Wednesday, March 15, 2017

ሀገርና ወገን ለማዳን አዉሬዉን ማስራብ



ሺፈራዉ አበበ
የትዉልድ አገራችን ኢትዮጵያ በጣም አሳሳቢ በሆነ አገራዊ ቀዉስ ዉስጥ ትገኛለች።
ባንድ በኩል ህገ-መንግስታዊና ሰብአዊ መብቶቼ ይከበሩልኝ ብሎ በመነሳቱ፣ ለግድያ፣ ለድብደባ፣ለእስራትና ለስደት የተጋለጠ ሰፊ ህዝብ አለ። ቁጣዉን ወደአደባባይ ይዞ ከወጣዉ ወይም ጫካ ከገባዉ ህዝብ በተጨማሪ ብሶቱንና ቁስለቱን በሆዱ አምቆ ይዞ፣ ቀን የሚቆጥር፣ ቀን የሚጠብቅ፣ አእላፍ ህዝብ አለ።
በተቃራኒ ጎን ያገሪቱን የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የመንግስት ተቋማትና፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ አዉታሮች የሚቆጣጠር፣ ባብዛኛዉ ክንድ ጎሳ ብቻ የመጡ እፍኝ የማይሞሉ ግለስቦች እንደግል ድርጅታቸዉ የሚጠቀሙበት የወያኔ-ህወሃት አገዛዝ አለ።

ይህ አገዛዝ፣ ከህዝባዊ መሰረቱ መጥበብና ከገዦቹ የአስተሳሰብ ደካማነትና ራስ ወዳድነት የተነሳ ባገሪቱ ውስጥ ለሚነሱ ፖለተካዊ ችግሮችና ተቃዉሞዎች የሚሰጠዉ ምላሽ ከድንጋጤና መደናበር የሚመነጭ የሃይልና የበቀል እርምጃ ሰለሆነ፣ አሁን አገሪቱ ላለችበት የፖለቲካ ቀዉስ ዘላቂና ሰላማዊ መፍትሄ ያመጣል ብሎ መጠበቅ ከንቱ ምኞት ነዉ። ይልቁንም፣ ያገዛዙ እድሜ ካላጠረ፣ አገሪቱን ወደባሰ ቀዉስና ህልዉናዋን ወደሚፈታተን መቀመቅ ሊከታት እንደሚችል ጥርጥር ሊኖር አይገባም።
ይሁንና አንድ አገዛዝ በሚያጋጥመዉ የፖለቲካና ወታደራዉ ተግዳሮት ብቻ ከስልጣን አይወድቅም። የኢኮኖሚ መሰረቱ ያልተናጋ አገዛዝ፣ በፖለቲካዉ በኩል የሚደርሱበትን ችግሮች የማለፍ እድሉ ከፍተኛ ነዉ። ባንጻሩ በኢኮኖሚ የኮሰመኑ አገዛዞች፣ የፖለቲካ ኃይላቸዉም ይመነምናል፣ ብሎም የስልጣን እድሜያቸዉ ያጥራል። ከጥቂት አመታት በፊት በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛዉ ምስራቅ ከስልጣን የተባረሩ አምባ-ገነናዊ አገዛዞች፣ የፖለቲካ ስልጣናቸዉ ከማጣታቸዉ በፊት፣ የኢኮኖሚ መሽመድመድ ዉስጥ ገብተዉ ነበር።
ከዚያ ቀደም ብሎ፣ ባፍሪካ፣ የእኛን አገር ጨምሮ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካና በምስራቅ አዉሮፓ በአመጽ ከስልጣን የተባረሩ አምባገነኖች ሁሉ፣ ከፖለቲካዊና፣ ወታደራዊ ዉድቀታቸዉ በፊት ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ዉስጥ ተዘፍቀዉ ነበር። ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ያገዛዞቹን የበጀት አቅም በማቀጨጭ፣ አንደኛ በህዝቦች ዘንድ ታላቅ ተቃዉሞ ያስነሳል፤ ሁለተኛ ፖለቲካዊና፣ ወታደራዊ አመጾችን ለመጨፍለቅ የሚጠቀሙባቸዉን የጦርና ሌሎች መሳሪያዎች የመግዛት አቅማቸዉን ያደክማል፤ ሶስተኛ የስለላ መረቦችን ለመዘርጋት፣ ሆድ አደር ባለሟሎችን ለመግዛትና አፋኝ ኃይሎችን በጉርሻና በድለላ ለመያዝ የሚችሉበትን የገንዘብ አቅም ያመነምናል፤ ብሎም ዉድቀታቸዉንም ያፋጥናል።
ወያኔ-ህወሃት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ፣ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንቱ ከዉጭ የሚያገኘዉ ገንዘብ ነዉ። ያገሪቱ ኢኮኖሚ በድርብ አሃዝ ይደግም፣ አይደግም፣ የእንቅስቃሴ መሰረቱ ይኸዉ ከዉጭ የሚገኝ ገንዘብ ነዉ።
ከዉጭ የሚያገኘዉ ገንዘብ ምንጩ የተለያዬ ነዉ፦
ለለጋሽ አገሮችና አለም አቀፍ ድርጅቶች ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቶች ብለዉ የሚሰጡት እርዳታ፣
አገዛዙ ካበዳሪ ድርጅቶች በወለድ የሚወስደዉ ብድር፣
ከዉጭ የሚገባ ኢንቨስትመንትና፣
ዘመድ ለመርዳት በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የሚልኩት ገንዘብ (ሃዋላ)

ላገርና ለወገን እድገት የቆመ መንግስት ቢሆን ኖሮ፣ እነዚህ የገንዘብ ምንጮች ሁለት ታላላቅ ጥቅሞችን ያስገኙ ነበር። አንደኛ ከዉጭ የተፈጠረን ሃብት ወደ አገር ቤት እንዲገባ መንገድ በመሆን፣ ያገሪቱን ጠቅላላ የንብረት/ካፒታል ክምችት ከፍ በማድረግ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና የስራ እድል መፈጠር፣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችሉ ነበር።
ሁለተኛ፣ እነዚህ ገንዘቦች ወደ አገር ቤት የሚገቡት በዉጭ ምንዛሬ ስለሆነ፣ አገር ዉስጥ ሊመረቱ የማይችሉ መድሃኒቶችን፣ የህክምና መሳሪያዎችን፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን፣ እንዲሁም ለግብርና፣ ኢንዱስትሪና ኢንፍራስትራክቸር እድገት የሚያስፈልጉ ማሺኖችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና፣ ንጥረ ነገሮችን ከዉጭ ለማስገባት በማስቻል፣ ባገሪቱ ሁሉን አቀፍ የሆነ እድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይጫወቱ ነበር።
ችግሩ፣ ትልቁ ችግር፣ የትዉልድ አገራችንን ላለፉት 26 አመታት የገዛዉ ወያኔ-ህወሃት፣ ምንም ዓይነት ህዝባዊ ዉክልና የሌለዉ ከመሆኑ ዉጭ፣ ላገር ጥቅም የማይቆም፣ እንዲያዉም ያገርን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ረጅም ታሪክ ያለዉ መሆኑና መጠነኛ እድገት አለ ቢባል እንኳ ተጠቃሚዎቹ ካንድ ጎሳ የወጡና ጥቂት የስርዓቱ ተባባሪዎች ብቻ መሆኑ ነዉ።
ከዉጭ የሚገባዉ ገንዘብ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚጠቅም መንገድ፣ በምርታማ ስራ ላይ ካልዋለ የመጀመሪያ ዉጤቱ የዋጋ ንረት መፍጠር ይሆናል። ይህ የዋጋ ንረት ደግሞ በቅድሚያ የሚጎዳዉ ድሆችንና ዉስን ወራዊ ወይም አመታዊ ገቢ ያላቸዉን ያገሪቱን አብዛኛ ኗሪዎች ነዉ። ለዚህም ነዉ አገዛዙ በዋጋ ንረት የተጋነነ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘገብኩ እያለ ላለፉት አስር አመታት ከሚያስተላልፈዉ ፕሮፓጋንዳ ጎን፣ ያገሪቱ አብዛኛ ኗሪ ህይወት ከፍ ሊል ቀርቶ፣ ካመት ወደአመት ወደታች ሲያሽቆለቁል የሚታየዉ።
በሁለተኛ ደረጃ፣ አገዛዙ የሚያካብተዉ የዉጭ ብድር ለወደፊቱ ትዉልድ ታላቅ የእዳ ሸክም ትቶ ማለፉ አይቀሬ ነዉ።የወያኔ-ህወሃት መሪዎች የትምህርትና የእዉቀት እጥረት ያለባቸዉ፣ የባለሙያ ምክር የማይሰሙ፣ ድብቅና ሃላፊነት የጎደላቸዉ፣ ኢኮኖሚያዊ ዉሳኔዎችን በፖለቲካ መነጸር አይተዉ የሚወስኑ፣ ይልቁንም ላገርና ወገን እድገት ግድ የማይላቸዉ ስለሆኑ፣ ከዉጭ የሚገቡ ዉድ የዉጭ ምንዛሬዎችን የግል ጥቅም በሚያስገኙላቸዉ ወይም የስልጣን ዘመናቸዉን በሚያራዝሙላቸዉ ባካና መስኮች በገፍ እንደሚያጠፏቸዉ መገመት ቀላል ነዉ። እነዚህም ቀጥሎ የተመለከቱትን ይጨምራሉ፦
አገዛዙ ለጭቆናና ለግድያ የሚጠቀምባቸዉን የጦር፣ የስለላና ሌሎች መሳሪያዎች ከዉጭ ለመግዣ፣
በተለያዩ ዘዴዎች ያገዛዙ ቁንጮዎች በዉጭ ባንኮች በድብቅ ለሚያስቀምጡት ገንዘብ፣
ባለም ዙሪያ ካምሳ በማያንሱ ታላላቅ ከተሞች ዉድ ቢሮዎች ተከራይተዉ ያገዛዙን ፕሮፓጋንዳ ለሚነዙና፣ ዉጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ላይ የስለላ ስራ ለሚያቀናጁ የወያኔ-ህወሃት አምባሳደሮችና የኤምባሲ ሰራተኞች እነሱንም በተላላኪነትና በእግረኛነት ለሚያገለግሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ክፍያ
ያሜሪካ አስተዳደርና ቁልፍ ኮንግረስ አባላትን ድጋፍ ለማግኘት፣ የድለላ ስራ የሚሰሩ የሎቢ ድርጅቶችን ወይም ግለሰቦችን ለመቅጠሪያ፣
ለምሳሌ በቅርቡ እንደተጋለጠዉ፣ በአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ፊት ሞገስ ለማግኘት፤ በ January 2017, በአሜሪካ የወያኔ-ህወሃት አምባሳደር SGR Government Relations የተሰኘ የሎቢ ድርጅት በወር $150,000 ወይም ባመት $1.8 ሚሊየን ዶላር ቀጥሯል።
እንደ ኢሳት አይነቱን የዜና ምንጭ የስርጭት ሞገድ ለማገድ ቴክኖሎጂዎችና ተዛማጅ ባለሙያዎችን ለመግዣ፣
በተለይ በአሜሪካ አገዛዙን ተግተዉ በሚቃወሙና በሚያጋልጡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያንና እንደኢሳት አይነት ድርጅቶች ላይ ርባና ቢስ ክስ ለመመስረት የህግ ባለያዎችን መቅጠሪያ፤
በሚሊየን የሚቆጠሩ በርሃብ አለንጋ በሚገረፉበት ወይም በሚሞቱበት አገር፣ ለአገዛዙ በማደግደግ ያለቅጥ “ያለፈላቸዉ” ባለሟሎችና ባለሃብቶች ለሚንደላቀቁባቸዉ ዉድ ቋሚና አላቂ እቃዎችን ከዉጭ ለማስገቢያ፣
አገዛዙ ባገሪቱ ላይ ለጫነዉ የዉጭ እዳ ወለድ መክፈያ፣
በምርታማ ቦታ ላይ የሚዉሉ የዉጭ ምንዛሬዎች ቢኖሩም እንኳ በርካታ የኤፈርት ኮርፖሬሽኖች ቁልፍ የሚባሉ ያገሪቱን የኢኮኖሚ መስኮች ከአምሳ በመቶ በላይ በሚቆጣጠሩት አገር፣ ዋና ተጠቃሚ ያገዛዙ ቁንጮዎችና ባለሟሎቻቸዉ እንደሚሆኑ እሙን ነዉ።

በመጨረሻም፣ ምንም እንኳ ያገሪቱ አብዛኛ ህዝብ አሁንም በግብርና የሚተዳደር ቢሆን፣ ከሃያ ስድስት ዓመታት ከንቱ ፕሮፓጋንዳ በኋላ ባሳፋሪ ሁኔታ አገሪቱ አሁንም ራሷን በምግብ አቅርቦት ልትደግፍ ስላልቻለች ቀላል የማይባል የዉጭ ምንዛሬ ስንዴና የመሳሰሉ እህሎችን ለመግዣ ይዉላል።
የዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን የትግል መስክ እልፍ አእላፍ ጀግና ኢትዮጵያዉያን ህይወታቸዉን ላደጋ አጋልጠዉ አገዛዙን በፖለቲካና በእምቢተኝነት ትግል ወጥረዉ በያዙበት ባሁኑ ሰአት፣ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን የዚህ ትግል አጋር ለመሆን ከምንችልባቸዉ የትግል መስኮች፣ ኢኮኖሚያዊ እቀባ ማድረግ በጣም ቀላሉና ቀጥተኛዉ ነዉ። በዚህ ረገድ ልናደርጋቸዉ ከሚገቡ ተግባራት ዉስጥ ሁለቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰፊዉ ተወስተዋል፤ እነዚህም፦
አንደኛ- አገር ቤት ያሉ ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ለመርዳት የምንልከዉ ገንዘብ ወያኔ-ህወሃት እጅ እንዳይገባ ማድረግ ሲሆን – ይኸም፣ ገንዘብ መለካችን የግድ አስፈላጊ ከሆነ፣ በባንክ ሳይሆን የዉጭ ምንዛሬዉ አገዛዙ እጅ እንዳይገባ በሚያረጋግጥ መልክ ማድረግን፤
ሁለተኛ- ያገዛዙ የዉጭ ምንዛሬ ምንጭ የሆኑ አገልግሎቶችን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የበረራ አገልግሎትን ጨምሮ፣ አለመጠቀምን ይመለከታሉ።
በሶስተኛ ደረጃ ማድረግ የምንችለዉ ደግሞ፣ ይህ አገዛዝ ተወግዶ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አገሩና መብቱን በእጁ እስኪያስገባ ድረስ፣ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት አገር ቤት አለማድረግን ይመለከታል።
ኢንቨስትመንትን በተመለከተ፣ ባሁኑ ወቅት አገዛዙ ጸጉርን ያቆመ ስጋት ተፈጥሮበታል። በአገሪቱ ዙሪያ፣ በተለይም በኦሮሞና አማራ ክፍለ-አገራት በተፈጠረዉ እምቢተኛነትና አገዛዙ በወሰደዉ ጨካኝ ርምጃ የተደናገጡ የዉጭ ኢንቨስተሮች እጃቸዉን መሰብሰባቸዉን በዜና ምንጮች በቅርቡ ታትቷል። በዚህም መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ወደአገሪቱ የገባዉ የዉጭ ኢንቨስትመንት ሃያ በመቶ ወይም በ$300 ሚሊየን ዶላር ዝቅ ብሏል።
በተመሳሳይ መልክም ያገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየቀዘቀዘ የመጣ ሲሆን፣ አገሪቱ ወደዉጭ የምትልከዉ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ወርዷል፤ ለምሳሌ፣ ከመስከረም እስከጥር በነበሩት ወራት ወደዉጭ የተላከዉ ምርት አገዛዙ አቅዶት ከነበረዉ በ$700 ሚሊየን ዶላር ዝቅ ብሏል።
አገሪቱ ወደዉስጥ የምታስገባቸዉ ሸቀጦችና ሰርቪሶች ወጭ፣ ወደዉጭ በምትልካቸዉ ሸቀጦችና ሰርቪሶች የምታገኘዉ ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ$10.5 ቢሊየን ዶላር ይበልጣል። አገዛዙ ይህን ከፍተኛ የዉጭ ንግድ ቀዳዳ ለመሸፈን ከሚያስችሉት መንገዶች ዉስጥ፣ አንዱ ከዉጭ የሚበደረዉ ገንዘብ ሲሆን፣ ይህም እዳ ባሁኑ ወቅት ከ$20 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል።
ሌላዉ የዉጭ ምንዛሬ ምንጭ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ወደትዉልድ አገራቸዉ የሚልኩት ገንዘብ ሲሆን፣ ይህም ካመት ወደአመት ከፍ እያለ መጥቶ በ2015 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.) $3.7 ቢሊየን ዶላር እንደደረሰ አገዛዙ ገልጿል። ከዚሁ ዉስጥ ምን ያህሉ ለኢንቨስትመንት የተላከ እንደሆነ ባይታወቅም፣ በኢንቨስትመንት ተሳትፈዋል ተብለዉ ከሚገመቱት በሺህ የሚቆጠሩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር አንጻር ቀላል የማይባል መጠን እንደሚኖረዉ መገመት ይቻላል።
የወያኔ-ህወሃት አገዛዝ በተለያዩ ጊዜያት ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያንን ለማማለልና በእጁ ዉስጥ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረቶችን ማድረጉ ይታወቃል። ከተጠቀመባቸዉ ዘዴዎችም ዉስጥ፣ ቤት ለመስራት ወይም ቢዝነስ ለመክፈት ለሚፈልጉ፣ በነጻ ወይም በትንሽ የኪራይ ዋጋ መሬት መስጠት አንዱ ነዉ። ይህ የማታለል ድርጊት ግቡን መቷል ማለት ከቶ ባይቻልም፣ ቀላል ቁጥር የሌላቸዉ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን በትዉል አገራቸዉ ቤት ሰርተዋል፤ የተወሰኑት ደግሞ ቢዝነስ ከፍተዋል።
ባሁኑ ወቅት፣ አገዛዙ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያንን በድምሩ በጠላትነት የፈረጀበት ጊዜ ነዉ። ጥፋታቸዉም ያገዛዙ ጥይት፣ ወከባ፣ እስራትና ስደት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻቸዉ ጎን በመሰለፍ እሮሮአቸዉን ማስተጋባታቸዉ ነዉ። ይሁን እንጂ አገዛዙ አሁን ካለበት ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ እጦት የተነሳ፣ ብዙን ሳይቆይ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያንን ማግባባት መጀመሩ አይቀርም።
የወያኔ-ህወሃት አገዛዝ ከዉጭ የሚያገኘዉ የዉጭ ምንዛሬ ቢደርቅ፣ ለጥቂት ወራት በስልጣን መሰንበት አይችልም። ይህም ማለት ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ፣ አገዛዙን በኢኮኖሚ መስክ ለማሽመድመድ፣ ብሎም እድሜዉ ለማሰጠር ቀላል የማይባል አቅም በእጃችን ዉስጥ አለ።
ባሁኑ ወቅት በትዉልድ አገራችን ቤት መስራት ወይም ሌላ ኢንቨስትመንት ማድረግ ግላዊ ጥቅምን ሊያስገኝ የሚችል ቢሆንም እንኳ፣ ለአገዛዙን የእድሜ እስትንፋስ ስለሚጨምር፣ በዚያዉ ልክ የወገኖቻችንን ስቃይና መከራ የሚያራዝም ነዉ የሚሆነዉ።
ስለዚህ አገርና ወገንን ለመታደግ አዉሬዉን ማስራብ ብሎም የሚወድቅበትን ጊዜ ለማሳጠር መረባረብ የሁላችንም ሞራላዊ ግዴታ ነዉ!

No comments:

Post a Comment