Wednesday, March 22, 2017

አለም-አቀፍ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ተጠቅሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን እንዲያስቆም ጥሪ ቀረበ




የአለም አቀፍ ማህብረሰብ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በማቆም በሃገሪቱ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲያበቃ አንድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋም ጥሪ አቀረበ።
መቀመጫውን በቤልጂየም ብራሰልስ ከተማ ያደረገውና ውክልና ያልተሰጣቸው ህዝቦች ድርጅት (Unrepresented Nations and People’s Organization) የሚል መጠሪያ ያለው ድርጅት በኢትዮጵያ ይፈጸማሉ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ አፈናዎችና፣ ድብደባዎች በተመለከተ የባለ 27 ገፅ ሪፖርት አቅርቧል።
የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች አካላት ሪፖርቱን ያቀረበው የሰብዓዊ መብት ተቋሙ፣ በኢትዮጵያ በተለይ የሶማሌ ክልል ስር በሚገኘው የኦጋዴን አካባቢ በርካታ ሰዎች የመንግስት ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን አስታውቋል።
እየተፈጸመ ያለውን ይህንኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ የኢትዮጵያ አጋር ሃገራትና የልማት ድርጅቶች የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጥ ይኖርባቸዋል ሲል ድርጅቱ በሪፖርቱ ገልጿል።
ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል ከእሬቻ በዓል አከባበር ጋር በተገናኘ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ያወሳው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሃገሪቱ ጥያቄን አንስተው ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች በገለልተኛ አካል ምርመራ እየተካሄደባቸው አለመሆኑን ኮንኗል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር አባልና ደጋፊ ናችሁ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አስገድዶ መድፈር ድርጊት ጨምሮ ስቃይና ወከባ እንደሚፈጸምባቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።
መቀመጫውን በቤልጂየም ብራሰልስ ከተማ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትኩረት እንዲያገኙ ሲሉ ያቀረበውን ሪፖርት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይን ያካተተ አይደለም ሲል ቅሬታ አቅርቦ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
ይህንኑ ቅሬታውን ተከትሎ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ሰፊ ሪፖርትን ያቀረበው ተቋሙ፣ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ መጠነ ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኦሮሚያ የሶማሌ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎች መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኦጋዴን አካባቢ ጥሎት የሚገኘው የጉዞ እገዳ በስፍራው እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአግባቡ ለመረዳት አስቸጋሪ አድርጎት መቆየቱንም ድርጅቱ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ባሰራጨው ሪፖርቱ አስፍሯል።
በገዢው የኢህአዴግ መንግስት አቀነባባሪነት ሆን ተብለው የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ እስራትና፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ተባብሰው ቀጥለዋል ያለው Unrepresented Nations and People’s Organization በልማት ስም ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ በርካታ ሰዎች የዚሁ ሰለባ መሆናቸውን አክሎ አመልክቷል።
በኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በአፋር ክልሎች ሲካሄድ የቆየው የመሬት ቅርምት ለበርካታ ሰዎች እስር ምክንያት ሆኖ መቆየቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ እንዲሁም ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በሪፖርቱ በዝርዝር መቅረባቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ተመሳሳይ መረጃን ለጋዜጣው የሰጠው የጸጥታ ባልደርባው የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል አክሎ ተናግሯል።

No comments:

Post a Comment