”ህዝባዊ እንቢተኝነት በየትኛውም ሀገር እንደ ሽብር ተቆጥሮ አየውቅም” ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
”መንግስት ባልታጠቁ ዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ የሀይል እርምጃ ሲውስድ ዜጎች ሳይታጠቁ እራሳቸውን ለመከላከል የወሰዱት እርምጃ ሽብር አይደለም” ዶ/ር መረራ ጉዲና
(በሰማያዊ ብሄራዊ ሸንጎ የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ)
ችሎቱ ለዛሬ የተቀጠረው አቶ ዬናታን ተስፋዬ በቀረበበት የሽብር ክስ ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና ዶ/ር መረራ ጉዲናን ለመስማት ሲሆን ሁለቱም የመከላከያ ምስክሮች ቅርበው የስላማዊ ትግል መርህዎችና አቶ ዬናታን ተስፋዬ በተከሰሰበት በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ትቃውሞ በተመለከተ ቃላቸውን ሰጠዋል። በመጀመርያ ምስክርነታቸውን የሰጡት ዶ/ር መረራ ጉዲና ህዳር 2008 ዓ/ም በኦሮምያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ ለችሎቱ ሲያስረዱ ህዝቡ ወደ አደባባይ የወጣው በፍትህና በመልካም አስተዳደር እጦት ነው። ህዝቡ ለረጅም አመታት በግፍ ላይ የነበረና የአካባቢው አስተዳዳሪዎች በአግባቡ ስላላስተዳደሯቸው የተነሳ ተቃውሞ ነው። ህዝቡ ባዶ እጁን ለተቃውሞ መውጣቱንና የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ያልተመጣጠነ እርምጃ መውሰዳቸው ሁኔታውን ያባባሰው ይህ የሀይል እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም እኔ ሶስት መንግስታት አይቻለሁ፤ የሚነሱባቸው ጥያቄዎች ሰላማዊና በህገመንግስቱ የተፈቀዱ ናቸው። ኢትዬጵያ ውስጥ ግን የህዝብን ጥያቄ ከሽብርተኝነት ጋር ማያያዝ አለ። ነገር ግን የተጠቀ አመፅ አልነበረም። የታጠቀ ሀይል እንኳ መንግስትን ለመጣል ቢሞክር፤ ሰላማዊ ዜጎች እስካልነካ ድረስ ሽብርተኝነት አይደለም በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል።
ከዚህ እንቅስቃሴ ጀርባ ማን አለ? ተብለው በአቶ ዬናታን ጠበቃ የተጠየቁ ሲሆን አለን የሚሉ ድርጅቶች እንዳሉና እውነታው ግን ገንፍሎ የወጣ የህዝብ ብሶት መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል።
አምስተኛ የመከላከያ ምስክር ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሰላማዊ ትግል መርሆች ላይ ማብራርያ የሰጠ ሲሆን ሰላማዊ ትግል ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጋር የሚደረግ ትግልና ከአምባገነን ስርዓት ጋር የሚደረግ ትግል እንዳለ ለችሎቱ አስረድተዋል። በዲሞክራሲያዊ ስርዓት በምርጫ የሚደረግ ሲሆን፤ እንደ ኢትዬጵያ አይነት በአምባገነን ስርዓት ባለበት የሚደረግ ትግል ደግሞ ህዝባዊ እምቢተኝነትን (civil disobedienc) ያጠቃልላል።
የትጥቅ ትግል የራሱ የሆነ አለም አቀፍ ህግ ያለው መሆኑንና ሽብር ደግሞ ምንም አይነት የጦርነት ህግ የሌለው በተመቸው መንገድ ማንኛውንም ተቋማትና ህዝብን ኢላማ ያደረገ ነው። ህዝባዊ እምቢተኝነት(civil disobedience) የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር የሚደረግ ትግል እንደሆነና ያልተፈቀዱ ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ማድረግን እንዳሚያካትት የሲቪል መብቶች ተሟጋች አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ህንድን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት የታገሉት ማህተመ ጋንዲ በይፋ ህዝባቸውን ሲያስተምሩ እንደነበር በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የአቶ ዬናታን ድርጊትም ሀሳብን በነፃነት መግለፅ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ በህዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ስልት እንደሚካተት ለችሎቱ አስረድተዋል። ህዝባዊ እንቢተኝነት በየትኛውም ሀገር እንደ ሽብር ተቆጥሮ አያውቅም ብለዋል።
ችሎቱም የመከላከያ ምስክሮችን ከአዳመጠ በሁዋላ ተጨማሪ የመከላከያ የሰነድ ማስረጃዎችን ለመቀበል ለመጋቢት 27/2009 ዓ/ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
No comments:
Post a Comment