በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን ልጆችና እናቶች ምግብ ሲለቅሙና ቆሻሻ ውስጥ ሲኖሩ በቆሻሻ ናዳ ማለቅ እስከማውቀው ድረስ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ እልቂት ነው፡፡ ይህ እልቂትም የሁላችንም የቁም ሞት ነው፡፡ ልጆችና እናቶች ቆሻሻ ሲበሉ በቆሻሻ ናዳ ያለቁት ለማኙ አገዛዝ በእነዚሁ ቆሻሻ በሚበሉት ዜጎች ሥም ሳይታክት እየለመነ በሚረጠበው ገንዘብ ከሆዳም በላጠጎች ጋር እየተሻረከ ውሀና መብራት የሌለው ፎቅ በሚቆልልበት ከተማ ነው፡፡
ባለጠጎች ሆይ! የራሱን ፍላጎት ለማራመድ የዓለም ባንክ ለማኝ ገዥዎችን እየገዛና የናንተን የባለ ጠጎችን ፎቅ እያሳዬ “አድገዋል” እያለ ሲያታልል የገጠጠው አጥንታችንና በቆሻሻ ናዳ ያለቁት ዜጎቻችን ፍትህ ለጠፋባት ምድር ሳይሆን ለሰማዩ እያመለከቱ ነው፡፡ ለናንተ ከፎቅ ለተሰቅላችሁት ባለጠጎችና በቆሻሻ ተመጋቢዎች፣ሶማልያና ሱዳን በሚያልቁት ወታደሮች ሥም በተረጠቡት ልጆቻቸውን በውጪ አገር ዩኑቨርሲቲዎችና ከተማዎች ለሚያንቀባርሩት ለማኝ ገዥዎች ባይታያችሁም ቆሻሻ መመገባችን፣ ቆሻሻ ውስጥ መኖራችን፣ እንጀራ ስንፈልግ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ መታረዳችን፣ ቀይባህርና ሜዲትራንያን መስመጣችን፣ በአረብ አገር እየተዠለጥን መደብደባችን፣ የአፍሪካን ወህኒዎች መሙላታችንና፣ የሚቆጠረው ጎድናችን እንደሚያረጋግጠው ችጋር ፈጅቶናል፡፡ ከነፍሰ-ገዳይ ገዥዎች በመሞዳሞድ የናጠጣችሁ ባለ ጠጎች የሕዝብን ደም እንደ ትኋን እየመጠጣችሁ የቁንጣንን ፌስታ ስታሽካኩ ስንቱ እንደ ቀለም ተመጦ የጠኔ እሽሩሩን ይቆዝማል? ስንቱ ከቆሻሻ ውስጥ ምግብ ሲለቅምና ቆሻሻ ውስጥ ሲያድር አለቀ? የናንተ ልጆች በአውሮጳ፣ አሜሪካና ቻይና በጥጋብ እንደ ፌንጣ ሲፈናጠዙ ስንቱ ህጻናት በጠኔና ጠኔ- ወለድ በሽታዎች ከጎዳና ዳር ሲያቃስት ዋለ?
ሰው በትጋቱና በሥራው ስለሚለያይ ባለ ጠግነትና ድህነት ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ባለ ጠግነት በኢትዮጵያ የሚበቅለው የትጋት፣ የጥበብና የሥራ እርግብ ዘርቶት ሳይሆን የጭካኔ፣ የማጭበርበር፣ የመዋሸት፣ የመክዳትና የመስሎ አዳሪነት ቁራ በትኖት ነው፡፡ ሰነፎች፣ ድልዱሞችና ቀጣፊዎች ባለ ጠጋ ሲሆኑ ትጉኃን፣ ጥበበኞችና እውነተኞች ምንዱብ ድሆች ይሆናሉ፡፡ ይህንን የተገላቢጦሽ የንብረት ሥርጭትም እንኳን ጥበበኛና እውነተኛ ድሆች ዱልዱምና ቀጣፊ ቱጃሮችም ያምናሉ፡፡
በኢትዮጵያ ንብረት ለማካበት ህሊናን እንደ ቅርፊት ገሽልጦና እግዚአብሔርን ክዶ ስስትን እንደ ሞራ መልበስንና ነፍሰ-ገዳይ ማምለክን ይጠይቃል፡፡ ንብረት ማፍራት ለነፍሰ-ገዳይ ጉቦ መነስነስን፣ ቤተሰብንና ጓደኛን አሳልፎ መስጠትን፣ ሁለት እግር አንስቶ ውሸትን ማቡነንን፣ አይንን በጨው ታጥቦ ማጭበርበርን፣ ጥቁር ካባ ደርቦ በአድሎ መፍረድን፣ አይኔን ግንባር ያርገው ብሎ በቅጥፈት መመስከርን፣ እንደ እንጨት ሸብቶ ጭራ መነስነስን፣ ኮፍያን አጥልቆ መነኩሴ መምሰልን፣ መስቀልን ጨብጦ ይሁዳን መሆንን፣ ምሁር ነኝ እያሉ ለድልዱም መታዘዝን፣ ወዳጅ መስሎ ቀርቦ አቃጥሮ ማስገደልን ይጠይቃል፡፡ “ካለእነዚህ ሰይጣናዊ ግብሮች በትጋቴና በሥራዬ ባለጠጋ ሆኛለሁ!” የሚል ቱጃር እስቲ እጁን ያውጣ!
ነፈሰ-ገዳይዎች ሕዝብን ለመግደልና ለመግዛት ባሩድን ይጠቀማሉ፡፡ ባሩዱን የሚተኩስ ካድሬና ሰላይ ለመቅጠርም ገንዘብ ያግበሰብሳሉ፡፡ ገንዘብ የሰይጣን መሳሪያ እንደሆነም ቅዱሱ መጽሐፍ ያስተምራል፡፡ ይህ የሰይጣን መሳሪያ ገንዘብም እሚመጣው ሰራዊታችንን፣ ክብራችንን፣ እርስታችንንና የተፈጥሮ ሐብታችን እንደፈለጉ ከሚጠቀሙትና እጣፈንታችንንም በመወሰን ላይ ካሉት ምዕራባዊና ምስራቃዊ ቅኝ ገዥዎች ነው፡፡ ይህ የቅኝ ገዥዎች ገንዘብ እሚገባውም ከባንዳ ነፈሰ-ገዳይዎች እጅ ነው፡፡ ባንዳ ነፍሰ-ገዳዮችም በዚህ ገንዘብ ሎሌ ባለ ጠጎችን ይፈጥራሉ፡፡ ሎሌ ባለ ጠጎችም የበለጠ ለመክበር ቦንድ፣ በልማት፣ በጫራታና በስጦታ ስም ጉቦ ለነፍሰ -ገዳዮች መልሰው ይሰጣሉ፡፡ በዚህ የቀለበት አዙሪት ገንዘብ ከቅኝ ገዥ ወደ ባንዳ ነፍሰ-ገዳይ ከዚያም ወደ ነፍሰ-ገዳይ አምላኪ ባለ ጠጋ፤ ተመልሶም ወደ ነፈሰ-ገዳይ ገዥ፤ በመጨረሻም ወደ ቅኝ ገዥ ባንኮች ሲሽከረከር የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቆሻሻ ውስጥ ምግብ ሲፈልግ በቆሻሻ ናዳ ያልቃል፤ በርሃብ ተግጦ አጥንቱ ይፈጣል፡፡ የፈጠጠው አጥንቱም ፎቶ እየተነሳ በዓለም ጋዜጦችና መጽሔቶች ይታያል፡፡ ይህንን በጋዜጣና በመጽሔት የሚታይ የገጠጠ አጥንትም ልመና እማይታክታቸው ነፍሰ-ገዳይዎች የገንዘብ መለመኛ አኮፋዳ ያደርጉታል፡፡ ያኮፋዳው ገንዘብ ሲመጣም በተዋቀረው የገንዘብ አዙሪት ቀለበት ይሽከረከራል፡፡ ከገንዘቡ አዙሪት ቀለበት የራቀውና ገንዘብ የተለመነበት የድሃ አጥንት ግን ለቀበርም ሳይበቃ ጆፌ ይግጠዋል፤ የተረፈውንም አውሬ ይቆረጥመዋል፡፡
ሐዋርያው ያዕቆብ ፩፡፱-፲”የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሳር አበባ ያልፋልና፡፡” እንዳለው ሕዝብ አእምሮውንና ሕዋሳቱን ታስሮ በርሃብ ሲረግፍና ሲዋረድ እናንተ በግል አውሮፕላን እየበረራችሁ፣ በአውሮጳና በአሜሪካ እየታከማችሁ፣ በድሃ ቁስል ፎቅ እየሰራችሁ፣ ባማረ አውቶሞቢል እየተመማችሁና በጎዳና አዳሪ እየተፋችሁ በውርደታችሁ ትመካላችሁ፡፡ ሕጻናት ምግብ ከቆሻሻ ሲፈልጉ በቆሻሻ ናዳ እንደ ቅጠል ሲረግፉ እናንተ “ለቦንድ፣ ለጫራታ፣ ለልደት፣ ለሰርግ፣ ለልማት፣ ለልጆቻችሁ መማርያ ወዘተርፈ” እያላችሁ ጉቦ ለነፍሰ-ገዳዮች በመነስነስ በውርደታችሁ ትንደላቀቃላችሁ፡፡ ይህንን የውርደት መንደላቀቅ እግዚአብሔር ስለሚያይ እንደ ሳር አበባም ትረግፋላችሁ፡፡
መስማት ባትፈልጉም አሁንም ሐዋርያው ያዕቆብ በ፭፡፩-፮ ያለውን ላስታውሳችሁ፡፡
ባለ ጠጎች ሆይ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ፡፡ ሐብታችሁ ተበላሽቷል፤ ልብሳችሁም በብል ተበልቷል፡፡ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጓል፡፡ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፡፡ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል፡፡ ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል፡፡ እንሆ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፡፡ ያጫጆችም ድምጽ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቷል፡፡ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፣ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፈር ልባችሁን አወፍራችኋል፡፡ ጻድቁን ኮንናችሁታል፣ ገድላችሁታልም፡፡
አዎ! “የተናገርኩት ከሚጠፋ የወልድኩት ይጥፋ!” እሚል ሕዝብ ህይወቱን፣ ክብሩን፣ መሬቱንና ሌላውንም የተፈጥሮ ሐብቱን በቱጃር ቅኝ ገዥዎች፣ በምታመልኳቸው ባንዳ ነፍሰ-ገዳይዎችና በናንተ ተቅምቶ ይጮኻል፡፡ በተቀማ ሐብት የደነደነው ልባችሁም በገጠሩ፣ በከተማው፣ በትምህርት ቤቱና በመንገዱ የሚያቃስተውን የሕጻናት ጠኔ አልሰማ ብሏል፡፡ የሕጻናት ጠኔ እንቅልፍ ነስቷቸው ለፍትህ እሚታገሉትን አሳስራችሁ ሥራቸውንና ንብረታቸውን ወስዳችኋል፡፡ ከነፈሰ-ገዳዮች እየተሞዳሞዳችሁ አንዳንዶችንም አስገድላችኋል፡፡
ባለ ጠጎች ሆይ! የእናንተ ልጆች በአሜሪካ፣ በአውሮጳና በቻይና ከተሞች ቁንጣንን ሲተፉን ሲያድሩ ምስኪን ህጻናትና እናቶቻቸው ከቆሻሻ ምግብ ሲለቅሙ ረግፈዋል፡፡ የእነዚህ ህጻናትና እናቶች ነፍስ ይጮኻል! ጩኸቱም ወደ ጌታ ፀባዖት ደርሷል፡፡ በምድር ተቀማጣላችኋል፡፡ ከነፍሰ-ገዳዮች ጋር ግብር በልታችኋል፡፡ እንደ ፍሪዳ ልባችሁንም አዎፍራችኋል፡፡ የትጉሁን፣ የጥበበኛውንና የእውነተኛውን ንብረት ቀምታችኋል፡፡ ከነፈሰ-ገዳዮች ጋር በማበር ጻድቁን ኮንናችኋል፣ አስገድላችሁታልም፡፡ ያስገደላችሁንት ደም ጠጥታችኋል፣ ያስራባችሁትን ሥጋም ለብሳችኋል፡፡ ሥጋችሁ ከድሀ የተገሸለጠ ሥጋ፤ ደማችሁ ከሙት የተማገ ደም ነው፡፡ አሜሪካ፣ አውሮጳና ኤሽያ እሚሽቀረቀቱት ልጆቻችሁ ሥጋና ደምም የድሀ ልጆች ሥጋና ደም ነው፡፡ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ፡፡ ሐብታችሁ ተበላሽቷል፤ ልብሳችሁም ብል በልቶታል፡፡ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጓል፡፡ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፡፡ ሥጋችሁም እንደ እሳት ይቃጠላል፡፡
ባለ ጠጎች ሆይ! የግፍ ክምርን ናዳ ፍሩ! ከናዳው እንድትተርፉ እጇን ወደ እግዚአብሔር የዘረጋችውን የኢትዮጵያን ጩኸት ስሙ፡፡ ጆሯችሁን እንደ አኩክ የደፈነውን ስስት መንቅራችሁ የህሊናን ደወልና የርሃብ ጉንፋን የሚስሉትን ወገኖቻችንን አዳምጡ፡፡ የድሀን ሥጋ ለገፈፋችሁት ድሃ፣ የሙትን ደምም ለመጠጣችሁት ሙት መልሱ፡፡ ለለማኝ ነፈሰ-ገዳይ ገዥዎች መስገዱን ተውና ፊታችሁን ወደ ሕዝብና እግዚአብሔር አዙሩ፡፡ ልቡናውን ይስጣችሁ፤ ኢትዮጵያንም እንደገና ቆሻሻ ስትበላ በቆሻሻ ናዳ ከማለቅ ይጠብቃት፡፡ አሜን፡፡
መጋቢት ሁለት ሺህ ዘጠኝ ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment