- ኹለገብ ሆስፒታሉ፥ የሜዲካል እና የነርሲንግ ዩኒቨርስቲን ያካትታል፤
- ትውፊትን ያንጸባርቃል፤ ሥነ ምኅዳርን የሚጠብቅ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል፤
- ለሕክምና ቱሪዝም ፍሰት አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ የውጭ ምንዛሬ ያድናል፤
- ተግባራዊ እንዲኾን፣ ቅዱስነታቸው፣ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፤
በዚኽም መሠረት፣ እነኚኽን ታላላቅ አገልግሎቶች ከጥንት ጀምሮ ስትፈጽም ኖራለች፡፡ በትምህርት ዘርፍ፥ ፊደል ቀርፃ፣ ቀለም አሽታ፣ ብራና ፍቃ መጻሕፍትን አዘጋጅታ፣ ከፊደል ቆጠራ እስከ ዳዊት ደገማ፣ ከዚያም እስከ ከፍተኛው ትምህርተ ሃይማኖት ያለውን ኹሉ በማስተማር ሰፊ ማኅበራዊ አገልግሎት አበርክታለች፤ እያበረከተችም ትገኛለች፡፡ በጤና ረገድም፣ ሊቃውንቷ ከተለያዩ ዕፀዋት መድኃኒቶችን በመቀመም በሽታን ሲከላከሉ ከመኖራቸው ጋራ በትምህርት፣ በተኣምራትና በመሳሰለው ኹሉ ሀብተ ፈውስ ስታሰጥ ኖራለች፡፡ በምግባረ ሠናይም በኩል፥ በሮቿን፣ ደጀ ሰላሞቿን፥ የድኾችና የችግረኞች መጠጊያ በማድረግ እስከ አኹን ስትረዳ ትገኛለች፤ እየረዳችም ነው፡፡
የቅድስናው በጎ ተግባራት በምእመኖቿና በማኅበረሰቡ እንዲተገበሩ ከማስተማር ጎን ለጎን፣ የተለያዩ ማኅበራዊ ተቋማትን ዘመኑ በሚፈቅደው መሠረት፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ማዕከል በማደራጀትና በማቋቋም፣ በአርኣያነት የሚጠቀሱ ተግባራትን እያከናወነች ኖራለች፡፡ ዛሬም፣ በትምህርት ዘርፍ – ከዐጸደ ሕፃናት እስከ ኮሌጅ፤ በጤና ዘርፍ – ከአነስተኛ ክሊኒክና ላብራቶር እስከ መለስተኛ ሆስፒታልና መድኃኒት ቤቶች፤ በምግባረ ሠናይ ዘርፍ – ከዕለት ደራሽ ርዳታ እስከ ዘላቂ መልሶ ማቋቋም፤ በገጠር ልማት ዘርፍ – ከአነስተኛ የግብርና ልማት እስከ የተቀናጁ ፕሮጀክቶችና ታላላቅ ፕሮግራሞች ድረስ አቅም በፈቀደ መጠን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮዋን በቀጣይነት በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን፣ የልማትና ማኅበራዊ ተልእኮዋን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማከናወን ከመሠረተቻቸው ተቋማት አንዱና ዋነኛው፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ነው፡፡ ኮሚሽኑ፥ የኅብረተሰቡን የልማትና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ በዐዋጅ የተቋቋመው፣ ታኅሣሥ 26 ቀን 1964 ዓ.ም. ሲኾን ከ47 ዓመታት በላይ ዕድሜን አስቆጥሯል፡፡ ኮሚሽኑ፣ ከለጋሾች በሚያገኘው ድጋፍ፣ በየክልሉና በየወረዳው ከሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ከተጠቃሚው ኅብረተሰብ ጋራ እያከናወናቸው ያሉት የልማት ፕሮግራሞችና አሳታፊ እንቅስቃሴዎች፡-
- በተቀናጀ የገጠር ልማት ፕሮግራም፣
- በንጹሕ ውኃ አቅርቦት፣
- የአካባቢ ጽዳትና ንጽሕና አጠባበቅ ፕሮግራም፣
- በኤችአይቪ ክትትል፣ ቁጥጥር የሥነ ተዋልዶና የእናቶች ክብካቤ፣
- በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ድጋፍና ክብካቤ ፕሮግራም፤
ከመንፈሳዊው አገልግሎት ጋራ፦ በትምህርት – የዕውቀት ብርሃን ምንጭ፣ በጤናው – የሕክምና ማዕከል፣ በሥነ ልቡናው – የሕዝቡ መጽናኛ፣ በሥነ ምኅዳሩ – የብዝሐ ሕይወት ጠባቂና በልማቱም እየደገፈች ቀዳሚ ኾና የኖረችው ቤተ ክርስቲያናችን፥ እነኾ አኹን ደግሞ፣ ለሀገራችን ታላቅ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ የኾነ ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላትን፣ ኹለገብ የሕክምና ማዕከል(an outstanding and iconic new Medical Center) በይዞታዋ ላይ ለመገንባት፣ በኮሚሽኑ በኩል ከዓለም አቀፍ ድርጅት ጋራ ስምምነት ላይ መድረሷን፣ ሰንደቅ ጋዜጣ በዛሬ እትሙ ዘግቧል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው ረዴ በስምምነቱ ላይ እንደተናገሩት፥ ቤተ ክርስቲያን፣ “ችግሮችን ለመፍታት፥ በጥናትና ምርምር የታገዙ፣ የቀድሞውን ማዕከል ያደረጉ፣ ሀገር በቀል መሠረት ያላቸው፣ ዘመኑ ያለበትን ኹኔታ ያጤኑ እንደዚኽና መሰል ፕሮጀክቶችንም በቀጣይነት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡”
(ሰንደቅ፤ ፲፫ኛ ዓመት ቁጥር ፮፻፪፤ ረቡዕ፣ መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ “ተዋሕዶ ዲፕሎማቲክ ሜዲካል ሲቲ” የተሰኘ ኹለገብ የሕክምና ማዕከል፣ በ400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚገነባ ያስታወቀ ሲኾን፤ የፕሮጀክት ስምምነቱንም፣ ሌጀንደሪ ሜጋኮርፕ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋራ መፈራረሙን ገለጸ፡፡
ስለ ፕሮጀክቱ ስያሜና ሒደት ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የመግባቢያ ሰነዱን ከድርጅቱ ጋራ ለመፈራረም፣ የተለያዩ የጥናት ሥራዎች መሠራታቸውንና የቦታ መረጣም መካሔዱን ጠቅሰው፤ የፕሮጀክቱ ስያሜም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ባሕርይ በአገናዘበ መልኩ የተሰጠ መኾኑን፣ ስምምነቱ በኮሚሽኑ አዳራሽ በተፈረመበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
በይዘቱ፣ በጠቀሜታውና በፋይናንስ ረገድ ግዙፍና በደረጃውም የዓለም የጤና ድርጅትን መስፈርት በማሟላት ተግባራዊ እንደሚኾን የጠቆሙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው ረዴ፥ በዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ ከሚኾነው ድርጅት ጋራ፣ በመጪው ሚያዝያ ወር የግንባታ ውል ከተፈጸመ በኋላ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጸሎትና ቡራኬ የመሠረት ድንጋዩ እንደሚቀመጥ አስታውቀዋል፡፡
ኹለገብ የሕክምና ማዕከሉ፥ በአዲስ አበባ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ በእንጦጦ ተራራ ላይ በሚገኝ 210ሺሕ ካሬ ሜትር አጠቃላይ ስፋት ባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቦታ ላይ ነው፣ የሚያርፈው፡፡ ከእዚኽም ውስጥ፦ በ67ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ በአንድ ጊዜ 600 ሕሙማንን አስተኝቶ ማከም የሚያስችል ዘመናዊ ሆስፒታል፤ በ28ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ፣ የሜዲካል እና የነርሲንግ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻዎች እንደሚገነቡ፣ ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው አስረድተዋል፤ ድጋፍ ሰጭ ኾነው የሚያገለግሉ፦ የአስተዳደር ሕንጻዎች፣ የውስጥ ለውስጥ መሠረተ ልማቶች፣ የመንገድ፣ የሜካኒካል፣ የአይ.ሲ.ቲ ሥራዎችን እንደሚያጠቃልልም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የሌጀንደሪ ሜጋኮርፕ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው፣ “ሀገሪቱን ከምትወክለው ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ጋራ በትብብር ለመሥራት እዚኽ ደረጃ በመድረሳችን ትልቅ ኩራትና ክብር ይሰማናል፤” ብለዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት እንደሚያካትትና የአካባቢውን የዕፀዋትና ደን ሥነ ምኅዳር የሚጠብቅ ትልቅ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እንደሚኾን አስረድተዋል፡፡
በግንባታው ወቅት በጊዜአዊነት 10ሺሕ800 ለሚኾኑ ሰዎች አዲስ የሥራ ዕድል ሲከፍት፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ፣ ለ5ሺሕ ያህል ባለሞያዎች፣ በቋሚነትና በኮንትራት ተጨማሪ የሥራ መስክ በማስገኘትና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ የራሱ የኾነ ሚና ይኖረዋል፤ በትምህርቱም ዘርፍ፣ በየዓመቱ ለመቶ ያህል የሜዲካልና ከ200 በላይ ለሚኾኑ የነርሲንግ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል በመክፈት ለማኅበረሰቡ የላቀ አገልግሎትና የተሻለ ሕክምና የሚሰጥ የተማረ የሰው ኃይል እንደሚያፈራ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፤ አያይዘውም፣ ሀገሪቱ፣ የሕክምናውን ሞያ ከሥነ ምግባሩ ጋራ የተካኑ ዶክተሮችን እንድታፈራ በማስቻል፣ ለሕክምና ቱሪዝም ፍሰት አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
በመሪ ዕቅዱ መሠረት፥ አምስት የግንባታ ምዕራፎች ያሉት ፕሮጀክቱ፣ የቁፋሮ ሥራው፣ በቀጣዩ ዓመት ኅዳር 2010 ዓ.ም. እንደሚጀመርና በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደታቀደ የተመለከተ ሲኾን፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም፣ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አማካይነት፣ የላቀና ዘመኑን የዋጀ ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላት ተገልጿል፡፡
No comments:
Post a Comment