Saturday, March 18, 2017

አዳማ ከኦሮሚያ የመውጣት መብቷ ሊከበር ይገባል – ይመር አብዶ

   



hqdefault
የአዳማ ልጅ ነኝ። እዚያው ተወልጄ ያደኩ። አባቴ ኦሮሞ ሲሆን እናቴ ጉራጌ ናት። አባቴ ኦሮምኛ ይናገራል። ግን ቤታችን የሚነገረው አማርኛ ነው። በአብዛኛው የናዝሬት ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ነው። በከተማዋ በየመንገዱ በብዛት የሚነገረው አማርኛ ነው። አዳማ ናዝሬት እንደ አዲስ አበባ ናት ማለት ይቻላል።
የናዝሬት ህዝብ አጣብቂኝ ዉስጥ ያለ ሕዝብ ነው የሚመስለው። ናዝሬት የኦሮሚያ ክልል መንግስት መቀመጫ ናት። በዚያ የክልሉ ምክር ቤት ጨፌው ይሰበሰባል። የጨፌዉን ስብሰባ ለተመለከተ ግን በምንም መስፈርትና ሚዛን ፣ የናዝሬትን ሕዝብ የሚወክል ስብስበ ስለመሆኑ የሚያመላከት ነገር አይታይበትም። ለምሳሌ አብዛኛው የናዝሬት ህዝብ በጨፌው የሚነገረዉ ንግግርና ዉይይት መከታተል እንኳን አይችልም።የሕዝብ ተወካይ ነን ባዮቹ ተሳስተው እንኳን በጨፌ ዉስጥ አማርኛ አይናገሩም።
በክልሉ ሆነ በከተማዋ መስሪያ ቤቶች ከሄድን፣ አቶ ግርማ ካሳ እንደገለጹት፣ ማመልከቻ ለማስገባት ችግር ነው። በአማርኛ ጽፈን፣ ገንዘብ በመክፈል ወደ ቁቤ እስተርጉመን ነው ማመልከቻውን የምናስገባው። ከክልሉ መንግስት ደብዳቤ ከተላከልንም፣ የተጻፈውን የሚተረጉምልን መፈለግ ግዴታ ነው። ይህ አይነት ችግር ያለባቸው ከአዳማ ናዘሬት ነዋሪዎች 2% ወይም 5% ቢሆኑ እሺ፣ ግን 75% የሚሆነው ህዝብ ለዚህ አይነት ችግር የተጋለጠ ነው።
አብዛኞቹ የናዝሬት ነዋሪዎች እየፈራን ነው የምንኖረው። የመብት ጥያቄ ብናነሳ ኦህዴዶች የፈለጉትን ሊያድርጉብን ይችላሉ። ዘመኑ የነርሱ ነውና። ተወልደን ባደግንበት ከተማ፣ አማርኛ ተናጋሪ በመሆናችን መጤ ነው የሚሉን። በመሆኑም አብዛኛው ህዝብ ዝምታን መርጦ ነው ያለው።
የአቶ ግርማ ካሳ ጽሁፍን ዘሃበሻ ላይ ሳነብ፣ በአብዛኛው የናዝሬት ነዋሪ ልብ ውስጥ ያለውን ትልቅ ጉዳይ አጉልቶ በማውጣቱ እንደ ናዝሬት ነዋሪ ደስ ነው ያለኝ። በዚህ አጋጣሚ ለአቶ ግርማ ምስጋናዬን ማቅረብ እወደለሁ። ስለ ወልቃይት ጠገዴ ብዙ ይወራል። “በወልቃይት መሬቱ የትግራይ ነው፣ እናንተ ትግሬ ናችሁ፤ ትግሬነትን የማትቀበሉ ከሆነ ወደ አማራው ክልል መሄድ ትችላላችሁ” እየተባሉ ነው። የወልቃይት ጥያቄም ትኩረት አግኘቶ ሕዝብን ማንቀሳቀሱ ተገቢ ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ናዝሬት ባሉ ከተሞች የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎችም በግድ ኦሮሞነት እየተጫነባቸው ነው። ኦሮምኛ የማይናገሩ ከሆነ ፣ ራሳቸውን ከኦሮሞነት ጋር የማያስተሳስሩ ከሆነ መኖር እንዳይችሉ ተደረጎ ነው ኦህዴድ እየተንቀሳቀሰ ያለው። የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲከበርለት ፣ ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ ጎንደር እንዲቀላቀል እያደረገ ያለው ትግል ትኩረት እንደተሰጠው፣ አቶ ግርማ እንደጠየቁት፣ የናዝሬት ሕዝብ ጨመሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች ከኦሮሚያ ወጥተው የራሳቸው አስተዳደር የመመስራት መብታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል። የናዝሬት ህዝብ በማይወክሉት መተዳደር የለበትም።
የአዳማ ህዝብ ሆነ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው ህዝብ ቢጠየቅ ሊመለስ የሚችለው የታወቀ ነው። አቶ ግርማ እንዳሉት ከኦሮሚያ ዉጭ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ነው የሚፈለገው። የሕዝብ ፍላጎት ደግሞ በማስፈራርት፣ በኃይል ወደ ጎን ማድረግ አይቻልም። እርግጥ ነው በአንዳንድ የኦሮሚያ ዞኖች አሁን ያለችው ኦሮሚያ እንድትቀጠል ጠንካራ አቋምና ፍላጎት አላቸው። ሆኖም ግን የነርሱን ፍላጎት በሌላው ላይ መጫን አይችሉም። እነርሱ የፈለጉት ወይም እኛ የፈለግነው ሳይሆን ሕዝብ የፈለገው ነው መሆን ያለበት። ህዝብ ደግሞ በወረዳ ደረጃ፣ በዞን ደረጃ ከአንድ ክልል ወጥቶ ራስን ማስተዳደር ወይንም ከሌላ ክልል ጋር መቀላቀል ከፈለገ መብቱ እንደሆነ መታወቅ አለበት።

No comments:

Post a Comment