንም በዚህ መልካም ተግባሩ እየቀጠለ ይገኛል።ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ( ጆሲ ) ከመጀመሪያ ጀምሮ እስካሁን በሚያከናውናቸው ሥራ ፣ የተግባር መገለጫ በሆነው የበጎ ሰው ሥራው ፣ የተለያየ ነቀፌታና ትችት በተለያየ መንገድ ሲቀርብብት ነበረ፤
በተለይ ሰወችን ለመርዳት እና እንዲረዱ ለማስተባበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ፣የራሱን ማንነት ለመገንባት በሰዎች ችግር ጥረት የሚያደርግ ነው። በማለት አንዳንዶቹ ትችታቸው በተለያየ መንግድና በተለያየ ወቅት ሲገልጾ ተስተውሏል።

ይሁን እንጂ፣ ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ( ጆሲ ) የሚቀርብበትን ትችት እና ነቀፌታ ከሥራው ወደኋላ አላስቀረውም ። እንዳሁም ጄቲቪ ኢትዮጵያ (JTV Ethiopia) የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ በማቋቋም የሚዲያ ኢንዱስትሪን ለመቀላቀል ችሏል። ጄቲቪ ኢትዮጵያ የ24 ሰዓት ስርጭቱን የሚያቀርብ ሲሆን ፣ጄቲቪ ኢትዮጵያ ፤ኢትዩጵያዊነት መልካምነት! በሚል መርህ በቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የተለያዩ አዝናኝ እና አሰተማሪ ዝግጅቶች እየተላለፉበት ይገኛል ። በህብረተሰብ ዘንድ አሁን ላይ ከሚታዩ የቴሌቪዥን ጣቢያ መካከል ፣ ተቀባይነት ካገኙ ውስን የመዝናኛ እና የመረጃ የቴሌቪን ጣቢያዎች አንዱ ለመሆኑ በቅቷል ።

በተለይ ፣ማንኛውም ሰው በማህበራዊ ህይወቱ ውስጥ ሲኖር መረዳዳትንና መተባባርን ባህል ማድረግ የዘወትር ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ የሚታመን ነው። በዚህም መሠረት ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ( ጆሲ ) ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ በሚሰኘው የቴሌቪዥን ዝግጅት ላይ ፣ ቀድሞ
ተዋቂ የነበሩ አሁን ላይ የተረሱ፣ አድናቆትና ክብር የነበራቸው ዝነኛ ሰዎች በበሽታ ታመው የሚጠይቃቸው ጠፍቶ በአልጋ ላይ የተኙ፣ ትላንት አንቱታን ያተረፉ ዛሬ በየመንገዱ ላይ ወድቀው የሚገኙ፣ አባትና እናታቸው ለአገርና ለህዝብ ክብር ተዋድቀው የእነሱ ልጆች ሜዳ
ላይ የቀሩ ፤ እና የመሳሰሉ ምን ይሄ ብቻ ፣እጅግ በጣም አሳዛኝ ታሪኮችን፣ በማንሳት ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ ፤ ሰዎችን መውደድ እና መርዳት የሰው ልጅ መልካም ስነምግባር መሆኑን በሥራና በተግባር የተረጋገጠበት ምርጥ የቴሌቪዥን ዝግጅት ነው።

በተለይ እንድ አገር ያዘንባቸው በጣም ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። አብዛኞቹ ከመንግስት የአስተዳደር ብልሹነት የመነጩ ስለ-መሆናቸው ለማንም ግልጽ ነው። እርግጥ ነው፣ በስልጣን ላይ ያለው የአገዛዝ ሥርዓት ይሄን እውነት ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለም። ይሁን እንጂ በንሮ ውድነት እና በችግር ምክንያት ብቻ ከአገራቸው የተሰደዱ ወገኖቻችን ፣ በሊቢያ በአሸባሪው አይኤስአይ ኤስ አንገታቸውን የተቀሉ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ሞት መቼም የማይረሳ ሐዘናችን ነው። በዚህም ጊዜ ቢሆን ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ( ጆሲ ) በሐዘንተኞች ቤት ቀድሞ በመገኘት፤ ለሀዘንተኞች እጅ አስታጥቦ በአገራችን በህል መሠረት እራት አቅርቦ አብሮ በመብላት ፣ ለሀዘንተኞች መፅናናት ይሆን ዘንድ እስፖንሰር(ደጋፊ) አፈላልጎ 142.000 (አንድ መቶ አርባ ሁለት ሺህ) ብር አበርክቶ ፣የሟች ቤተሰቦች በዘለቄታ የሚረዱበት እንዲሁም ስለ ደረሰው አደጋ እና የሟች ቤተሰቦች ሁኔታ ሰፊ የፕሮግራም ሽፋን በመስጠት ወገንተኝነቱን አሳይቷል።

አሁን ደግሞ ፣በመንግስት ቸልተኝነት እና ግዴለሽነት ምክንያት ብቻ !በአንድ ቀን ምሽት ከ120 የማያንሱ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን የቆሻሻ ክምር ተንዶባቸው ህይወታቸውን ሊያጡ ችለዋል። ለነዚህ ንጹሃን ዜጎቻችን ለህይወታቸው ማጣት ተጠያቂው በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ብቻ ነው። የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ የዚህን ያህል ሰው መሞት በአለማችን ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋትም ጭምር ነው። ይሄ አይነቱ አሳዛኝ ታሪካችን ፣ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲሁም ሌሎቹ ከዜና ሽፍን እና በሙዚቃ መሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ከማሰማት የዘለለ አንድም ነገር ሲያደርጉ አልታየም።ሆኖም ግን ሁሉም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ካደረጉት ነገር በተጨማሪ፣ ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ( ጆሲ )፣ ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ በተሰኘው ፕሮግራም ላይ እንደተለመደው “ኢትዮጵያዊነት መልካምንት!” የሚለውን መርህ አንግቦ ፣ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመገኘት ፣ የብዙ ተመልካቾችን ቀልብ የሳበ አሳዛኝ ፕሮግራም በጆሲ ኢን ዘ ሀውስ ተላልፉ ለመመልከት ችለናል።

ይህን ፕሮግራም ፣ በትክክል ቆሼ ላይ የደረሰውን አደጋ የሚቃኝ ነው። በተለይ የሟች ቤተሰቦች ስለ-ሟች በቤተሰቦቻቸው የኖሩ ሁኔታ ፣ የት/ት ደረጃ ፣ በሥራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ፣በቤተሰብና በወዳጅ ዘመድ የነበራቸው ተቀባይነት፣ አደጋው በሚደርስበት ወቅት የነበረው ሁኔታ፣ አንዱ ሌላውን ለማትረፍ ያደርግ የነበረው ጥረት፣ አደጋው ከመከሰቱ ቀደም ብሎ በአካባቢው የተሰማው የፍንዳታ ድምጽ በተመለከተ ፣ ከአደጋው በኋላ እየተደረገ ስላለው እርዳታ ….. እና ሌሎች ጉዳዬች በጆሲ ኢን ዘ ሀውስ
ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ ሽፍ ተሰጥቷቸዋል ። ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ( ጆሲ ) ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሌሎችን በማስተባበር ለተጎጂ ቤተሰቦች መጠነኛ እርዳታ እንዲደርሳቸው የበኩሉን አሰተዋአዖኦ አድርጓል ። አዎ ! “ኢትዮጵያዊነት
መልካምነት! ” ማለት ለእኔ ይሄ ነው። እግዚአብሔር ሁሌም መልካም የሆነውን ነገር ያመላክተን ፣ ህይወታቸውን ላጡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር ፤ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመድ መጸናናት ፈጣሪ ይስጥልን ፤ አሜን!!!

No comments:

Post a Comment