BBN News | የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ ‹‹አባላቶቼ እና አመራሮቼ ህወሓትን ተጠራጥረውት ነበር›› ሲል ገለጸ፡፡ ድርጅቱ አቋሙን በተነተነበት መጽሔቱ ላይ እንደገለጸው ከሆነ፣ በአማራ ክልል ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ወቅት የድርጅቱ አመራሮች እና አባላቶች የትግራዩን አገዛዝ ህወሓትን በጥርጣሬ ሲመለከቱት ነበር፡፡ የህወሓትን የበላይነት ተሸክመው ከሚኖሩት የኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ብአዴን፣ በዚህ ወር ባሳተመው መፅሔት ላይ ለህወሓት ጥብቅና ሲቆም ተስተውሏል፡፡

‹‹ሌላ ስራ የሌለ ይመስል ትምክህትንና መሰል ኋላቀር አስተሳሰቦችን እያራገቡ መኖርን የመረጡ አመራሮችና አባላት ካሉ፣ በቂ የሀሳብ ትግል ከተካሄደና ይኸው ዝንባሌ የሚቀጥል ከሆነ “መስመርህን ለይ” መባል የለበትም፤ ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡” የሚል ሃሳብ ድርጅቱ ባሳተመው መጽሔት ላይ ሰፍሯል፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የተነሳውን ታላቅ ህዝባዊ ቁጣ ተከትሎ፣ ህወሓት በክልሉ መንግስት አሰራር ጣልቃ ገብቶ፣ እነማን መታሰር እንዳለባቸው እና እነ ማን መገደል እንዳለባቸው ውሳኔ ሲያሳልፍ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ ህወሓት በክልሉ ከመጠን በላይ ጣልቃ ገብቶ የተመለከቱ የብአዴን አመራሮች እና አባላት፣ ህወሓትን በጥርጣሬ ዓይን ተመልክተውት እንደነበር ነው የተጠቆመው፡፡
No comments:
Post a Comment