ቢቢኤን እንደዘገበው በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት ውስጥ እጃቸው ያለበት የመንግስት አካላት ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡ መደበኛ ጉባኤውን ሲያካሂድ የቆየው የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ)፣ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ አሁንም የቀጠለውን ግጭት አስመልክቶ በጉባኤው ላይ ሲወያይ ቆይቷል፡፡ ጨፌው ግጭቱን ለመፍታት መፍትሔ ነው ያላቸውን የተለያዩ ሃሳቦች ያቀረበ ሲሆን፣ አንዱም በግጭቱ ላይ እጃቸው ያለበትን የመንግስት አካላት ለፍርድ ማቅረብ ነው ብሏል፡፡ ምክር ቤቱ ባካሄደው ጉባዔ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ ከነበሩ ጉዳዮች የላቀ ትኩረት የተሰጠው፣ ላለፉት አራት ወራት የቀጠለው የወሰን ግጭት መሆኑ ታውቋል፡፡
በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይም ጥቃቱን በመሰንዘር የሰው ሕይወት የማጥፋትና ንብረት የማቃጠል፣ ነዋሪዎችን የማፈናቀልና የሶማሌ ክልል ባንዲራን የመትከል አዝማሚያ እንደታየ የተለያዩ የጨፌው አባላት በጉባኤው ላይ አንስተው ተወያይተዋል፡፡ ግጭቱ የተነሳው ከሶማሊያ የሚነሱ ታጣቂዎች በአምስት የኦሮሚያ አዋሳኝ ዞኖች እና ወረዳዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት መሆኑም በጉባኤው ተጠቁሟል፡፡ ጥቃቱ እየተሰነዘረ ያለው በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እና በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች እንዲሁም በጉጂ ዞን ሲሆን፣ በዚህ ግጭትም በርከታ ሰዎች ማለቃቸው ተመልክቷል፡፡
ችግሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በሰላማዊና የአካባቢውን የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት በዘላቂነት ባስከበረ መልኩ መፈታት እንዳለበት የገለጸው የኦሮሚያ ምክር ቤት፣ የኦሮሞ ሕዝብን ደኅንነት መጠበቅ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል በሕዝቡ ሙሉ ተሳትፎ ተደግፎ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሚያስችል ሁኔታ ተጠናክሮ ግዴታውን እንዲወጣ ማድረግ አለበት ሲልም ጨፌው ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የሁለቱ ክልሎችን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት በ1997 በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት ለችግሩ እልባት መሰጠት አንዳለበትም ተወስኗል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ግጭት በረድ ጋል እያለም ቢሆን መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment