Thursday, March 16, 2017

የፓትርያርኮች ምርጫና ተሃድሶ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን




ዘማርያም ከአትላንታ
ዲያቆን ህዝቅያስ መኮንን የተባለ የማህበረ ቅዱሳን ፕሮፖጋንዲስት ፤ኢሳያስ 8 ቁጥር 19 ያለውን ጥቅስ ተንተርሶ የህዝቡን ጥያቄ ማን ይመልሰው በሚል አርእስት ያሰተማረው ትምህርት ላይ ፤ተሃድሶ የሚል ፍረጃ የያዘች ጣቶቹን ወደ ታላላቅ የሃገራችን አባቶችም በጅምላ መጠቆሙን አስተውያለሁ።ተሃድሶ የሚባለውን ቃል ማህበሩ የሚጠቀምበት ሃራጥቃ/Heretic ለማለት ነው። ሀራጥቃ ማለት ደግሞ ፤የራሱን የተሳሳተ የግል አስተያየት ንፁህ የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት እምነት ውስጥ አምጥቶ የሚቀላቅል፤ ሃሰተኛ ትምህርት የሚያስተምር፤ የቤተክርስትያንን ስርአት የሚቀይር ከተቻለም የሚንድ ማለት ነው።ባሁን ሰአት ተሃድሶ ማነው የሚለው ግራ አጋቢና አወዛጋቢ ነው።ምክንያቱም፤ ካለው ፕሮቴስታንታዊ ተሃድሶ በተጓዳኝ በማህበረ ቅዱሳን እየተደረገ ያለው ትክክለኛ የቤተክርስትያን አባቶችን አስቀድሞ ተሃድሶ እያሉ በማሸማቀቅና አፍ በማስያዝ፣ ማህበረ ቅዱሳናዊውን ተሃድሶ ካለምንም ተገዳዳሪ ማስፋፋት እንዳለ እናውቃለንና።አባቶችን ማዋረድ፣ ክብር አለመስጠትና የምናየው ከዚህ በፊት ቤተክርስትያናችን ያልነበረ የአለባበስ ለውጦች ጥቂቶቹ ናቸው።የዚህን ማህበር እምነት በተመለከት ውስጡን ለቄስ ብሎ መተው ይሻላል።
የዲያቆኑ ትምህርት እንደምታ በሃገራችን የተደረጉ የፓትርያርኮች ምርጫዎች እንደ ሌሎች የአለም አብያተ ቤተክርስትያናት ዕጣ በማውጣት አልተካሄዱምና ኢትዮጲያውያኑ አባቶች የሃይማኖት ድንበር አፍላሾች ተሃድሶዎች ናቸው የሚል ነው።አንድን አስተሳሰብ አዲስ በቤተክርስትያናችን ያልነበረ ወይም ተሃድሶ ለማለት መነሻችን አባቶቻችን ካልሆኑና እነርሱም መሰረት አይደሉም የምንል ከሆነ አንድን ሃሳብ መጤ ፣አዲስ፣ቀያሪ፣የተሳሳተ ለማለት ማነፃፀርያ እናጣለን። ሁላችንም አብረን ወደ ባሰ ቀውስ እንነጉዳለን።በሌሎች የአለም አብያተ ቤተክርስትያናት የፓትርያርክ ምርጫ የሚካሄደው በዕጣ ነው ስንል ይህ እውነት ላይ ያልተመርኮዘ ነጭ ውሸት ከሆነ ደግሞ ጭራሽ ትምህርቱ ሌላ ድብቅ አላማ ሊኖረው ይችላል ብለን እንድንጠራጠር ያደርገናል።ትምህርቱ የሃዋርያት ስራ ምእራፍ 1 ቁ 20 አካባቢ ካለው ታሪክ ይነሳና
ሃዋርያቱ ማትያስን በአስራ ሁለተኛ ሀዋርያናት ሲመርጡ ፀጋው የበዛላቸው ሲሆኑ በግዴለሽነት አንዱ ይሁን አላሉም መንፈስ ቅዱስ ያፅድቅ አሉ፣ ፀልየው ሲያበቁ ፣የመረጥከውን ሹም አሉና እጣ ጣሉ ፣እጣው ለማትያስ ወደቀ አስራ ሁለተኛ ሆኖ ተቆጠረ
በማለት የተሰመረበትን የራሱን የግል ሃሳብ ማለትም ግዴለሽ መሆን አለመሆን የሚለውን ከመፅሃፍ ቅዱስ እውነት ጋር ቀላቅሎ ይንደረደርና ለኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያላውን ንቀት ኢትዮጲያውያኑን ጳጳሳት በአንፃራዊ አነጋገር ፣ፀጋው ያልበዛላቸው፣ለሃዋርያዊ ህግጋት ግዴለሾች በማለት ይፈርጃቸዋል።ይህንንም ፀረ ኢትዮጲያዊ ፓትርያርክና ፀረ ኢትዮጲያዊ ጳጳሳት እስተሳሰብ የበለጠ ሽፋን ለመስጠት የሚከተለውን በሬ ወለደ ውሸት ይረጫል ሀሰተኛ ትምህርቱን ይነዛል፣ምእምናንን ያሳስታል።
ከዝያ ጊዜ ጀምሮ ከሃዋርያት በሁዋላ የተነሱ አባቶች በሌሎቹ አብያተ ክርስትያናት በኛ አብያተ ክርስትያናት ሲቀር ይህ ስርአት ይህ ክንውን አለ በኛ ቤተ ክርስትያን ግን የለም የተረሳ መድሃኒት ሆኗል
ከሃገራችን ኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በስተቀር ይህ የዕጣ አሰራር በሌሎች በሁሉም አብያተ ክርስትያናት አለ የሚለውን የተሳሳተ ሃሳብ ለመደገፍ ያቀረበው ግን አንዱን የግብፅን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በቅርብ የተጀመረ ስርአት ብቻ ነው።ቄርሎስ ስድስተኛ ከሞቱ በሁዋላ የግብፃውያን ጭንቀት በመንበረ ማርቆስ ላይ የሚቀመጥ መንበሩን በሞት የሚለቅ፣ ለመንጋው የሚጠነቀቅ ለመንጋው የሚጨነቅ ቅዱስ አባት ማግኘት ነበር ጭንቀታቸው ይልና የሚከተለውን የዕጣ ምርጫ እውነታ አስቀምጦ ሌሎችን ድንበር አፍራሽ የሚል አሳፋሪ ድምዳሜ ያደርጋል።
ይህንን አባት ለማግኘት ግን የተጠቀሙበት የመጀመርያው አማራጭ የአባቶቻቸውን ስርአት ነው (ዕጣ) ።የአባቶቻቸውን የድንበር ምልክት አላፈለሱም። አላፈረሱም ።
በጣይቱ ማእከል 16ኛ አመት ክብረ በአል ላይ ይምስለኛል የእያዩ ፈንገስ ደራሲ ወጣት በረከት በላይነህ ባነበበው ግጥም መጨረሻ ላይ ያለው ማሳረጊያው ትዝ አለኝ
“ጀግና ልጅ አትወልድም አያቶቿን ገላ የምትሸልል ሀገር ።”
ያ ግጥም ስለሃይማኖት ባይሆንም የአባት ካህናትን ስም በዚህ ደረጃ የሃይማኖት የድንበር ምልክት አፍላሽና አፍራሽ ማለት አያቶችን ገሎ ከመሸለል በምን ይለያል ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል።ህዝቅያስ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የራሷ የፓትርያርኮች አሰያየም ስርአት ሊኖራት እንደሚችል የሃገራችንን አባቶች የበጠበጣቸው የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነትና
የምዕምናኑ እነሱን ከመደገፍ አንፃር ያሳየነው ክሽፈት እንጂ ሃገር ውስጥም ሆነ ውጪ በስደት ላይ ያሉ የሃይማኖት አባቶቻችን በቂ ክህሎትና መንፈሳዊነት እንዳላቸው ለሰከንድ ያሰበ አይመስልም።ዋና ግቡ ከግብፆች ቀላውጦ የያዘውን በቤተክርስትያናችን በመጨመር ማህበረ ቅዱሳናዊ ተሃድሶ ማድረግ ስለሆነ።ለምሳሌ የቤተክርስትያናችን ቀኖና አካል የሆነው ፍተሃ ነገስት ውስጥ የሚከተለው የዕጣ ሳይሆን የምርጫ ሃሳብ አለ።
ስለ ሊቃነ ጳጳሳት ቁ 57 የሊቀ ጳጳሳቱ ሹመት ጉባኤ ሳይሆን አይፈፀምም።ስለ ሹመቱ ፣ጠብ ክርክር ቢሆን በድምፅ ብልጫ ያድርጉት።ከዚህም በሁዋላ የሚገባው በላያቸው ይሾም። ቁ 68 መራጮች የዚህች ሹመት ስርአት የምትገኝባቸውን ብዙ ሰዎች ቢያገኙ በስርአትዋ ከነርሱ ፍፁም የሆነውንና ሰዎች ብዙ ጊዜ ፈጥነው የሚታዘዙለትን ሊመርጡት ይገባል።የተመረጠውም እምቢ ብሎ ባይቀበላት ከነርሱ ሌላውን ይምረጡ።
ፍተሃ ነገስቱን የደረሱት ሃዋርያት፣ሰለስቱ ምእትና ከዛም በሁዋላ የነበሩ ታላላቅ የኦርቶዶክሳውያን አባቶች መቼም የሃዋርያት ስራ ምእራፍ 1 ቁ 20 አካባቢ ያለውን ታሪክ ሳይረዱ ቀርተው አይደለም።ታድያ ይህን ሀሁ ያወቀና በሃገራችን የነበሩትን የፓትርያርክ ምርጫዎች በመጠኑም ቢሆን የተረዳ ሁሉንም የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርኮች ፣ጳጳሳትና የቤተክርስትያን የበላይ ጠባቂ የነበሩትን ሃፄ ሃይለ ስላሴን ጨምሮ ፣ዕጣ አልተጠቀሙም ብሎ መክሰስ፣እናስ ሲባል የአባቶች የሃይማኖት ድንበር ምልክት አፍላሽ ናቸው ማለቱ ምራቅን ወደላይ ከመትፋት ሌላ ምን ትርጉም ይኖረዋል።የሰደበው እራሱን ነው የተፋው ምራቅ የራሱ ፊት ላይ ስላረፈ።እለት ተእለት በየአውደ ምህረቱ የሚታየው ብልግናና ጳጳሳትን ማዋረድ የሃሳቡ ምንጭ እንደዚህ አይነት የማህበሩ ካህናትና ተሃድሷዊ ፍልስፍናቸው ነው።
ህዝቅያስ በኛ አብያተ ክርስትያናት ሲቀር ይህ የዕጣ ስርአት በሌሎች አብያተ ክርስትያናት አለ በማለት የተናገረው ምን ያህል አይኑን ያፈጠጠ ሃሰት መሆኑን ለማረጋገጥ የሚከተሉትን የአለም የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት አሰራር በአጭር በአጭሩ እንመልከት።
  1. Armenia (Oriental) – ፓትርያርኩ የሚመረጡት የቤተክርስትያን ተወካዮች በምርጫ ሳጥን በሚስጥር በሚሰ ጡት ድምፅ ነው።The Catholicos is elected for life, by secret ballot, by the National Ecclesiastical Assembly — the highest legislative body of the Armenian Church, made of two-thirds lay representatives of the Armenian nation and one-third clergymen.[11] The representatives to the Assembly are elected by their respective communities.[12] Source http://oxbridgepartners.com/hratch/index.php/publications/book-chapters/55- the-catholicos-and-the-hierarchical-sees-of-the-armenian-church
  2. Syria ( Oriental) ፓትርያርኩ የሚመረጡት የቤተክርስትያን ተወካዮች በምርጫ ሳጥን በሚስጥር በሚሰጡት ድምፅ ነው። On March 31, 2014, Bishop Afrem II Karim was elected as patriarch by the Synod in Lebanon, just three days after the deceased Patriarch Zakka was buried in the Damascus suburb of Sednaya. …The Aramaic faction’s candidate was most likely Bishop Eugene Kaplan of California, but he received half as many votes as Bishop Karim. Source http://www.acsatv.com/?p=2621
    ለሰላሳ አራት አመታት የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ በመሆን ያገለገሉት የቀድሞው ፓትርያርክ ሞራን ኢግናተስ ዛካ ኑዛዜያቸው ጎርጎርዮስ ዮሃና ኢብራሂም ከአይ ሲስ እስር ነጳ ሆነው፣በምትካቸው የቤተክርስትያኗ ፓትርያርክ እንዲሆኑ መሆኑን የቀድሞው የፓትርያርክ ሴክረታሪ Suryoyo SAT ሳተላይት ቴሌቪዥን ቀርቦ መናገሩንም አድምጠናል።
  3. India (Oriental) የህንዶችንና የሶርያውያኖችን ጭቅጭቅ ወደጎን ትተን ፓትርያርኩ የሚመረጡት የቤተክርስትያን ተወካዮች በምርጫ ሳጥን በሚስጥር በሚሰጡት ድምፅ ነው። Catholicos of the East & Malankara Metropolitan is nominated then elected by delegates Source –
http://indiatoday.intoday.in/story/supreme-court-mandated-election-fails-to-resolve- dispute-of-orthodox-syrian-church/1/219995.html 

  1. Romania (Eastern) – ፓትርያርኩ የሚመረጡት የቤተክርስትያን ተወካዮች በምርጫ ሳጥን በሚስጥር በሚሰ ጡት ድምፅ ነው። Each bishop is given a ballot, he “kisses the Holy Gospel, and marks the ballot, with fer of God, the name of the one who he thinks worthy to be elected.” Article 128 , Section 4. … The Patriarch of Romania is the candidate who receives two thirds of the votes cast, if non one is elected on the first ballot a second ballot is taken Source http://www.frpeterpreble.com/2013/03/the-election-of-a-patriarch.html
  2. Russia (Eastern) ፓትርያርኩ የሚመረጡት የቤተክርስትያን ተወካዮች በምርጫ ሳጥን በሚስጥር በሚሰጡት ድምፅ ነው። Russian Orthodox patriarch Chose Metropolitan Kirill of Smolensk and Kaliningrad, received 508 votes in a ballot of the Church Council in Moscow. Source – http://news.bbc.co.uk/2/hi/europe/7852711.stm
  3. Greek (Eastern) – ፓትርያርክ የሚመረጠው ድምፅ በመቁጠር እንጂ በእጣ አይደለም።
    On October 22, 1991 the Holy Synod of the Greek Orthodox Church unanimously chose Patriarch Bartholomew to be the Archbishop of Constantinople- New Rome and Ecumenical Patriarch (Greek Ecumenical Patriarchate of Constantinople – 1st among equals) Source http://www.focolare.org/en/news/2016/11/03/ad-multos-annos- patriarca-bartolomeo/
ግብፆችም ቢሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የምርጫ ስርአቶችን ሲጠቀሙ ኖረዋል። ሲኖዶሳቸው በተለያየ ጊዜ እንደሁኔታው የሚመቸውን የአመራረጥ ቀኖና እያወጣ መጠቀም ይችላል።የኢትዮጵጽያ ሲኖዶስም እንደዚሁ ።ይህ ማናቸውንም የሃይማኖት ድንበር አፍላሽና አፍራሽ ተሃድሶ አያደርጋቸውም።
የሃዋርያት ስራ 1 ቁ 20 ላይ የተገለፁት ዮሴፍና ማትያስ፣ሁለቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀበት እስካረገበት ፣በገባበትና በወጣበት ጊዜ ሁሉ አብረውት የነበሩ፣ሃዋርያት ከሁለቱ ለመምረጥ ወይም ለመለየት የተቸገሩባቸው ስለነበሩ ፣ ለመለየት ፀልየው እጣ ተጠቀሙ ነው የሚለው።እጣ ለመጣል ሲሉ ብቻ ፣ሊወዳደሩ የማይገባቸውን ሁለት ሰዎች አምጥተው አይደለም እጣ የጣሉት።መፅሃፉ ኢዮ 33 14 ላይ እግዚአብሄር በአንድም መንገድ በሌላም ይናገራል ይል አይደል እንዴ ። እንዴት ነው ታድያ ህዝቅያስ መፅሃፍትን ሳያገናዝብ እግዚአብሄርን በሎተሪ ብቻ የሚሰራ፣ የሎተሪ አምላክ ያደረገውና እጣ ያልጣለ ሁሉም የአባቶችን ድንበር አፍላሽ ነው በሚል ደንባራ ትርጓሜ የሃገራችንን ጳጳሳትና ፓትርያርኮቻችንን ተሃድሶ ለማለት የዳዳው ።አባቶቻችን ቃል ይገላል ትርጉም ያድናል ብለው አላስተማሩትም።ይህንንስ የተሳሳተ ጠባብ የመፅሃፍ ቅዱስ ትርጓሜ ይዞ ከማርቲን ሉተር በምን ይለያል። ጠላት ድያቢሎስ ፣የሃሰት አባት፣ መንጋዎቹ፣ምእምናንን ሊበታትንና ከሙሽራዋ ወደ ጋለሞታዋ ቤተክርስትያን ሊያስት መጀመርያ ፍላፃውን የሚያሳርፈው እረኞች የሆኑንን ጳጳሳቶቻችንና ፓትርያርኮቻችን ላይ እንደሆነ እናውቃለን።
ምእምናን ልብ ማለት የሚገባን ሌሎች አብያተ ቤተክርስትያናት ልክ እንደኛው ዕጣ ሳያወጡ ፓትርያርኮች በተለያየ የድምፅ መስጠት ስርአት ይመርጣሉ።ግን እኛ ቤተክርስትያን የሚታየው አይነት የካህናት ብልግናና የአውደ ምህረት ላይ ብጥብጥ አልታየም። ፓትርያርክንና ጳጳሳትን መሳደብና ማዋረድ የማህበረ ቅዱሳኑ ተሃድሶ ዋናው ባህሪ መሆኑን መረዳት የግድ ነው። የማህበሩ ሰዎች እራሳቸው አባቶችን ሳያከብሩ እነሱ ለምን እንደሚከበሩ አዙረው መጠየቅ አለባቸው።በቤተክርስትያናችን በተመሳሳይ ፕሮቴስታንታዊ ተሃድሶ ለማድረግ የሚጥሩም እንዳሉ እናውቃለን።ምንም ቅፅል ስም ይኑራቸው ሁለቱንም አይነት ተሃድሶዎች ነቅተን መዋጋት ይኖርብናል።
መፍትሄው የሃይማኖት አባቶቻችንን በተቻለን ሁሉ መደገፍና ሲኖዶሳችንን ማጠናከር ነው ። ኦርቶዶክስ እምነት ሁሌም ሲኖዶሳዊ ነች።ማንም ማህበር እያቋቋመ አባቶችን ሲገፋ ፣ሲዘልፍና ሲሳደብ ዝም ብለን ማየት የለብንም።ከማህበራዊ ኦርቶዶክስንት ሲኖዶሳዊ ኦርቶዶክስነትን መምረጥ አለብን።ከዛ ውጪ የሃራጥቃ ሃይማኖት ነው።ህዝቅያስ ፊቱን በጨው ታጥቦ ፣ከሃገራችን በስተቀር ፓትርያርክ የሚመረጠው በዕጣ ነው ሲል ከላይ የተቀመጠውን እውነት አጥቶት አይደለም።ምስኪን ምእምናንን በማሳሳት ሃይማኖት ለዋጭ ብሎ የፈረጃቸው ፓትርያርክና ጳጳሳት ላይ ለማዝመት ነው።በተለይ ስደተኛው ሲኖዶስ ስር ያሉ አባቶች ላይ። ምክንያቱም እነዚህ ኢትዮጲያ እንዳለው ሲኖዶስ የመንግስት ጥበቃ አይደረግላቸውምና።ከግብፆች ስርአት ቀላውጦ በማምጣት የሃገራችንን ኦርቶዶክሳዊ ስርአት ለማደስ ወይም ለመቀየር ሲባል ብቻ አባቶቻችንን አስቀድሞ ተሃድሶ ማለት ተራ ብልጠት ነው።
የዚህን ፅሁፍ ሰፊ ማብራርያ ለማንበብ የሚከተለውን ድህረ ገፅ ይጎብኙ። www.eneweyaye.com ሲኖዶስ ሲኖዶስ ሲኖዶስ

No comments:

Post a Comment