Thursday, March 30, 2017

የኢትዮጵያዊነት ድምጽ ያስተጋባል #ግርማ_ካሳ




ቴዲ አፍሮን አላውቀዉም ነበር። ከአስራ አራት አመት ስደት በኋላ ወደ አገሬ ተመለስኩ። በ1997 ዓ.ም። መኪናም አልተከራየሁም፤ ታክሲ እየያዝኩ ነበር አዲስ አበባ ዉስጥ የምመላለሰው። ያስተስርያል የሚለው ዘፈን ሚኒባስ ዉስጥ ሲዘፈን ሰማሁ። ከአይኔ እምባ መፍሰሰ ጀመረ። “ይሄ ማን ነው ?” ብዬ ከጎኔ ያለችዋን አንዲት እህት ስጠይቃት “ቴዲ ነዋ” አለችኝ፣ ቴዲ አፍሮን ባለማወቄ በመገረም ቢጤ። ያኔ ከቴዲ አፍሮ ጋር ተዋወቅን።
ክዚያ በኋላ ጥቁር ሰው፣ ሃሌሉያ አበባየሁ(ለአለም) ..ብዙ ጣእመ ዜማዎቹን አደመጥኩኝ። በቀለኞች የሆኑት ሕወሃቶች አስራ ሰባት መርፌ በማለቱ በቂም በቀል፣ ባላጠፋው ጥፋት ለሁለት አመት ወህኒ አወረዱት። እርሱ ግን አልተቀየመም። የአሳሪዎቹና አሰቃዮቹ አለቃ መለስ ዜናዊ ሲሞት፣ የአሰቃዮቹን ስሜት ላለመጉዳት ሲል የሰርግ ቀኑን አራዘመ። መለስ ዜናዊ በመሞቱ፣ ከእጮኛው ጋር ለቅሶ በመድረስ ሃዘኑን ገለጠ። ክፋትን በደግ መመለስ ይሉታል ይሄ ነው።
እነርሱ ግን ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት ፣ ስልጣኔ የማይገባቸው ትንሾች በመሆናቸው አሁንም ውስጣቸው በቀል አለ። ሕወሃቶች ከአክራሪ ኦነጎች ጋር በመሆን ኮንሰርት እንዳያዘጋጅ ሆነ ማድረግ የሚፈለገውን እንዳያደርግ መዶለታቸውን አላቆሙም። እርሱ ግን ቀዳዳ አልከፈተላቸውም። የነርሱን ጥላቻ በፍቅር እየመከተ አሁንም የፍቅርን፣ የአንድነትን የኢትዮጵያዊነትን መልእክት ለማስተላለፍ ተዘጋጅቷል።
በቴዲ አፍሮ ዙሪያ ኤርሚያስ ቶኩማ (Ermias Tokuma) ከጦመረው የተወሰነዉን እንደሚከተለው አስቀምጫለሁ። ኤርሚያ ካለው በተጨማሪ አንድ መጥቀስ የምፈለገው ቴዲ አፍሮ ለልጆቹ መልካም አባት፣ ለባሌበቱም መልካም ባል ነው። ለቤተሰቡ ያልሆነ ለአገር ሊሆን አይችልምና።
==============================
ብዙዎቻችን ቴዲ አፍሮን ከሙዚቃ ሥራውና ከሐገር ወዳድነቱ ባሻገር እምብዛም የግል ሕይወቱን እና ምን አይነት ሰው እንደሆነ አናውቀውም እርሱም ቢሆን ስለራሱ ማውራት ስለማይወድ እና ይህንን ፈፀምኩኝ ብሎ ስለማያወራ የቴዲን ማንነት በግልጽ ልናውቀው አልቻልንም ሆኖም ቴዲ አፍሮ እንደዚህም አይነት ሌላ ገፅታ አለው።
★ ሐምሌ 30,1998 ዓመተ ምሕረት በድሬዳዋ ደርሶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ30 ሺህ ብር ድጋፍ በማድረግ ለወገን ደራሽነቱን አሳየን።
★ ጥቅምት 1,2002 Elshaday relief and development ባዘጋጀውና ከ50 ሺህ በላይ በተገኘበት የአዲስ አበባ ስታዲየሙ ኮንሰርት ከ 1 ሚሊየን ብር በላይ አሰባስቦ ለእርዳታ ድርጅቱ ያስረከበ ሲሆን በእለቱ ለአበበች ጎበና ሕፃናት ማሳደጊያ 100 ሺህ ብር ለይልማ ገ/አብ የወርቅ ብእር ሸልሟል።
★ ጥቅምት 23,2002 በህመም ላይ ትገኝ ለነበረችው ማንአልሞሽ ዲቦ መታከሚያ ይሆን ዘንድ 20 ሺህ ብር አበረከተ
★ ጥቅምት 17,2004 የወጣት አስመሮም ሃይለስላሴን ነፍስ ለማዳን ለሶማሊያ ሽማግሌዎች 700 ሺህ ብር ከፈሎ የወገኑን ህይወት አተረፈ።
★ ጥቅምት 17,2004 ለኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበር የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጎ ለማህበሩ ያለውን አጋርነት አሳየ። ማህበሩም የምስጋና ምስክር ወረቀት ሰጥቶታል።
★ የአራት ኪሎ ወጣቶች ከአልባሌ ሥፍራ ይርቁ ዘንድ በአባቱ ስም ተቋቁሞ ለነበረው የእግር ኳስ ቡድን ለአራት አመታት በየአመቱ ግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
★ በራሱ አነሳሽነት ለአበበ መለሰ ኮንሰርት በማዘጋጀት የአርቲስቱን ህይወት ከህልፈት ታደገ።
★ ጥቅምት 2005 ቀድሞ ይማርበት ለነበረው ቤቲልሄም ት/ቤት የኮምፒውተር እና የሙዚቃ መሣሪያ ድጋፍ አደረገ።
★በተለያየ ግዜያት በተዘጋጁ ዝግጅቶች ላይ እንደዚሁም እዛው ድረስ በመሄድ ለወይዘሮ አበበች ጎበና እፃናት ማሳደግያ ከመቶ ሺ ብር በላይ የገንዘብ እርዳታ።
★ ባለቤቱ አምለሰት ባስመረቀችው አረንጋዴ መሬት ዶክመንተሪ ፊልም ምርቃት ላይ በእንጨት ለቀማ ይተዳደሩ ለነበሩ እናት የ 20ሺብር ቼክ ሰታቸዋል።
★ እንደዚሁም ለተለያዩ ድምፃዊያን ግጥም እና ዜማ በነፃ የሰጣቸውም አሉ::
ይህ ነው የቴዲ አፍሮ ሌላው ገፅታ ይህ ህዝቡ የሚያውቀው ነው ቴዲና ድጋፍ ያደረገላቸው ብቻ የሚያውቁት ብዙ አለ። ቴዲ ከመልካምነቱ በተጨማሪ ጥሩ የፍቅር መምህርም ነው

No comments:

Post a Comment