Tuesday, March 28, 2017

የህግ ሽፋን የተሰጠው በደል! – ይድነቃቸው ከበደ


“ለራሳችሁ ስትሉ ጉድጓዱን አርቃችሁ አትቆፍሩት፣ መከራውንና ግፍን በፅናት የምንቀበለው፣ እኛም፣ እናንተም አብረን ነፃ እንወጣ ዘንድ ነው!”

ዓይናችሁን በጨው አጥባችሁ እዩኝ እዩኝ የምትሉ አቤት ድፍረታችሁ ! ዛሬ አብዛኛው ሰው በደረሰበት ስቃይ ሐዝነው፣ ምንም ማድረግ እንኳን ባይቻላቸውም በፀሎትና በሃሳብ ከሱ ጎን ሲቆሙ፣ እነዚያ የስም ላጲሶች የሐሰት ተግባራቸውን ነገ ሊቀጥሉበት ዛሬ ከሰው መምሰል እና እነሱም እንዲህ አሉ ለመባል ድፋ ቀና ሲሉ ለጉድ ነው። የቀድሞ አንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ሀብታሙ አያሌው ፣ በማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ በእሱና በሌሎች ላይ የደረሰባቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊት በሁለት ክፍል በተከፋፈለው ቃለ መጠይቅ ይፋ አድርጓል ።

ታሰረ ሲባል ፣የታሰረው የደህንነት ስልጣና ሊወስድ ነው፣ እሱ ወያኔ ነው። ታመመ ሲባል ህመሙ ትንሽ ነው፣ እሱ አውቆ ለማስመሰል እና የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ነው። በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ ነበር።በስንት መከራ እና ጉትጎታ ለእክምና ወደ ውጪ ወጣ ሲባል፣ ድሮስ እሱ ውጪ እንዲወጣ ይፈቀድለታል የእሱ ጓደኛ እስር ቤት ይወረወራሉ፣ ይሉ ነበር ። ኧረ እንዲህ አይባልም ይቅር ይሄ ነገር በማለት አስተያየት ለሚሰጡ፣ይሰጥ የነበረው ምላሽ ። መታሰርን ለዕውቅናና ለታማኝነት ማረጋገጫ መጠቀም ይቻላል።ምን ችግር አለው።በተለይ ድብደባ ተፈጸመብኝ ሲል ትኩረት ለማግኘት ቀላል ነው። እግዚኦ ምን ያልተባለ ነገር አል ። ግን ማንም ምንም ሊል ይችላል ፣እውነት ግን መቼም ቢሆን እውነት ነው። የሚገርመው ነገር ነገ ሙሉ በሙሉ ጤናው ተመልሶ ለሃገሩ የበኩሉን አሰተዋአዖኦ ሲያደርግ ፣እነዚያ የስም ላጲስ እንደ-እነሱ መምሰል ካልቻለ እና እነሱ በሚፈልጉት መንገድ የማሄድ ካልመሰላቸው፣ መልሰው እንደ ትንሽነታቸው የትንሽ ሥራ ለመስራት ሲባክኑ መታየታቸው አይቀርም ።

የሐብታሙ አያሌውን ቃለ መጠይቅ ያዳመጠ ማንም ቢሆን ሰውነቱ በድንጋጤ ይሸማቀቃል፣ ልብ በሐዘን ይሰበራል፣ከዓይኖቹ ዕንባ ዱብ ዱብ ይላል፣የሰው ጭካኔ ምን ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ በማሰብ ፣ሁሉም ለእራሱ ያለቅሳል።በተለይ የዚህ አይነቱ ግፍ ህጋዊ ሽፋን ተሰጥቶት ሲፈጸም ፣ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት ያጣል። በዚህም ምክንያት መንግስትና ህዝብ ሆድ እና ጀርባ ይሆናሉ። በዚህን ጊዜ፣ የህግ ሽፋን ተሰጥቶት መንግስታዊ በደል በዜጋ ላይ በዚህ ደረጃ መፈጸሙን የማይቀበል ዜጋ ይበረክታል። እራስንም ከእንዲ አይነቱ ጥቃት ለመከላከል ይጠቅመኛል የሚለውን ይመርጣል። እርግጥ ነው ፣ እንደዚህ አይነቶ አስከፊ በደል በመፍራት የያዙትን ትልቅ ዓላማ የሚተው ጥቂቶቹ አይደሉም ። የግፈኞችም ትልቁ ዋና ዓላማ ይሄ ነው።

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ፣በተለያየ ወቅት፣ከዚያ ከማሰቃያ ቦታ ህይወታቸው ተርፉ የወጡ እንደገለጹት ከሆነ፣ የገራፊዎቹ ነውረኝነት እና ከእንስሳ ያልተሻለ ጭካኔያቸው ለአዕምሮ የሚከብድ፣ ለመንገርም ሆነ ሲናገሩ ለማዳመጥ የሚሰቀጥጥ ነው።በተለይ ከአካላዊ ስቃይ ባሻገር ሰው የመጣበት ዘርና የወላጆቹ ብሔር እየተጠየቀ ሲሰደብ እና ሲገረፍ የእውነት ከዚህ በላይ ምን ስቃይ አለ ?! ምንም!!! የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆነው ፣አቶ አግባው ሰጠኝ ፤ፍርድ ቤት ቀርቦ በተደጋጋሚ እንደገለጸው፣ “በህግ ሽፋን በድል እየተፈጸመብን ነው”በማለት አቤቱታውን ከመግለጽ አንድም ቀን ወደኋላ ብሎ አያቅም ።

በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ 15ኛ ተከሳሽ የሆነው፣ አቶ አግባው ሰጠኝ “እኔ ዘረኛ አይደለሁም፣ፍጹም ዘራኛ በሆኑ የማረሚያ ቤት አስተዳደሮች እና ጥበቃዎች “ዐማራ”ነህ እያሉ ስቃይና
እንግልት እያደረሰብኝ ነወ፡፡” በማለት መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም በከፍተኛው ፍርድ ቤት 10ኛ ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ነው፡፡ ይህን አቤቱታ በሚያቀርብበት ወቅት ፣ በደረሰበት በደል የረሃብ አድማ ላይ ነበር። አግባው እንዲህ አይነቶ በደል ተፈጽሞበት፣ እኔ ዘረኛ አይደለሁም፣ ፍጹም ዘራኛ በሆኑ “በደል እየተፈጸመብኝ ነው ፤በማለት ዘረኝነትን ይቃወም ነበር።

ሌላው በደል የተፈጸመበት አቶ ባህሩ ደጉ፤ በማዕከላዊ የደረሰበትን ስቃይ፣ “ይድረስ ለገራፊዎቻችን”በሚል ከእስር ቤት ጽፉ ለንባብ በበቃው ደብዳቤ፣ ደርሶበት የነበረው ስቃይ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው።ባህሩ በእሱ እና በጓደኞቹ የደረሰባቸውን በደል እና ስቃይ ችሎ እንዲህ የሚል መልእክት አስተላልፏ ነበር። ” ያደረጋችሁብን ሁሉ ፅናታቸውንና የሀገር ፍቅራችን ይበልጡን አጠናከረው እንጅ ቅንጣት ታክል አልቀነሰብንም፡፡ ግን ለራሳችሁ ስትሉ ግፍና ሰቆቃውን ባታበዙት ይሻላል፡፡ እደግመዋለሁ! ለራሳችሁ ስትሉ ጉድጓዱን አርቃችሁ አትቆፍሩት ፡፡ እኛ መከራውንና ግፍን በፅናት የምንቀበለው እናንተን ወደ ትልቅ ጉድጓድ ገፍትረን ነፃ ለመውጣት ሳይሆን በጋራ፣ እኛም፣ እናንተም አብረን ነፃ እንወጣ ዘንድ ነው!” በማለት መከራ እየተቀበለ ፣ መከራውን ለሚያሳዩት ጭምር በጎውን ነው የተመኘ ምርጥ ሰው ነው ።

በተለያየ ወቅት የተለያዩ ሰዎች፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ከፍተኛ እስር እና እንግልት ተፈጽሞባቸዋል፣ አሁንም እየተፈጸመ ይገኛል። እንዲህ አይነቱ በደል እንዲቆም ከማድረግ ይልቅ ፣ ሊናገሩት እንኳን የሚከብድ በደል የደረሰባቸውን ሰዎች፣ የንፋስ ሽውታ ያላገኘው የማህበራዊ ድረ ገጽ ” ጀግኖች ¡” ስቃይና እንግልት የደረሰባቸውን ፣ ከእነሱ ሃሳብ የተለየ የሚያስብ እና ሃሳብን ለመግለፅ የሚሞክር ፣ ያለ-ገብሩ ስም እየሰጡ ማብጠልጠል ትርፉ የህሊና ዕዳ ነው።

No comments:

Post a Comment