Sunday, March 12, 2017

በጅማ ዩኒቨርስቲ: በማዕተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋራ የተጋጨው ተማሪ ራሱን አጠፋ፤ መምህሩ ታሰረ፤ “ቤተ ክርስቲያን፥ የእምነት ነጻነታችንን ታስከብርልን”/ተማሪዎቹ/

    



በጅማ ዩኒቨርስቲ: በማዕተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋራ የተጋጨው ተማሪ ራሱን አጠፋ፤ መምህሩ ታሰረ፤
“ቤተ ክርስቲያን፥ የእምነት ነጻነታችንን ታስከብርልን”/ተማሪዎቹ/
  • መምህሩ፣ በተመሳሳይ ጥፋት በተወሰደበት የዲስፕሊን ርምጃ ተባርሮ የተመለሰ ነው፤
  • ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች፣ የእምነት ነጻነታቸው እንዲከበር አቤቱታ አቅርበዋል፤ 
  • “በነጻነት መማር አልቻልንም፤ የእምነት ነጻነታችን ይከበር፤ የሕግ ከለላ ይሰጠን!”
በጅማ ዩኒቨርስቲ መምህራን ኮሌጅ፣ የኹለተኛ ዓመት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተማሪ የነበረው ወጣት፣ በማዕተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋራ ተጋጭቶ የትምህርቱ ውጤት በመበላሸቱ ራሱን አጠፋ፡፡
ተስፋዬ ገመዳ የተባለው ተማሪው፣ የሥነ ልቡና ሳይንስ መምህሩ፣ በቡድን የሰጧቸውን የቤት ሥራ አዘጋጅተው በመድረክ ሊያቀርብ ሲል፣ መምህሩ፥ “በአንገትኽ ላይ ያደረግኽውን ማዕተብ አውልቅ ወይም ሸፍነው፤” ሲሉት ተማሪው፥ “ይኼ የእምነቴ መግለጫ ነው፤ ያዘዙኝን ማድረግ አልችልም፤” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸውና መምህሩም፥ “ያዘዝኩኽን ማድረግ ካልቻልክ የሠራኸውንም ማቅረብ አትችልም፤” ስላሉት ከመድረኩ ወርዶ በእጁ የያዘውን የቡድን ሥራ ሪፖርት በብስጭት ቀድዶ መቀመጡን የዓይን እማኞች አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ ተማሪው፣ ክፍለ ጊዜውን አቋርጦ መውጣቱንና ተመልሶ ሊገባ ሲል፣ መምህሩ፣ አትገባም ብለው እንደከለከሉት፤ ተማሪውም፣ ስሜታዊ ኾኖ ከመምህሩ ጋራ ለጠብ መጋበዙንና ሌሎች ተማሪዎች በመሀል ገብተው እንደገላገሏቸው፤ የኮሌጁ አካዳሚክ ዲን፣ በቦታው ተገኝተው ስለተጠፈረው ችግር ተማሪዎችን በመጠየቅ ጠቡን ማረጋጋታቸውን፣ እማኞቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በሌላ ቀን፣ ተማሪ ተስፋዬ እንደተለመደው፣ የሥነ ልቡና ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ክፍል ሲገባ መምህሩ ከክፍል እንዳስወጡት፣ ለአካዳሚክ ዲኑ አቤቱታ ማቅረቡንና፣ “የትምህርቱ የመጨረሻ ክፍለ ጊዜ ስለኾነ በቃ ተወው፤ በውጤትኽ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም፤” ብለው አረጋግተው እንደሸኙት የተማሪው የቅርብ ጓደኞች ገልጸዋል፡፡
በኋላም ለፈተናው የተቀመጠ ሲኾን፣ የተለጠፈው የፈተና ውጤት ግን “No Grade’’/ምንም ውጤት የለም/ የሚል ስለነበረ፣ ወዲያው በንዴት ወደተከራየበት ቤት በማምራት በግቢው በሚገኝ የማንጎ ዛፍ ላይ ራሱን ሰቅሎ መግደሉን ጓደኞቹ አስረድተዋል፡፡
ፖሊስና የአካባቢው ኅብረተሰብ ከቦታው ደርሰው ከተሰቀለበት ሲያወርዱት፣ ነፍሱ ከሥጋው እንዳልተለየችና ወደ ሆስፒታል ይዘውት በማምራት ላይ ሳሉ ሕይወቱ ማለፉን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ አስከሬኑ፣ ማክሰኞ፣ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. መሸኘቱንና የቀብር ሥነ ሥርዓቱም፣ በትውልድ ስፍራው በሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ደገሞ ወረዳ ከትላንት በስቲያ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስከሬኑን ለቤተ ሰዎቹ ያደረሱት መርማሪ ፖሊስ ዮሐንስ መገርሳ፣ ተማሪው ከመምህሩ ጋራ በመጣላቱ ራሱን እንዳጠፋ ጥርጣሬ መኖሩንና፣ የሆስፒታል የምርመራ ውጤት በመጠበቅ ላይ መኾኑን፤ ጉዳዩም ገና በመጣራት ላይ እንዳለ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
[ተማሪው የደረሰበትን በደል ቀደም ብሎ ለጅማ ሀገረ ስብከትም በማስታወቅ እገዛ ጠይቆ እንደነበር ያወሱ ምንጮች፣ ጽ/ቤቱ ከትላንት በስቲያ ኃሙስ ጀምሮ ጉዳዩን እየተከታተለው መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮችም፣ የሃይማኖት ነጻነታቸው እንዲከበር የሚጠይቅ አቤቱታ ተፈራርመው፣ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አስገብተዋል፤ ለሚመለከታቸው የኮሌጁና የመንግሥት ሓላፊዎችም በየደረጃው እንደሚያደርሱ ተነግሯል፡፡
በአቤቱታቸው፥ ከዚኽም በፊት፣ በአጽዋማት ወቅት ሥርዓተ እምነታቸውን በአግባቡ እንዳይፈጽሙ በሴኩላሪዝምና በአካዳሚክ ነጻነት ስም የተደረገባቸውን አድልዎ በማካተት፥ “በነጻነት መማር አልቻልንም፤ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ነጻነታችንን ታስከብርልን፤ የሕግ ከለላ ይሰጠን፤” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ለሀገረ ስብከቱ የደረሰው አቤቱታ፣ በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አማካይነት፣ ከዞን እስከ ፌዴራል መንግሥት አካላት ድረስ እንደሚቀርብ ተገልጿል፤ የሟች ቤተሰብም በሕግ እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡]
******************
  • አካዳሚክ ዲኑ ግጭቱን ሲያጣሩ፣ መምህሩ፥ ሊደበድበኝ ነው፤ ብሎ ተማሪውን ከሦት ነበር፤ የክፍል ጓደኞቹን ሲጠይቁ ግን፥ ማዕተብኽን ካልበጠስክ፤ ብሎት በዚያ የተነሣ እንደኾነ ተረድተዋል፤ ጥፋቱም የመምህሩ እንደኾነ ነግረውና ይቅርታ ጠይቀው ልጁን አረጋግተውት ነበር፤ ከዚያ በኋላ በነበረ አንድ ክፍለ ጊዜ፣ ውጣ ብሎ እንዳይገባ ሲከለክለውም ለአካዳሚክ ዲኑ አስታውቋል፤ እርሳቸውም፣ ለኮርሱ፥ የመጨረሻ ክፍለ ጊዜ ነው፤ በሚል አባብለውታል፤ ፈተናውን ተፈትኖ ውጤቱን ሲያበላሽበትም ወደ አካዳሚክ ዲኑ ሊያመለክት ሔዶ ነበር፤ አላገኛቸውምና በየአንጻሩ፣ ለመምህሩ በሚታየው የአስተዳደሩ ከልክ ያለፈመለሳለስ ምክንያት ነው የተበሳጨው፤
  • መምህሩ፣ ከዚኽም በፊት በተመሳሳይ የዲስፕሊን ችግር ከማስተማር ሥራው ተባርሮ የነበረ ሲኾን፣ በአንዳንድ ሓላፊዎች ልመና ከተመለሰ ገና አንድ ዓመቱ ነው፤ የአእምሮም እክል እንዳለበት ነው የሚነገረው፤ እብሪትም ይታይበታል፤ የዲኑ ቢሮ ገብቶ ወንበራቸው ላይ ተቀምጦ፣ ጸሐፊዋን፥ “ከዚኽ በኋላ ማንም ሰው እንዳይገባ፤ ዲኑ እኔ ነኝ” የሚልበት ጊዜ አለ፤
  • ተማሪው ራሱን ባጠፋበት ቀን ምሽት፣ መምህሩ በቁጥጥር ሥር ውሎ በእስር ላይ ነው ያለው፤ አስከሬኑ በተሸኘበት ዕለትም፣ በዩኒቨርስቲው በር ላይ ተማሪዎች ቁጣቸውን ሲገልጹ የነበረ ሲኾን፣ ፖሊስ በአስለቃሽ ጢስ በትኗቸዋል፤ ማምሻውንም ከዐሥር የማያንሱቱ ከየዶርሚተራቸው እየተያዙ ተወስደዋል፤
  • ተማሪው ከመሞቱ በፊት ለጓደኞቹ አራት ጊዜ በተከታታይ ደውሎ ነበር፤ ወደሚግባባው ጎረቤት ባለሱቅም ሔዶ ነበር፤ አላገኛቸውም፤ ብሶቱን የሚተነፍስበትና የሚያናግረው ሰው እየፈለገ ነበር፤ በርግጥ፣ የንስሐ አባቱን በዚያኑ ቀን ጠዋት አግኝቷቸው፣ ከመምህሩ ጋራ መጋጨቱን ነግሯቸው፣ እንደ መንፈሳዊ አባት አጽናንተውት ነው ወደ ቅዳሴ የገቡት፤ ከጸሎተ ቅዳሴው ሲወጡ የተረዱት ግን አሳዛኝ ኅልፈቱን ነበር፡፡
  • በጅማ ዩኒቨርስቲ መምህራን ኮሌጅ፣ በእንግሊዝኛ ዲፓርትመንት፣ የኹለተኛ ዓመት ተማሪ የነበረው ተስፋዬ ገመዳ(ወስመ ጥምቀቱ ወልደ ገብርኤል)ከ3.6 በላይ ድምር አጠቃላይ ውጤት ያለው ጎበዝ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ነበር፡፡
(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም.)

No comments:

Post a Comment