Monday, October 24, 2016

እዉነት ሁልጊዜም ለተናጋሪው ኩራትን ይሰጣል


እዉነት ሁልጊዜም ለተናጋሪው ኩራትን ይሰጣል Dejenie A. Lakew
አቶ አቻምየለህ ታምሩ ኢሳት ባዘጋቸው የጋራ የሃገር እናድን አላማ ስብሰባ ላይ አማራዉን ወክሎ ያቀረበውን ጽሁፍ ሰማሁ፤ እዉነትን ያዘለ እጅግ በጣም ድንቅ የሆነ ስራ ነው። መሰማት ያለበት ንግግር ነው፤ ለሃገራችን እወነተኛ የሆነ የፖለቲካ መፍትሄ የሚመኝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማዳመጭ የሚገባው ሃቅ ነው፤አማራው በዉሸት ኢትዮጵያ ዉስጥ እጅግ በጣም ተበድሏል፤ተግፍቷል፤ በሞተላት ሃገር፤እንዲገደል ተፈርዶበታል።

ኢትዮጵያን አደጋ ዉስጥ የጣላት ዋናው ነገር ፤ እውነቱን የሚያዉቁ ሰወች ዝም ማለትና ዉሸትን አንግበው ህዝብን በስሜት በመንዳት ዘረፋንና የፖለቲካ አጭበርባሪነትን ዋነኛ የስልጣን መሰላል አድርገው የተነሱ ሰወች ናቸው። ይህ አማራን የመኮነን የስነ ልቦና በሽታ መጠን ከማለፉ የተነሳ፤ አንድ የኦነግ ደጋፊ በዚሁ ተመሳሳይ ስብሰባ ላይ፤ እኔ አማርኛ ቃላቶችን የተማርኩት እየተገረፍኩ ስለሆነ ይቅርታ አድርጉልን ስሳሳት ብሎ አማራዉን ሲከስና የተጨፈነ የአስተሳሰቡን ቆሻሻ ሲያራግፍ ሰምቻለሁ። ልብ በሉ፤ ማን አለ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ ዉስጥ ጥያቄ በትክክል ካልመለሰ ሳይገረፍ የቀረ ተማሪ፤ የቄስ ትምህርትም ይሁን የአስኳላ ትምህርት፤ አማርኛ ይሁን፤ሂሳብ ፤እንግሊዝኛ ይሁን፤ የህብረት ወይም ሳይንስ። እኔ ጎንደር ዉስጥ ሳድግ ተማሪወች ትክክል መልስ ካልሰጡ ዪገረፉ ነበር፤እንዳዉን አንዳንዴ እኛ ተማሪወች ገራፊወች እንሆን ነበር፤ አማራ አካባቢ ያደጉት ልጆች ግን እኔ እንደዚህ ስለሆንኩ ነው የሚል ባህል የላቸዉም ፤ መልስ በትክክል ስላልመለሰኩ መምህሩ ቀጣኝ ነው የሚለው።
እነዋለልኝ መኮነንም የተሳሳቱት እንደዚህ በዉሸት አንድን ወገን የመወንጀል በሽታ ያላቸው ተንኮለኛ ሰወች እንዳሉ ባለመንገዘባቸው ነበር፤ ሁኔታዉን በትክክል ሳያውቁና ሳያጤኑ በስሜት በመነዳት ብቻ፤ አማራ ጨቁኗል የሚለውን የመሰሪወችን የዉሸት ወንጀል አምነው፤ ከወንጀሉ የሌለበትን ንጹሁን የአምሃራን ህዝብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጥቃት ኢላማ እንዲሆንና እንዲሰቃይ ፤እንዲታረድ ፤ እንዲፈናቀልና እንዲዋረድ ከጠላቶቹ ጋር ተስማምተው ፍርድ ያስተላለፉት።
አሁን አቶ አቻምየለህ በተጨባጭ እንዳሳየው፤ ባለፉት ዘመናት የአማራው ህዝብ እንጂ የተጎዳው ሌላው አልነበረም ። አቶ ጁነዲን ሶዶ ያቀረበዉም ክስ፤ዉሸት ከመሆኑም አልፎ ወያኔያዊ ህልሙ ገና እንዳለቀቀው ያሳያል። እኔ የማዉቀው፤ ከኛ 10 ወይም 20 አመት በፊት ከ 9ኛ-12ኛ ክፍል ለመማር ሁሉም ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዉስጥ ያለ ተማሪ ጎንደር ከተማ እየሄደ ነበር ትምህርቱን የሚጨርሰው። አጼ ሃይለሲላሤ ከጎንደር ወይም ከጎጃም ጠቅላይ ግዛቶች ይልቅ በሌላ አለም ያዩአቸው ሃገሮች ይበዛሉ። መንግስቱም ሃይለማሪያምም እንዲሁ። ወያኔና የሱ መሰል ተንኮለኛ ተኩላወች ግን የሚያወሩት ከዉሸት ማሰልጠኛ ተቋማት በከፍተኛ ማእረግ ተክነው የወጡበትን የሃሰት ልብወለድን ሃሽሽ ነው። ይሀንን የሃሰት ሓሽሽ ነው የኦሮሞው፤ የአማራው፤የደቡቡ፤የጋምቤላው፤ ኣፋሩ ወጣት የተረዳውና አሁን ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችን ከልዩነታችን ዪበልጣል፤ አንድ ሆነን የህልዉናችን ማነቆ የሆነዉን ወያኔን እናጥፋ ፤ ኢትዮጵያ ሃገራችን እናድንና፤ በሰላም፤ በኩልነትና በብልጽግና እንኑር ብሎ ደረቱን ለወያኔ ጥይት እየሰጠ ያለው።

No comments:

Post a Comment