Wednesday, March 29, 2017

የአባይ ጸሐዬ መስሪያ ቤት ጥናት እጅጉን አስቂኝ መሆኑ ተገለጸ




ፈላጭ ቆራጭ ከሆኑት የህወሓት ባለስልጣናት መካከል አንዱ በሆኑት አቶ አባይ ጸሐዬ ዋና ዳይሬክተርነት የሚመራው የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ‹‹አካሔድኩት›› ባለው ጥናት ላይ፣ ‹‹የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነት ዋነኛ ማነቆ ነው፡፡›› ሲል አስቂኝ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞከልራሲዊ ስርዓት እንዳይሰፍን ማነቆ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነት መሆኑን የገለጸው የአቶ አባይ ጸሐዬ ተቋም፣ ራሱን ከችግር ፈጣሪነት ማንጻቱም ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በስርዓቱ ውስጥ የአዛዥነት ስፍራውን የተቆናጠጠው ህወሓት፣ በወህኒ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣብያዎች እና በመሰል አስፈጻሚ አካላት ውስጥ ጣልቃ በመግባት የፈለገውን ዓይነት ውሳኔ እንደሚወስን ይታወቃል፡፡
ከጄነራል እስከ ገራፊ ድረስ ህወሓቶች በተቆጣጠሩት ስርዓት ውስጥ ጥናት አካሔድኩ ብሎ የተሳለቀው የአቶ አባይ ጸሐዬ ተቋም፣ ጣቱን ወደ ሌሎች በመቀሰር በሀገሪቱ ላይ እና በህዝቧ ላይ ከተፈጸሙት በደሎች ራሱን ለማንጻት መጣሩ እንዳስገረማቸው ጥናቱን የተከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡ የሀገሪቱ ቁጥር አንድ ችግር ፈጣሪ የሆኑት አቶ አባይ ጸሐዬ፣ መልሰው ራሳቸው የመፍትሔ ጥናት አጥኚ በሆኑበት ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ለውጥ ሊመጣ እንደማይችልም ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ እንደ ህወሓት በአስፈጻሚ አካላት ስራ ጣልቃ የሚገባ እንደሌለ የሚገልጹት እነዚሁ ታዛቢዎች፣ የህወሓት አጃቢ የሆኑት ብአዴን እና ኦህዴድ ደግሞ ለህወሓት ጣልቃ ገብነት መሳሪያ መሆናቸውን ታዛቢዎቹ ያክላሉ፡፡
‹‹ምክር ቤቶች፣ መገናኛ ብዙኃን እና የሕዝብ ማኅበራት መብቶቻቸውን በተቀመጡ ህጎችና በህገ-መንግሥቱ መሰረት የመጠየቅና ፊት ለፊት መጋፈጥ ላይ ክፍተቶች አሉባቸው፡፡›› ያሉት አቶ አባይ ጸሐዬ፣ የተጠቀሱት አካላትም ሆኑ ሌላው ማኅበረሰብ መንግስትን ፊት ለፊት ያለመጋፈጥ ችግር እንደሚስተዋልበት ተናግረዋል፡፡ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች መንግስትን ፊት ለፊት የተጋፈጡ ተቃዋሚዎች፣ ግንባራቸውን በጥይት ተመትተው በተገደሉበት ሀገር፣ አቶ አባይ እና ጥናታቸው አስመሳይነታቸውን ከማሳበቅ በቀር ፋይዳ እንደሌላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡ ጋዜጠኞች መንግስትን ለምን ተቻችሁ ተብለው 18 ዓመት በሚፈረድባቸው ሀገር ውስጥ፣ ስለ መገናኛ ብዙኃን ደካማነትም አቶ አባይ ተናግረዋል፡፡ ነጻ ሚዲያ በሌለበት ሀገር ውስጥ ሚዲያዎችን የወቀሰው የአቶ አባይ ጥናት አስቂኝ ሆኗል፡፡
ከህዝባዊ ተቃውሞ ወዲህ ሁሉ ነገሩ የተመሳቀለበት ህወሓት፣ የተበላሸውን ለማስተካከል ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሆኖም ነገሮች እንደቀደመው ጊዜ ሊሔዱለት አለመቻላቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በጥናት እና በመሰል ጉዳዮች ሌሎችን በመውቀስ ራሱን ለማዳን ጥረት ሲያደርግ የሚስተዋለው ህወሓት፣ እንደለመደው የተወሰኑ ባለስልጣናትን ዞር በማድረግ ቆዳውን ገልብጦ ለመምጣት የሞከረባቸው አጋጣሚዎች ብዙ መሆናቸውን የሚገልጹ ወገኖች፣ ዘንድሮው የተጋፈጠው ተቃውሞ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደከበደው እነዚሁ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡

No comments:

Post a Comment