Tuesday, October 11, 2016

የኦሮሚያ ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጥሏል


የኦሮሚያ ከተሞች ህዝባዊ እምቢተኝነት በእጅጉ አይሏል፡፡ ትላንትም ሆነ ዛሬ የሚደረጉ ተቃውሞዎች የበረቱ ሲሆን፣ ህወሓትም ተቃውሞዎችን በአጋዚ ወታደሮቹ በኩል ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከአጋዚ ወታደሮች ቁጥጥር እየወጡ መምጣታቸው እጅግ ያሳሰበው ገዥው የህወሓት መንግስት ጀምበር ያዘቀዘቀችበት እንደሚመስል ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ብርቱ ተቃውሞ መካሔዱን የሚገልጹ የዓይን ምስክሮች፣ በተቃውሞ ወቅት በተደረገ ራስን የመከላከል ድርጊት ከአጋዚ ወገን ከ30 በላይ ወታደሮች ሲያልቁ ከታጠቁ አርሶ አደሮች ወገንም የተጎዱ መኖራቸውን ምስክሮቹ ገልጸዋል፡፡ አጋዚዎቹ ተቃውሞ በሌለበት ሁኔታ አስቀድመው ተኩስ የከፈቱ ሲሆን፣ ከተገደሉት ወታደሮች በተጨማሪም የቆሰሉ መኖራቸውንም እነዚሁ የዓይን ምስክሮች አስረድተዋል፡፡
በምስራቅ ሐረርጌ ህዝባዊ ተቃውሞ መኖሩን መረጃዎች ያመለከቱ ሲሆን፣ በስፍራው ያለው የንግድ እንቅስቀሴ እጀግ ተዳክሞ ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን ከስፍራው የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡በምስራቅ አርሲ ዞንም ህዝባዊ ተቃውሞ መኖሩን እማኞች ገልጸዋል፡፡ እንደዚሁም በድሬዳዋ የተቃውሞ መንፈስ ከተማዋን የተቆጣጠራት ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም የአጋዚ ጦር በተለይ ለገሀሬ በሚባለው የከተማዋ ስፍራ መስፈሩን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
በአወዳይ ከተማ ተመሳሳይ ሁኔታ መኖሩን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በርካታ ወታደሮችም በኦራል መኪኖች ተጭነው ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ነዋሪዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ እንደዚሁ በወለጋ ያለው ሁኔታ ካለመረጋጋቱ በተጨማሪ፣ ጋምቤላን ከቄለም ወለጋ ጋር የሚያገናኘው የመኪና መንገድ በህዝቡ መዘጋቱን ተከትሎ አጋዚዎች ማለፊያ ማጣታቸውን የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአዳማ ቱሉ ህዝባዊ ቁጣ መነሳቱን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለከተ ሲሆን፣ በባቱ እና አካባቢው በተነሳው ተቃውሞም ቃድሮ አቦ የተባለ ወጣት በአጋዚዎች መገደሉን ተከትሎ ከተማዋ በከፍተኛ የህዝብ ቁጣ መናጋቷን እማኞች ገልጸዋል፡፡
Image may contain: text and one or more people

No comments:

Post a Comment