Tuesday, March 21, 2017

በጋምቤላ የባለሃብቱ ልጅ የራስ ቅሉ አራት ቦታ በጥይት ተመቶ ተገደለ




ዛሬ በኢትዮጵያ ታትሞ የተሰራጨው ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበው ከጋምቤላ ዋና ከተማ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዲማ ወረዳ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ወጣት አማኑ መኮንን ኢተፋ ከጫካ ውስጥ በመጡ ማንነታቸው ለጊዜው ባልታወቁ ኃይሎች በአራት ጥይት ተደብድቦ መሞቱን ተገለጸ::
የሟች ወጣት አማኑ መኮንን ወላጅ አባት አቶ መኮንን ኢተፋ በትናትናው ዕለት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጹት “አለምንም ምክንያት በጥይት ተመቶ ነው የተገደለው:: ከ እርሻ ቦታ ወደከተማ የቀን ሠራተኞችን ለማምጣት እየሄደ በመውጣት በጥይት ደብድበው ገድለውታል:: ጉዳዩን ለጣቢያ አመልክቻለሁ:: አሁን የልጄን አስከሬን ይዤ ወደ ነቀምት እየሄድኩ ነው” ብለዋል::
“ቤተሰብ እስከመግደል የሚያደርስ ጠብ ወይም በሌላ ሁኔታ የሚጠራጠሩት ሰው አለ ወይ?” በሚል በሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መኮንን “ልጄ ከሰው ተግባቢ በአካባቢው የሚወደድ ነው:: እኔም በግሌ ጠብ ውስጥ የገባሁበት ሁኔታ የለም:: የምጠረጥረው ሰው የለኝም::: ለልጄ ሞት የምሰጠው ምክንያት የከኝም:: ፍርዱ ከአምላክ ነው የምጠብቀው” ብለዋል::
በአካባቢ የነበሩ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዓይን እማኝ እንደገለጹልኝ ሲል የዘገበው ሰንደቅ ጋዜጣ “ሟች ጥቃቱ ከደረሰበት በኋላ ከዋናው መንገድ ከመኪና ላይ ሸሽቶ ለማምለጥ ሞክሮ ነበር:: አስከሬኑን ያገኘነው ጫካ ውስጥ ነው:: የራስ ቅሉ አራት ቦታ በጥይት ተመቶ ፈርሶ ነበር:: አባቱም በአቅራቢያ ባለመኖሩ አስከሬኑ በአዲስ አበባ ሚሊልክ ሆስፒታል አስመርመርን አሁን እርሱን አጅበን ወደ ወለጋ እየተጓዝን ነው” ብለዋል::
አቶ መኮንን ኢተፋ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው እየሰሩ የሚገኙ ባለሃብት መሆናቸውን ሰንደቅ ጋዜጣ ዘግቧል:: የክልሉ የኮምዩኢኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላዲ አቶ ዑመድ ኡቶ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ቃል “ወጣቱ መገደሉን አውቃለሁ ግን ዝርዝር መረጃ የለኝም” ብለዋል::

No comments:

Post a Comment