Monday, March 27, 2017

ተስፋ አንቆርጥም ……. ትግሉ ይቀጥላል!!! – ኄኖክ የሺጥላ

   
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው የነፃነት ትግል ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሚመስል ፥ ተስፋ ለማስቆረጥ የሚከጅለው አይነት ነው። ግን ተስፋ ብቆርጥ ምን ላይ ነው ተስፋ የምቆርጠው? አዎ ተስፋ ብንቆርጥ የልጆቻን ቀዳሚ ማንነት ላይ ነው ተስፋ የምቆርጠው ፥ ተስፋ ብንቆርጥ በየ ጎዳናው ላይ የተበተኑ ፥ ወላጆቻቸው ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ የተሰው ፥ እግር እና እጃቸውን አጥተው በክራንች ሲለምኑ ኖረው በየ ጠላ ቤቱ በራፍ ላይ እንደ አንድ በደለኛ ተደፍተው የቀሩ ፥ ቀና ማለት እንደተመኙ እንዳቀረቀሩ ያለፉትን ፥ የነፃነት ቀን ወጥቶ በእኩልነት እንደ ማንኛውም ዜጋ በዚያች አገር እኩል ሆኖ መኖር ሲናፍቁ የተመኟትን ቀን ሳያዩ ያሸለቡት እናት ፥ አባት ፥ እህት እና ወንድሞች የትጋት እና የትስፋ ህይወት ላይ ነው ተስፋ የምንቆርጠው።
እርግጥ የዘር ፖለቲካው እሰጣ ገባ ፥ ድሉ የኔ ነው ንትርክ ፥ ምኑም ሳይያዝ የይገባኛል እና የኛ ነን ደባው ፥ የማግለሉ እና የመገለሉ ፥ የሸሩ እና የሴራው ፥ የስውር ሰይፉ እና በንፁሃን ደም ገንዘብ እንደ የኔ ቢጤ የመቅፈፉ ጉዳይ ሁሉ ፥ ተስፋ ለማስቆረጥ ከበቂ በላይ ነው። ግን ግን ተስፋ ከቆረጥን በኋላስ ? አለመግባባት ባርነትን ለመቀበል ምክንያት ይሆናል ? ዛሬ ባለ ድል አለመሆን የዘላለም መረገጥ ላይ እራስን በአወንታ ለመነቅነቅ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል? ተስፋ እንቁረጥ ግን ተስፋ ከቆረጥን በኋላስ ? የምንሞትለት ፥ የሚሞትልን ፥ ስቃዩን የምንካፈለው እና ስቃያችንን የሚካፈለን ህዝብ የሌለን ፥ ስሜት አልባ ፥ ውጥን አልባ ፥ ትልም አልባ ሆኖ መኖር ከተስፋ መቁረጡ የባሰ አይጎመዝዝም ወይ ? ዝምታ ቃና አለው ወይ ? የጨቋኞች ጉልበት ፥ የሚጨቁኑበት መሳሪያቸው ሳይሆን ፥ ሲጨቁኑ ጭቆናውን እንዳላየ ሆኖ የሚያልፈው ህዝብ አይደለም ወይ ? ተስፋ እንቁረጥ ምንም አይደለም ፥ ግን ተስፋ የነጠፈ ህይወት ለመኖር ያሳሳል ወይ ? በባህር ተጭነው ለባርነት የመጡት አፍሪቃውያን መጀመሪያ የተነጠቁት እኮ ተስፋቸውን ነው ! ነገን ሊተልሙበት ፥እልፍ ዘመን አልፈው ራሳቸውን በልጅ ልጆቻቸው መነጥር ሊያዩ የሚችሉበትን ሰዋዊ ምህዳር ነበር እኮ የተቀሙት! ተስፋ ቆርጠን ሰው መሆን ይቻላል ወይ ? ወይስ ሰው ለመሆን የሚደረገው ትግል ከሞት ጋርም ቢሆን ሰው ለመሆን ነውና እጅጉን አይጣፍጥም ወይ ? ተስፋ መቁረጥ ማለት በራሳችን ህሊና ፥ እና በህሊናችን ፍርድ መታዘዝ እና መገዛት የማንችል እንስሶች ሆነን መኖር መምረጥ ማለት ነው !
«ከወይን ሃረግ ፍሬ ባይገኝ፥ በለስም ባታፈራ » እንዳለው እኛም ሩቅ ለሆነው ግን ተስፋ ለማያስቆርጠን የማንነት ትግል የተሰጠን ነን ! እኔ ተስፋ አልቆርጥም አንተስ ?
ኄኖክ የሺጥላ

No comments:

Post a Comment