Saturday, October 1, 2016

የጎባጣ አሽከር አጎንብሶ ይሄዳል


መርሐጥበብ
ከባህር ዳር
tigist-satenawnews-6
ዲንቢጧ የሕወአት ተላላኪና የተላላው ደርጅት ብአዴን አባል ገነት ገ/እግዚአብሔር ገ/ኢየሱስ
እኔማ ዘንድሮ በግርምት መሞቴ ነው፡፡ የሰው ልጅ በሚያውቀውም ሆነ በማያውቀው እየገባ መዘባረቁ የግርምቴ መነሻ ነው፡፡ የሻይ ማንኪያ ያህል መረጃ ይዞ ጭልፋ ሙሉ ወግ ማውጋት ምን የሚሉት በሽታ ነው፡፡ ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም እንዲሉ በትንሽ ነገር ሲነኩ እንደ ቆሌ ዶሮ መርገፍገፉ የሰሞኑ የአገሪቱ ካብኔ ተብየዎች ባህርይ በመሆኑ ከመደነቅ ይልቅ መገረም ነው የዕለት ቀለቤ፡፡
ሰሞኑን የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ በኃላፊነት የምትመራው ዲንቢጧ የሕወአት ተላላኪና የተላላው ደርጅት ብአዴን አባል ገነት ገ/እግዚአብሔር ገ/ኢየሱስ በምትፈጽመው ድርጊት በመላው አማራ ክልል የሕዝብ ጥላቻ ከማትረፏ በላይ አመኔታ የሌላት ደካማ ፍጡር መሆኗን በምትመራው ተቋምና በተለያዩ መድረኮች ሲነገራት የማትሰማና ከወድቀት የማትማር የባህር ዳር ከተማ ወጣት እያሳደነች የምታሳስርና የምታስገድል እንዲሁም በአማራ ክልል ሕዝብ ስም የምትነግድ ትውልድና ዘመን የማይረሳት ጠላት መሆኗ እየታወቀ የክልሉ መንግስት ቃል አቀባይ ተብየው ንጉሱ ጥላሁን ለክልሉ መንግስት ቃል ማቀበሉን ትቶ ለወ/ሮዋ ጥብቅና መቆሙን በራሱ የማኅበራዊ ድረ ገጽ በለቀቀው መረጃ መታዘብ ችያለሁ፡፡
የጠሉትን ማስጠላት ምን ያደርጋል በሚል ርዕስ የለቀቀው መረጃ “ወ/ሮ ገነት ሙሰኞችን አጥብቃ የምትታገል ምርጥ የሴት አመራር መሆኗን መመስከር እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን በቢሮው ውስጥ ያሉ መሃንዲሶች በአጭር ጊዜ በሙስና ተዘፍቀው ሃብት በማካበት መኪና መግዛት፣ የቤት ባለቤት መሆን እና የቅንጦት ኑሮ ከማንም የኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ለመሆን ሲባል ይህች ሴት የምትጠላውን ኪራይ ሰብሳቢነት ስለሚሰሩ ሴትነቷ ሳይገድባት ትታገላቸዋለች፣ ከስራ ታግዳለች፤ ለአብነት በቅርቡ የኮንትራክተሮችን የደረጃ ማሳደግ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከአንድ ኮንትራክተር እስከ 20 ሽህ ብር በመቀበል ህጉና መመሪያው የሚጠይቀውን መረጃ ሳያሟሉ ደረጃ የማሳደግ ስራ የሰሩ 4 ባለሙያዎችን ማንም ወንድ ያልደፈራቸውን እሷ ከስራ አግዳቸዋለች ታዲያ ይህችን ሴት ከዚህ በላይ ብትባልም አይገርመኝም ነገር ግን ደሃው የአማራ ህዝብ ነገ እለወጣለሁ እያለ የሚከፍለውን ግብር ሙሰኞች ሲዘርፋት ዝም ብዬ አላይም በማለቷ እንድትሸማቀቅ የሚያደርጉ የፌስ ቡክ ጀግኖች የገባችሁም ያልገባችሁም ከዚች ጀግና ሴት ራስ ላይ ብትወርዱ ጥሩ ነው፡፡ ከሚፃፈው ነገር ስነሳም ወ/ሮ ገነት ተወልዳ ያደገችው ባህር ዳር ቀበሌ 11 ሆኖ ሳለ ሌላ ታርጋ በመስጠት በሴትነት አታሸማቋት ኪራይ ሰብሳቢው ትታገልበት ይህ እውነታ ታሪክ ነው፡፡” የሚል ነው፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ዲስኩር ሙሰኞችን አጥብቃ የምትታገል ምርጥ የሴት አመራር መሆኗን መመስከር እፈልጋለሁ ማለቱ “የጎባጣ አሽከር አጎንብሶ ይሄዳል” የሚለውን አባባል ለጽሁፌ በርዕስነት እንድመርጥ አስገደደኝ፡፡ ለምን ቢሉ ከጌታው ከፍ ብሎ ላለመታየትና ጌታውን ላለማሳጣት ነው የሚለው አባባል ትዝ አለኝ፡፡ የንጉሱ ጠበቃነት በመረጃ ያልተደገፈ ነው፡፡
በሶማሌ አንድ አባባል አለ ልንገራችሁ። አባባሏን የሰመኋት ይህን ጦማር ስሞነጫጭር ነው፡፡ አንዲት ሶማሌ ሴት ነበረች። በሶማሌ ባህል ጋብቻ በግልጽ ካልሆነ አይፈጸምም። አንዲት ሶማሌ ከባህሉ ውጭ በድብቅ የወደደችውን ባል አገባች። ሁለቱ ተጋቢዎች  ከጊዜ በኋላ እንናገራለን በሚል ስምምነት የተጋቢ ቤተሰቦች ሳያውቁ አብረው መኖር እንደጀመሩ ባል በድንገት በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያልፋል። ሚስት እንዴት ብላ ታልቅስ፤ ምክንያት አጣች። ‘ባሌ ነበረ’ ብላ ካለቀሰች፣ ሕጋዊ ባል አይደለም፤ ስለዚህ ‘ብልግና ነበር የምትሰሩት፤ መቼ ነው የተጋባችሁት?’ ሊባል ነው። ስለዚህ ልጅቷ ተጨንቃ ዝም አለች። በዚህ አጋጣሚ ከነበራቸው ፍየሎች አንዱ በቀበሮ ተበላና ሞተ የሚባል ወሬ በእረኛው መልዕክት ይደርሳል፡፡ ‘የኛ ፍየል እኮ በቀበሮ ተበላ ይላታል። ሚስቲቱም ምክንያት አግኝታ በዛ አለቀሰች። የልቅሶ ደረጃውን በመገንዘብ ይህን ያዩ አባትም “ልጄ ይሄ ለቅሶ ከፍየል በላይ ነው!” አላት። ይባላል፡፡ የንጉሱ ወግም ከገነት ትግል ጀርባ ያለውን ድርጊት አለመገንዘቡን ያስታውሳል፡፡
በቅድሚያ ገነት ተብየዋን ግለሰብ በሚገባ አያውቃትም፡፡ የቀን እንጂ የሰው ጀግና እንደሌለውና በአንድ ድርጅት መሰባሰብ የግለሰቦች ማንነት መገለጫ እንደማይሆን እንኳን የመንግስት ቃል አቀባይ በሌላም ሙያ የተሰማራ ይዘነጋዋል የሚል ህሳቤ የለኝም፡፡ የንጉሱ ሀሳብ አላዋቂ ሳሚ … ነው የሆነብኝ፡፡
ግለሰቡ በቢሮው ውስጥ ያሉ መሃንዲሶች በአጭር ጊዜ በሙስና ተዘፍቀው ሃብት በማካበት መኪና መግዛት፣ የቤት ባለቤት መሆንና የቅንጦት ኑሮ እየኖሩ ያሉትን ጾታዋ ሳይገድባት ትታገላለች ያለው ሀሳብ ጅምላ አስተያየት በመሆኑ ብዙም ባልቀበለውም ድክመቱንና ሀቁን ጉዳይ ለማሳየት እሻለሁ፡፡ አቶ ንጉሱ ቆርጦ ቀጥል አመለካከትህ ብዙም ርቀት አያስጉዝህም፡፡ የአማራ ክልል አመራር ስሙ በተነሳ ቁጥር የምትሰነዝረው አስተያየት ለስልጣንህ ማቆያ የምትጠቀምበት ስትራቴጂ እንደሆነ ማስረጃ መጥቀስ አያስፈልግም፡፡ የጎንደር ቅዳሜ ገበያ በእሳት ሲጋይ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ላይ ሆነህ በቪኦኤ የአማረኛ ቋንቋ ሬዲዮ ጣቢያ የሰጠኸው መግለጫ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሌለህበትና በማታውቀው ጉዳይ መዘባረቅ በክራሞት የተላበስከው የሙያ ካባ ስለሆነ ብዙም  አይደንቀኝም፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ ግለሰቧ የሰጠኸው አስተያየት ብዕሬን ከወረቀት ጋር እንዳዋድድ አስገደድከኝ፡፡ ምክንያቱም ነገ ደግሞ ሌላ ላለማለትህ ዕምነት ስላጣሁብህ ነው፡፡
በእኛ አገር የጋዜጠኝነት ሙያ  የአንድ ወገን መረጃ ዜና እየሆነ አገር ማመስ ከተጀመረ ሩብ ዓመት እንዳለፈው ላንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆንብኝ፡፡ ሴትየዋ ብቻ የነገረችህን ተቀብለህ በቢሮው ውስጥ ያሉ መሃንዲሶች ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው ማለትህ አዘንኩልህ ይህ ቀን እንዲህ ሆኖ የሚቀር መስሎህ ሁሉንም መሃንዲሶች በኪራይ ሰብሳቢዎች ቅርጫት ማስቀመጥህ ዘንግተኸው እንደሆነ እንጃ እንጂ የኮንስትራክሽን ዘርፉን የሚመራውም ኃላፊ መሃንዲስ ነው፡፡ ዳሩ ከመንግስት ቃል አቀባይ ምን ይጠበቃል፡፡
አቶ ንጉሱ ከሰጠኸው አስተያየት ተነስቼ ለአብነት ብለህ ያቀረብከው ሀሳብ “ጅል አይሙት እንዲያጫውት” የሚያሰኝ ነው፡፡ ቢሮው የኮንትራክተሮችን የደረጃ ማሳደግ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከአንድ ኮንትራክተር እስከ 20 ሺህ ብር በመቀበል ህጉና መመሪያው የሚጠይቀውን መረጃ ሳያሟሉ ደረጃ የማሳደግ ሥራ የሰሩ 4 ባለሙያዎችን ማንም ወንድ ያልደፈራቸውን እሷ ከስራ አግዳቸዋለች ያልከው ጉዳይ ጫፍ ይዘህ መሮጥህን ያሳያል፡፡ በቅድሚያ ምነው ዛሬ ይህን ሀሳብ ይዘህ ወጣህ ጃል? ከነገረ ቀደም በዚህ ዘርፍ ከሥራ የታገደ አይደለም አራት አንድም ባለሙያ የለም፡፡ በሥራ ተቋራጮች የደረጃ ማሳደግ ተግባር ከመመሪያ ውጭ ተደራድረዋል በሚል ተብለው የተጠረጠሩ በተለያየ የሥራ መደብና ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎች ከነበሩበት የሥራ መደብ አንተ እንዳወራኸው ታግደው ሳይሆን በሌላ የሥራ መደብ ተዛውረው እየሠሩ እንዳሉና እስካሁንም የተጠረጠሩበት ጉዳይ አስካሁን ዳር ሳይደርስ ባለሙያዎችም በተመደቡበት የሥራ መደብ እያገለገሉ እንደሚገኙ ልብ ትለው ይገባል፡፡
“ወዳጄ” አለ አጎቴ ታየር ወዳጄ ንጉሱ የወግህን ብዕር አልወደድኩትም፡፡ በደብዛዛ አመለካከት የወጣ ሀሳብ ከማደናቆር ውጭ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ ታዲያ ይህችን ሴት ከዚህ በላይ ብትባልም አይገርመኝም ያልከው ነገር አልገባኝም ለምን አትነግረንም ቃል አቀባይነትህን ዘነጋኸው፡፡
ደሃው የአማራ ህዝብ ነገ እለወጣለሁ እያለ የሚከፍለውን ግብር ሙሰኞች ሲዘርፋት ዝም ብዬ አላይም በማለቷ እንድትሸማቀቅ የሚያደርጉ የፌስ ቡክ ጀግኖች የገባችሁም ያልገባችሁም ከዚች ጀግና ሴት ራስ ላይ ብትወርዱ ጥሩ ነው ያልከው ጉዳይ እጅግ አስጋራሚና እስስታም ባህርይን የሚያንፀባርቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ርካሽ ተወዳጅነት የሚፈጥረው ስሜት በመሆኑ አልተቀየምኩህም፡፡ ግለሰቧ ልውደድህ ብትልህስ በምን ቀልቧ ትወዳሃለች ጊዜውንና ቦታውን ማየት ነው እንጂ፡፡
ካቀረብከው ሀሳብ ሌላው ያስገረመኝ ጉዳይ “…ከሚፃፈው ነገር ስነሳም ወ/ሮ ገነት ተወልዳ ያደገችው ባህር ዳር ቀበሌ 11 ሆኖ ሳለ ሌላ ታርጋ በመስጠት በሴትነት አታሸማቋት ኪራይ ሰብሳቢው ትታገልበት ይህ እውነታ ታሪክ ነው፡፡” ያልከው ነው፡፡ ይህ ሀሳብ ጤንነትህን ሁሉ እንድጠራጠር ነው ያደረገረኸው
በቅድሚያ ምነው ስሟን ብቻ ጠርተህ ተውካት? ብዕርህ የፍርሃት ቀለም ለምን ይተፋል? ሌላው ትውልድ በማን ይገለጻል? በወላጅ ወይስ በቦታ? ደግሞም የግለሰቧን የትውልድ ቦታ ለማወቅ የግል ማኅደሯ ከሚገኝበት ተቋም ፈትሽ፡፡ እያሸማቀቃት እያለው ጾታዋ ሳይሆን ተግባሯ ነውና በመጀመሪያ ኪራይ ሰብሳቢነት ከመታገሏ በፊት ራሷን ከኪራይ ሰብሳቢነት ታጽዳ ያኔ የቃል አቀባይነትህ ተግባር ትፈጽማለህ፡፡ ዘመዴ ጫፍ ይዘህ አትባዝን- አበቃሁ፡፡

No comments:

Post a Comment