Saturday, March 18, 2017

የቆሼውን እልቂት ፖለቲካ ነው አትበሉ?! – ከተማ ዋቅጅራ



በኑሮ ተገፍተው ፍርደ ሚዛኑ ለእውነት አላመዝን ብለው የሰው ልጅ መኖር በሚከብድበት ቦታ ላይ መከራና ችግር ሳይበግራቸው ወደው ሳይሆን የግዜው ሁኔታ አስገድዶአቸው የቆሻሻ ሽታውና የቆሻሻው ቃጠሎ አየሩን በክሎት ጉም በሚመስል ጭስ ውስጥ ህይወታቸውን የሚገፉት እነዚህ ወገኖቻችን ቆሻሻ ላይ ኖረው ቆሻሻ ተደርምሶባቸው ህይወታቸው እንዲያጡ በኢትዮጵያ መንግስ የተፈረደባቸው ለምን ይሆን? በእንባና ከጥልቅ ኃዘን ጋር ከቆሻሻው መሃል ሟች ወገኖቻቸውን መፈለግ ምን ያህል እንደሚያም ሁላችንም እናውቃለን ምነዋ ወገኖቻችን ላይ እንደዚህ የመረረ ችግር ተጭኗቸው የመረረ ሃዘን እስከሚደርስባቸው በህዝብ ተመርጫለው ያለው መንግስት የት ነበረ ብሎ መጠየቅ ለነሱ የፖለቲካ ጉዳይ ነው።

በለቡ፣ በየካ፣ በመሃል አዲስ አበባ እና በዳር አዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸው ክረምትን እየጠበቁ በማፍረስ ቤት አልባ በማድረግ ጎዳና ላይ እንዲወጡ ሲደረጉ ምን አልባትም ዛሬ በቆሼ የደረሰው አደጋ ቤታቸውን በማፍረስ ቤት አልባ ያደረጋቸው ዜጎቻችን ሊኖሮበት እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለው ህጻናትን፣ አዛውንትን ብሎም አራስ እናቶችን በላያቸው ላይ ቤታቸውን የማፍረሱ ውጤት ነው ዛሬ ያየነው ብሎ መናገር ለነሱ ፖለቲካ ነው።
ኮንደሚኒዬም ተሰርቶ እየታደለ ያለው ቤት ላለውና ትርፍን ማካበት ለሚፈልጉ ጥቅመኞች እንጂ ቆሻሻ ለይ ለሚኖረው ቤት አልባው ህዝባችን አይደለም ብሎ መናገር ለነሱ ይሄም ፖለቲካ ነው።

ግለሰቦች የተዘጉ ኮንደሚኒዬሞችን ሰብረው በመግባት ያለ አግባብ ሲኖሩበት እና ሙሉ እንጻውን በማን አለብኝነት እያከራዩ የሚጠቀሙት እንዲሁም ሪል ስቴት እና ኮንደሚኒየሙን የተቆጣጠሩት ፍቃድ ያላቸው ሙሰኞች ናቸው ለደሃው ኢትዮጵያዊ ብሎም ለአዲስ አበባ ተወላጅ ነዋሪ የቤት ባለቤት የመሆን እድሉ የለም ብሎ መናገር ይሄም ለነሱ ፖለቲካ ነው።
ተገፍተው ተገፍተው ቆሻሻ ላይ እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያን ወገኖቻችን አድገናል ሃብታም ሆነናል የሚሉት በሚጥሉት ቆሻሻ ክምር ስር ወደው ሳይሆን አማራጭ በማጣት መርጠውት ሳይሆን ኑሮን ማሸነፍ ግድ ሆኖባቸው ነገን ለማየት ተስፋን የሰነቁ ድንገት እንደዚ አይነት ጆሮን ጭው የሚያደርግ ዜናን ሲሰማ ምን ያህል እንደሚያም ሁላችንም እናውቃለን። ይሄንን ያህል ግዜ እና እንደዚህ አደጋ እስከሚደርስባቸው ዝም ብሎ ከሶስት ቀን በኃላ መንግስት ድምጹን ሲያሰማ የጀርመን ኤንባሲ ሃዘኑ ልባቸውስት ገብቶ የአውሮፓ ህብረት እና የአገራቸውን ባንድራ ዝቅ አድርጎ በማውለብለብ ሃዘናቸውን በአፋጣኝ ገልሰዋል። የጀርመን ኤንባሲን በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያን ህዝብ ስም ላመሰግን እወዳለው።
በቆሼ ወገኖቻችን አሳዛኝ ክስተት የኢትዮጵያ መንግስት ጭንቢል የወለቀች ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከኑሮአቸው ጀምሮ እስከ ሞታቸው ድረስ በጥልቅ ኃዘን ሲዋጥ ገዢዎቻችን እና ካድሬዎች ያዘኑት መጥፎ ገጽታቸው ሊሸፍኑት በማይችሉት መልኩ ለዓለም ማህበረሰብ ፍንትው ብሎ አደባባይ መውጣቱ ነው። በእውነት ላይ ያልተመሰረት እድገት እና በእውነተኛ ታሪክ ያልታገዘ የፖለቲካ አዙሪት ለግዜው ምስኪኑን ኢትዮጵያዊ ቢጎዳም ቅሉ የኋላ ኋላ ግን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ችግር ፈጣሪዎችን ጠራርጎ የሚያጠፋበት ማዕበል እንደሚፈጥር መዘንጋት እንደሌለባቸው ላስታውስ እወዳለው።
ይሄንንም ደግሞ ፖለቲካ ነው እንዳትሉኝ!!! አበቃው
ከተማ ዋቅጅራ

No comments:

Post a Comment