Sunday, October 30, 2016

የማለዳ ወግ … በኢትዮጵያ “አትፈርስም ፣ ትፈርሳለች ” መካከል …


የማለዳ ወግ … በኢትዮጵያ “አትፈርስም ፣ ትፈርሳለች ” መካከል …
=========================================
* ከሞት ባናመልጥም ፣ ከሞቱ አሟሟቱ ያማል 🙁
* መብት አስከባሪ ጠባቂ አልባ ዜጎች …
* ለስብዕና ቀናኢ እንሁን
ከቀናት በፊት እዚህ ሳውዲ አረቢያ ጅዳ የደረሰኝ መረጃ ምክንያት ሆኖ ውስጤን አሞኝ ሰንብቷል ። የሀገሬ ሰው ከለንደን የተሰማውን የኦነግ ቀባጣሪ ” ኢትዮጵያ ትፈራርስ ” ቱማታ ተከትሎ ሀገር ወዳዱ ወገን ከአድማስ አድማስ ታውኮ ከርሟል ። እኔም እንደቀረው ወገን በሆነው አዝኘ ” የኢትዮጵያ አትፈርስም ትፈርሳለች ” መረጃ ስመለከትና ስታዘብ ሰንብቻለሁ ። በኢትዮጵያ “አትፈርስም ትፈርሳለች ” መካከል መካከል ከንጉስ ፉአድ ሆስፒታል ኃላፊዎች በኩል በአን ሀገር ወደድ ጥቆማ መሰረት ተጠርቸ ያየሁ፣ የሰማሁትና የተሰጠኝ መረጃ ሰቅጣጭ ነበር ።
በመንግስት እውቅና የኮንትራት ስራ ተብለው ከመጡት መካከል ያልታደሉት በውስጥ ደዌና በአዕምሮ ሁከት ተለክፈው ሲንገላቱ ህክምና በሚያገኙበት የህክምና ማዕከል ከ10 ያላነሱ በጠና ታመው ተኝተዋል ። ሶስት ያህሉ አስሰሚም አያዩም ፣ የቀሩት ከአልጋቸው መንቀሳቀስ አይችሉም ። የሀኪም ቤቱ ኃላፊዎች የመንግስታችሁ ተወካዮች ለህክምና የመጡ ዜጎቻቸውን ጉዳይ አይከታሉም የሚለውን ስሞታ በመረጃ ማስረጃ አቀረቡልኝ ። የተወሰኑትን በየአልጋቸው ሄጅ ስለመለከታቸው የተሰማኝን ሃዘን ብቻ ሳይሆን ባዶነት ነበር …ከቀናት በፊት በጠና ታሞ የጠየቅኩት ወንድም አልጋ በሌላ በሽተኛ ተይዟል ። ይህ ወንድም የት እንደሄደ ጠየቅኩ ፣ አሳዛኙ መርዶ ተነገረኝ 🙁 ወደ ማይቀረው አለም ማሸለቡን መረጃውን ከሚያቀብሉኝ አንዱ ሳውዲ ሀኪም ” እኒህ የምታያቸው እህቶች ዜጎቻችሁ ናቸው ፣ ከምንም በላይ ሰዎች ናቸው ፣ ቤተሰብ አላቸው ፣ ቤተሰቦቻቸው ይፈልጓቸዋልና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የመንግስታችሁ ተወካዮች ለምን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲገናኙ እንዲንቀሳቀሱ አታደርጉም ? ” ብለው አፋጠጡኝ ። መልስ የለኝም 🙁
ጉብኝቴን ሳልከውን ሌላ መረጃ መዥረጥ አድርገው አወጡ ፣ በተለያየ ምክንያት ህይዎታቸው አልፎ በሬሳ ማስቀመጫ ለረዥም ጊዜ የተመጡ የዜጎቻችን ስም አጋሩኝ ። ውስጤ ታመመ 🙁 የማደርገው ባጣ ፣ ለመፍትሔው እጄ አጭር በመሆኑ አዝኘና አፍሬ ለመረጃው አመስግኘ የምችለውን እንደማደርግ ቃል ገብቸ ተለያየን!
በቀጥታ ያመራሁት ወደ ጅዳ ቆንስል መ/ቤት ነው ። የቆንስሉ ግቢ እንደቀድሞው በባለጉዳዮች አልተሞላም ። ቀዝቃዛ እንቅስቃሴውን እያስተዋልኩ ወደ ዲፕሎማቱ ቢሮ አመራሁ ። በቢሮው ኮሪደሮች አንዳንድ ባለ ባለጉዳዮች ፣ የቆንስሉ ቤተኞችና ሰራተኞች ይተላለፋሉ ። ከቤተኞች መካከል በቅርቡ አዲስ ቢሮ የተሰጣቸው የሴቶችን ሊቀ መንበር ተመለከትኳቸው ። ጉዳዬ በአልጋ ላይና በሬሳ ክፍል ውስጥ ስላሉት አብዛኛው እህቶች ጉዳይ ክትትል ማጣራት ቢሆንም በቀደመው የሻከረ ግንኙነት ባላንጣ ስላደረጉኝ እርሳቸውን መጠየቅ ከአንባጓሮ ባለፈ ፋይዳ እንደሌለው ስለተረዳሁ ልጠይቃቸው አልፈቅድኩም። እናም ወደ ሚመለከታቸው ዲፕሎማት ቢሮ አቀናሁ …
ዲፕሎማቱን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ወንድም አገኘኋቸው ፣ ከሰላምታ በኋላ ውይይታችን ጀምርን ። በመጀመሪያ የጠየቅኳቸው በአሁኑ ሰአት በመጠለያው ከርማ ከወር በፊት ወደ ሀኪም ቤት እንድትገባ ስለተደረገው እህትና አሁን ያለችበትን ሁኔታ ማወቅ ስላለማወቃቸው ነበር ። ባለስልጣኑም ሆኑ ረዳታቸው በሆስፒታሉ ዘጠኝ ያህል ታማሚዎች በሆስፒታሉ ስለመኖራቸው መረጃ እንዳላቸው እምጅ የጠቀስኳት እህት ስለመኖሯ መረጃ የላቸውም ። ቀጥዬ ከሆስፒታሉ የተሰጠኝን መረጃ በተለይም ፖስፖርት ኮፒዋንና በቆንስሉ ለአሰሪዋ የተጻፈውን ደብዳቤ አሳየኋቸው ። መረጃው ትክክል መሆኑን ቢያረጋግጡኝም ዜጋዋ በሆስፒታሉ ስለመኖሯ በመዝገናቸው አለመስፈሩን አረጋገጥኩ ። ንዴቴ በፊቴ እየተነበበ ፣ ዝም አልኩ….
ከዚያ አከታትየ የጠየቅኳቸው ሞተው የቤተሰብ አድራሻና ማንነታቸው ባለመታወቁ አፈር መቅመስ ያልቻሉትዜጎች ጉዳይ ነበር ። ለዚህም ሲመልሱ ቤተሰብን ለማፈላለግ ማስታወቂያ እናወጣለን ቤተሰቦችን ማግኘት ከባድ ነው የሚል ምላሽ ሰጡኝ … ባለስልጣኑ ታመው የሚገቡትም ፣ የሚሞቱትም ሳውዲ ቤተሰብ አላቸው ብለው ያምናሉ ። እኔ ግን በዚህ አልስማማም ፣ ታመው ሲጨንቃቸው አምጥተው የጣሉ ሁሉ ቤተሰብ ላይሆኑ ስለሚችሉ ቢያንስ መርዶን ለቤተሰብ ለማርዳትና አፈር እንዲቀምሱ ለማድረግ አድራሻቸው ሀገር ቤት መፈለግ አለበት ባይ ነኝ ፣ ይህ ካልሆነ የፖስፖርት መምጣትን ከማየት ባለፈ ነዋሪው በማይጎበኘው በቆንስሉ ፊስ ቡክ ማስያወቂያ ለጥፎ ቤተሰብ ካላችሁ ሪፖርት አድርጉ ብሎ መናኛ ማስታወቂያ ማፈላለጉ ጠቀሜታው ብዙም እንደማይታየኝ አሳወቅኳቸው ። ደስተኛ አልሆኑም ፣ እኔ ግን ሀሳባቸው አልገባኝም !
በጫወታችን መካከል በጠና ታመው ካንቀላፉት መካከል ልክ የዛሬ ሁለት ሳምንት በአንበቱ ሀገር ቤት ስላሉ ቤተሰቦቹ ፣ ስለ ደጋፊ አልባ ልጆቹና ባለቤቱ አጫውቶኝ የነበረው ወጣት እስከ ወዲያኛው ማሸለቡን ስለተረዳሁት ወንድም መረጃ ጠየቅኩ ። ስለ ወጣቱ አትራፊ አጉዳይ ወጣት አባወራ መረጃው ያላቸው የጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች የዚህን ወንድም መርዶ ለቤተሰቦቹ አሳውቀው አፈር እንዲቀምስ የማድረጉን ሂደት አለመጀመራቸውን ግን ተረዳሁ 🙁
እኔ ሞቅ ባለ የያገባኛል ስሜት ፣ ባከስልጣኑ ” ለመፍትሔው ሁሉም ዜጋ መረባረብ አለበት ፣ መንግስት በጀት የለውም! ” በሚል ድፍን ምክንያት ውይይታችን ቀጠለ … እኛ እንደ ዜጋ መረጃ እናቀብላለን የሚቻለውን እናደርጋለን ፣ እናንተ ደግሞ አንድም እንደ ዜጋ ፣ ከፍ ሲል እንደ ከባድ የሀገር ኃላፊነት ፣ ከዚያም ወረድ ሲል ስለምትለፈሉበት ደመወዝ ስትሉ በማስተባበርና ለዜጎች መብት ልትቆሙ ይገባል ፣ ስል የሰጠኋቸው አስተያየት ዲፕሎማቱን ቱግ አደረጋቸው ! በውይይታን ብዙም አልቀጠለም ፣ ጥያቄ ለመጠየቅ ሳኮበኩም ያለወትሯቸው ያልተመቸኋቸው ዲፕሎማት ቆጣ ብለው ” አቶ ነቢዩ ጨረስን ይመስለኛል? ” አሉኝ … ጥቁት አተኩሬ አየኋቸውና መጨረሴን ገልጨላቸው እንደ ታመምኩ ቆዝሜ ከዚያ የሹሞች ቢሮ ወጣሁ … !
በሴቶች ስም ተመስርቶ ፖለቲካ የሚቆመርበትን የሴቶች ማህበር ሊቀ መንበር ቢሮ በአሻጋሪ ፣ ሊቀ መንበሯን በኮሪደሪ ሲውረገረጉ አየኋቸውና ሀዘኔ ተጨማምሮ ከራሴ ጋር እያወጋሁ ግቢውን ለቅቄ ወጣሁ 🙁
በበሽታ ተቀስፈው ፣ ተስፋ ቆርጠው ጨንቆ ጨልሞባቸው አልጋ ላይ ተጋድመው ያየኋቸው ዜጎች ባይኔ ውልብ አሉ ፣ ሰው ከሞት ባናመልጥም ፣ ከሞቱ አሟሟቱ እንዲሉ ማንነታቸው ሳይታወቅ ፣ ቤተሰብ መርዶ ሳይሰማ ወደ መቃብር ሊሸኙ የሚችሉትን ግፉአን እያሰብኩ በእኒህ የሆነው በእራሴ ቤተሰብ ቢሆንስ ? ብሎ የሚያስብ ጠፍቷል 🙁 ይህን ካየሁ ቀን ጀምሮ ለማትፈርሰው ኢትዮጵያ ትፈርሳለች አልፈርስም ብሎ መጦመር ለእኔ የፊዝ ነበር !
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ጥቅምት 19 ቀን 2009 ዓም
Nebiyu Sirak's photo.
Nebiyu Sirak's photo.

No comments:

Post a Comment