(የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት) የ65 አመቱ መሬት መብት ተሟጋቹ ኦሞት አግዋ የቀረበባቸው የሽብር ክስ በህዳር 05/2009ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ተነስቶ ወደ መደበኛ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ ቁጥር 256/ሀ “ወታደሮችን፣ የሽምቅ ተዋጊዎችን፣ ሽፍቶችን መመልመል” ከተቀየረ በኋላ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተነፈገው የዋስትና መብታቸው በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን ጥር 10/2009ዓ.ም በዋለው ችሎት የ50ሺ ብር ዋስትና አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ ትእዛዝ ከሰጠ በኋላ ከእስር ውጪ ሆነው ክሳቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ ይታወሳል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ቀን መጋቢት 18/2009 በዋለው ችሎት የኦሞት አግዋን የተከሳሽነት ቃልና የመከላከያ ምስክሮች ሰምቷል።በዚህም መሰረት ተከሳሹ ለመከላከያ ምስክርነት 12 ሰዎችን ያስመዘገቡ ሲሆን በዛሬው እለት 5 የሰው ምስክሮች በችሎት ተገኝተው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ጠዋት በነበረው ምስክር የመስማት ሂደት በቅድሚያ የተከሳሽነት ቃላቸውን የሰጡት አቶ ኦሞት አግዋ በጋምቤላ ክልል ይኖሩ እንደነበረ፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረው አባታቸው በመሞቱ ምክንያት ወደ እርሻ ልማት ተሰማርተው እናታቸውንና ሌሎች የቤተሰብ አባላትን ያስተዳድሩ እንደነበረ፤ የመማር እድል ለማግኘት ብዙ እንደለፉ ትምህርታቸውንም ቀጥለው በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1976-1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ መፅሃፍ ቅዱስን ወደ አኝዋክ ቋንቋ እንደተረጎሙ፤ በኬንያ አገርም መንፈሳዊ ትምህርት ተከታትለው በ1986 ወደ አገራቸው እንደተመለሱ በቤተክርስትያን ትምህርት ላይ ይሰሩ እንደነበረ፤ በ1996 ዓ.ም በጋንቤላ ክልል በተነሳ የዘር ግጭት ወቅት “ጋንቤላ ሰላምና ልማት ትብብር ማህበር” በመመስረት በግጭቱ ወቅት ጫካ የገቡ ሰዎችን መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ በመሄድ አምጥተን በመልሶ ሟቋቋም እንዲሰማሩ እንዳረጉ ማህበሩም በመንግስት የሚደገፍ ማህበር እንደነበረ ተናግረዋል። አቶ ኦሞት ሲቀጥሉ ስዊዘርላንድ ከሚገኝ የክርስትያን ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር ተፃፅፈው ‘Food For All’ የሚባል ፕሮጀክት ቀርፀው ህብረተሰቡን ለመርዳት ሲነቀሳቀሱ እንደነበርና ለዚሁ ጉዳይ ከሲውዘርላንድ ተራዶ ድርጅት ጋር ለመምከር ወደ ኬንያ ሊሄዱ ሲል የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነ ከቀረበው ቄስ ሽብሩ ጋር አየር መንገድ ላይ ተይዘው ማእከላዊ እንዳስገቧቸው፤ ማእከላዊ በገቡበት ወቅት ለአንድ ወር ያክል ጨለማ ቤት ውስጥ እንደተቀመጡ፤ በማእከላዊ ወቅት በአሰቃቂ የምርመራ ሂደት ውስጥ እንዳለፉ ቃላቸው ያልሆነው የተፃፈ ወረቀት ላይ በፀያፍ ስድብና ማስፈራራት በግዳጅ እንዳስፈረሟቸው ከኮምፒውተር ተገኘ የተባለው ወረቀትም በለንደን አገር የሚገኝ አኝዋክ ሰርቫይቫል የሚባል የግብረሰናይ ድርጅት የሰራው ጥናት ነው እኔ የፃፍኩት አይደል፤ ፕሮጀክት ለመቅረፅ ብዙ ግብአቶች ስለምጠቀም ነው እሱም ኮምፒውተሬ ላይ ያረኩት፤ ለኔ ይሄ አይገባኝም መፅሃፍ ቅዱስን ከማስተማር ውጩ ሌላ አላውቅም፤ ህፃናት በሞረሌ ጦር ሲወድቁ ሳይ በጣም ነው የማዝነው ብለዋል። አቶ ኦሞት ቃላቸውን በሚሰጠበት ወቅት በተደጋጋሚ “ተበድያለሁ” ይሉ ነበር።
የተከሳሹን ቀል የሰማው ፍርድ ቤት ምስክር በእለቱ የተገኙትን አምስት ምስክሮች ቃለ-መሃላ እንዲፈፅሙ ካረጉ በኋላ ምን ጭብጥ ላይ እንደሚመሰክሩ በተከሳሽ ጠበቃ አማካኝነት መዝግበዋል።
በቅድሚያ የምስክርነት ቃላቸውን 1ኛ ምስክር በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 05 የሚኖሩት ኩሩ ኡሙድ ኡጅሉ የተባሉ ግለሰብ ናቸው። በ1996 ዓ.ም በጋምቤላ በተነሳው አመፅ ምክንያት በተነሳው ችግር ከተማዋን መልሶ ሰላማዊ ለማድረግ የአቶ ኦሞት አግዋ ሚና ምን እንደነበረ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። “በ96 ዓ.ም በክልል በተነሳው ግጭት ምክንያት ጫካ የገቡ ሰዎችን በመመለስና ወደ ልማት እንዲገቡ በማድረግ አቶ ኦሞት ከመንግስት ጋር በመሆን ትልቅ ስራ ሰርተዋል” በማለት የተናገሩ ሲሆን በወቅቱ በተቋቋመው የሰላም ቡድን ውስጥ አቶ ኦሞት ሰብሳቢ እንደሆኑና ይህም ቡድን በመንግስት የተቋቋመ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመቀጠል ሊሰሙ የነበሩት ምስክርች አማርኛ ቋንቋ ስለማይችሉ አስተርጓሚ ይዘን መጥተናል ያሉት የተከሳሹ ጠበቃ በአቃቤ ህግ ተቃውሞ ገጥሞታል። ለመተርጎም የመጡት ግለሰብ ተከሳሹ የተከሳሽነት ቃላቸውን ሲሰጡ የሰሙ ስለሆነ ትርጉም ሊያዛቡብኝ ይችላሉ በማለቱና ቅሬታው በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት በማግኘቱ አስተርጓሚ ከተገኘ ከሰአት ምስክር የማሰማት ሂደቱ እንደሚቀጥል በማዘዝ ተጠናቋል።
ከሰአት በነበረው ሂደት ተከሳሹ እራሳቸው አስተርጓሚ ያዘው የመጡ ሲሆን አቃቤ ህግም አንደማይቃወም በመግለፁ ኦቡላ ኦባንግ የተባሉት ተርጓሚ ቃለማህላ ፈፅመው ምስክር የመስማቱ ሂደት ቀጥሏል።
የተከሳሽ 2ኛ ምስክር የሆኑት በጋምቤላ ከተማ 05 የሚኖሩት ቄስ ደኩ ኦቦን ከኦሞት አግዋ ጋር ጋምቤላ የሚገኘው መካነ እየሱስ ቤተክርስትያን አብረው ያገለግሉ እንደነበረ፤ በ96 ዓ.ም በተነሳው እረብሻ ላይ በመንግስት በተቋቋመው የሰላም ቡድን ውስጥ እሳቸውን ጨምሮ 5 ሰዎች እነዳሉበት ኦሞት ደግሞ የቡድኑ ሰብሳቢ እንደሆነ፤ በክልል ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት አቶ ኦሞት ብዙ እንደሰሩ በችሎት ፊት መስክረዋል።
የተከሳሽ ቀጣይ ምስክር የሆኑት ኦሞድ ኪፒዮ በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ ስለሚመሰክሩ በተከሳሹ ጥያቄ መሰረት ሳይመሰክሩ ቀርተዋል።
3ኛ ምስክር ሆነው የቀረቡት ፕሌማን ወድ የክልሉ ልዩ ሀይል አባል ሲሆኑ በጋንቤላ ከተማ ቀበሌ 05 ኗሪ ናቸው። እኚህ ምስክር በኦሞት አግዋ ተመልምለዋል በሚል የክሱ ወረቀት ላይ ስማቸው የሰፈረ ሲሆን በተመሳሳይ ክስ ተከሰውም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ከሽብር ክስ ነፃ ወጥተዋል። በአቶ ኦሞት አግዋ የክስ ወረቀት ላይ የምስክሩ ስም ተጠቅሶ በኦሞት አግዋ ለጋህነን የተመለመለ ቢልም ግለሰቡ ተመለመለ በተባለበት ወቅት በእስር ላይ ይገኝ እንደነበር ተናግሯል። “እስር ቤት ሆኜ እንዴት ይመለምለኛል” ያለው ምስክሩ ከ2002 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ በእስር ላይ ይገኝ እንደነበረ ከዛም በኋላ ከአመት በፊት ደግሞ የጋህነን አባል ነህ በሚል በሽብር ተከሶ በዚሁ ፍርድ ቤት ነፃ እንደተባለ መስክሯል።
በእለቱ የቀረቡት የመጨረሻ ምስክር 4ኛ ምስክር ወ/ሮ አጅሎ ኪዮ እሳቸው በሚኖሩበት በአኝዋ ዞን ኤዮ ቀበሌ አቶ ኦሞት ከግብርና ባለሙያዎች ጋር ሁሌም ይመጡ እንደነበረ ግብርናን በተመለከተ ትምህርትም ከእሳቸው እንዳገኙ ተናግረዋል። በአቶ ኦሞት ምክንያት እሳቸውንም ጨምሮ ብዙ ሴቶች ተጠቃሚ እንደሆኑ፤ አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ኦሞት ባስተማረኝ የግብርና ትምህርት ምክንያት ሽልማት እንደወሰዱ ገልፅል። ምስክሯ አቶ ኦሞት ከግብርና ሰዎች ጋር ሲመጡ በማን መኪና ነው የሚመጡት ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ በመንግስት መኪና እንደሚመጡ ተናግረዋል።
የእለቱ ምስክር የማሰማት ሂደት በዚሁ የተጠናቀቀ ሲሆን ማረሚያ ቤት የሚገኙ በመከላከያ ምስክርነት የተመዘገቡ 4 ግለሰቦች (የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳን ኦኬሎ አኳይን ጨምሮ) በሚቀጥለው ቀጠሮ እንዲመጡ ትእዛዝ እንዲጻፍና ቀሪ 3 ምስክሮች ከውጪ ይዘው እንዲመጡ ለሰኔ 05/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት
No comments:
Post a Comment