Friday, October 14, 2016

ከአሸናፊዎች መዳፍ -ወደ- የተሸናፊዎች ወገብ (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት )


ከአሸናፊዎች መዳፍ -ወደ- የተሸናፊዎች ወገብ
በዲ/ን ዳንኤል ክብረት
‹ሰላም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ አትገኝም› የሚል ወርቃማ አባባል አላቸው የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች (First Nations)፡፡ አደን ልዩ ችሎታቸው የነበረውና በዚህች ሀገር ከሺ ዓመታት በፊት ሠፍረው መኖር የጀመሩት እነዚህ ሕዝቦች አያሌ የእርስ በርስ ጦርነቶችንና ችግሮችን ለመፍታት የቻሉት በዚህ ምክንያት እንደነበረ ይነገራል፡:
ሁለት ጎሳዎች በአደንና በእርሻ ቦታ ወይም በድንበር ምክንያት በተፈጠረ ችግር ወደ ጦርነት ይገባሉ፡፡ የእነዚህ ጥንታውያን ሕዝቦች ሽማግሌዎች ግን ጦርነቱ በአንደኛው አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አይፈቅዱም፡፡ ጦርነቱ ሲደረግ የተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የሚታገሡት፡፡ የዚህን ምክንያቱን ሲያስረዱ ደግሞ ‹ሁለቱም ወገኖች የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ መቅመስ አለባቸው› ይላሉ፡፡ የችግር መፍቻው መንገዳቸው ወደ ባሰ ችግር እየወሰዳቸው መሆኑን ከምክርና ከትምህርት ይልቅ በተግባር እንዲያዩት ጊዜ ይሰጧቸዋል፡፡
በኋላ ግን በመካከል ይገባሉ፡፡ ‹ጦርነቱ በአንደኛው ወገን አሸናፊነት መጠናቀቅ የለበትም› የሚል እምነት አላቸው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ቀን ጣላቸው፤ ችግር ለያያቸው፤ መንገድ አጣላቸው እንጂ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ የእነዚህ ወንድማማቾች ትግል በአንደኛው አሸናፊነት ከተጠናቀቀ ሰላም አይገኝም፡፡ አሸናፊው ጨቋኝ፣ በቀለኛ፣ ጉልበተኛና ዘራፊ ሆኖ ይቀራል፡፡ ተሸናፊው ደግሞ ቂመኛ፣ ቀን ጠባቂ፣ በጥላቻ የተሞላና ባዕድ ሆኖ ይኖራል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ ቦታ መቀያየራቸው አይቀርም፡፡ የሕዝቡም ችግር ይቀጥላል፡፡
ለካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች መፍትሔው አንድ አሸናፊ መፍጠር ሳይሆን ሁለት ተሸናፊ ማግኘት ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ጦራቸውን መሬት ተክለው፤ እግራቸውን አጣጥፈው፣ ምንጣፍም ላይ ተቀምጠው መነጋገርና መደራደር አለባቸው፡፡ እስኪስማሙ ድረስ መነጋገር፤ እስኪግባቡ ድረስ መደራደር፡፡ ሲያቅታቸው በሽማግሌዎቹ እየታገዙ ወደ አንድ የመግባቢያ ሐሳብ መምጣት፡፡ ያን ጊዜ ሁለቱም ወገኖች ከሁለቱም ለተሻለ ሉዐላዊ ሐሳብ ተሸናፊ ሆነው ይወጣሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹ሰላም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ አትወጣም› የሚሉት፡፡ ‹የተሸናፊዎች ወገብ› ሲሉ በባሕላቸው ስምምነቱ የሚፈጠረው ከወገብ ጎንበስ ብሎ በትኅትና የመጨረሻውን ሐሳብ በመቀበል ስለሆነ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ መምጣት አይችልም፡፡ ሁሉም ወገን ለዚህች ሀገር የተሻለውን ሐሳብ ለማምጣትና በዚያም ለመመራት ወገቡን መስበር አለበት እንጂ የእርሱን ሐሳብ በሌሎች ላይ በአሸናፊነት ጭኖ ማለፍ የለበትም፡፡ ካለፈው ታሪካችን ይህን መማር አያቅተንም፡፡ የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች እንዳሉት በኛም ሀገር የአንድ ወገን አሸናፊነት አሸናፊውን ጨቋኝ፣ በቀለኛ፣ ጉልበተኛና ዘራፊ ሆኖ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ ተሸናፊውን ደግሞ ቂመኛ፣ ቀን ጠባቂ፣ በጥላቻ የተሞላና ባዕድ ሆኖ በየዘመናቱ የራሱን ጥያቄና የራሱን የነጻነት ትግል እንዲጀምር በር ከፍቶለታል፡፡ ምጣድ ላይ ጢቢኛ ተጋግሮ ላይኛው የዳቦው ክፍል ታችኛውን በእሳት በመለብለቡ ሲስቅበት ‹የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ስትገለበጥ ትቀምሰዋለህ› አለው ይባላል፡፡
ተጋድሏችንና ጥረታችን እገሌን አስወግደን፣ በእገሌ መቃብር ላይ ሐውልት ለመሥራት፤ አንዱን በሌላኛው ለመተካት፤ ከአንደኛው አገዛዝ ወደሌላኛው ለመሸጋገር ከሆነ በላሸቀ ጎማ በዳገት ጭቃ ላይ እንደመንዳት ይቆጠራል፡፡ ጎማው በተሽከረከረ ቁጥር ጭቃው እያንዳለጠው መኪናውን ወደኋላ እንጂ ወደፊት አይወስደውም፡፡ አሁንም ይቅደምና ይውደም የትግላችን መፈክር ከሆኑ ያለፉት ዘመናት ትግሎቻችን ካመጡልን ለውጥ የተሻለ አናመጣም፡፡ አሁንም ‹እኛ› እና ‹እናንተ› እየተባባልን አንዱ ለሌላው መብት ሰጭ፣ ዋስትና ሰጭ፣ ምሕረት ሰጭ ሆኖ ከቀረበ ሥጋት እንጂ ሰላምን ማምጣት አይቻልም፡፡
ጉዞው አንድ አሸናፊ ወገንን ከፈጠረ ጊዜ የሚያፈነዳውን ፈንጂ የመቅበር ሥነ ሥርዓት ይሆናል፡፡ ጉዞው አሸናፊ ሐሳብን ከፈጠረ ግን የፈንጂ ማምከኛ እንደመሥራት ይቆጠራል፡፡ የምንጋደለው ሁላችንም ወደ ውይይቱና ድርድሩ አዳራሽ ለመግባት እንድንችል፤ የሁላችንም ሐሳብ የሚፋጭበትና የተሻለው ሐሳብ አሸናፊ የሚሆንበትን ሥርዓት ለመዘርጋት እንድንበቃ፤ ከጭንቅላታቸው ይልቅ በጡንቻቸው፣ ከሐሳባቸው ይልቅ በመሣሪያቸው የሚተማመኑት ወገኖች ተሸንፈው ወደ ተሸናፊዎች መድረክ እንዲመጡ ለማድረግ ከሆነ ትግሉ ፈዋሽ ነው፡፡
በአፍሪካችን ታሪክ ውስጥ አስቸጋሪው ምዕራፍ በጦርነት ያሸነፉ ኃይሎች የአሸናፊነት ልምድ ብቻ ስለሚኖራቸው ሰላም የምትፈልገውን የተሸናፊነት ባሕርይ ለመያዝ አለመቻላቸው ነው፡፡ በናይጄርያ የሚኖሩ ዮሩባዎች ‹ከበሮን እንዲመታ አድርጎ መሥራትና ከበሮን ለኢሻይ ኦ ሉዋህ መምታት ይለያያሉ› የሚል አባባል አላቸው፡፡ [ኢ ሻ ኦሉዋህ – ‹የእግዚአብሔር ሥራ ሳይፈጸም አይቀርም› የሚል የዩሩባ ባሕላዊ ዘፈን ነው] ነጻነትን ማምጣትና በነጻነት የምትኖርን ሀገር መገንባት የተለያዩ መንገዶችንና ችሎታዎችን ይጠይቃሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ተዋጊዎች ከሰሜን ሱዳን ነጻ የሆነች ሀገር በዘመናት ትግል ፈጠሩ፡፡ በሰላምና በነጻነት የምትጓዝ ሀገር መፍጠር ግን አቃታቸው፡፡ ሰላም ከአሸናፊዎች መዳፍ ልትወጣ አትችልምና፡፡ ከአሸናፊዎች መዳፍ የምትወጣ ሰላም ሰላማዊነቷ ለአሸናፊዎቹ ብቻ ነው፡፡ ተሸናፊዎቹ ምንጊዜም በጦርነት ሥነ ልቡና ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡
የምንታገለው ለመሸነፍ መሆን አለበት፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ የመጨረሻዎቹ ዘመናት የአፓርታይድ መሪዎች ለድርድር ሲጋብዙት ፈቃደኛ በመሆኑ ከሌሎች የኤ ኤን ሲ መሪዎች ክርክር ገጥሞት ነበር፡፡ የአፓርታይድን ፍጻሜ ‹በፈረስ አንገት፣ በጦር አንደበት› ማምጣት ስንችልና ሲገባን ለምን? የሚል ሙግት፡፡ የማንዴላ መልስ የተለየ ነበር፡፡ ‹የታገልነው በሁላችንም ፍላጎት ላይና በሁላችንም ድርድር የምትገነባ ደቡብ አፍሪካን ለማምጣት እንጂ የአንድ ወገን የነበረችውን ሀገር የሌላ ወገን ለማድረግ አይደለም፡፡ የሁላችንም የምትሆነውን ሀገር ሁላችንም እንድንፈጥራት ለማድረግ ነው› ነበር ያለው፡፡
ትግሉ ተሸናፊዎች ወደሚገቡበት አዳራሽ ለመግባት ማንም በማንም ላይ በሩን እንዳይዘጋ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም ወገቡን እንጂ መዳፉን ይዞ እንዳይመጣ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ መዳፍ የጨበጡትን አላቅቆ ወገብ እንዲይዙ ለማስቻል መሆን አለበት፡፡ ዮሐንስ ሐፂር ‹አንተ ስትገባ እርሱ ወጣ› እንዳለው አንዱ ሲገባ የሚወጣ ሌላ መኖር የለበትም፡፡ ሁሉም በገቢ ደረሰኝ የሚመዘገብበትን አካውንት ነው መክፈት ያለብን፡፡
የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች ‹የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ መቅመስ አለባቸው› ካሉት በላይ በአንድ ወገን አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ትግልና አብዮት የሚያስከትለውን ጣጣ በሚገባ ቀምሰነዋል፡፡ ዩሩባዎች ‹የፀሐይ መጥለቂያ የጨረቃ መውጫ ነው› እንደሚሉት የአንዱ ወገን ትግል መጨረሻ ለሌላው ወገን የትግል መጀመሪያ እየሆነ ስንገላበጥ ኖረናል፡፡ የሺ ዓመታት ታሪክ አለን የምንል ሕዝቦች ስንት ጊዜ የነጻነት ቀን፣ ስንት ጊዜ የሕዝብ መዝሙር፣ ስንት ጊዜ የባንዴራ ዓርማ፣ ስንት ጊዜ ሕገ መንግሥት፣ ስንት ጊዜ የየአካባቢዎቻችንን ስያሜ እንደቀያየርን እናውቀዋለን፡፡
አንድ ጊዜ አንዱ ባላባት በሌላው ባላባት ርስት ይሾምና ይሄዳል፡፡የተሾመው ባላባት ግብር አውጥቶ ሕዝብ ይጋብዛል፡፡ በዚያ ግብር ላይ የተሿሚው ወገኖች ‹ዓይናማው ገዳየ› እያሉ ሲዘፍኑ የተሸናፊው ወገኖች ‹አሃው ገዳይ› በማለት ፋንታ ‹አለን ጉዳይ› ይሉ ነበር አሉ፡፡ ልባቸው እንደሸፈተ ሲናገሩ፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዞም ‹ዓይናማው ገዳይ› ብሎ አንዱ ሲዘፍን ሌላው ‹አለን ጉዳይ› የማይልበትን ሥርዓት ለመዘርጋት መሆን አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የአሸናፊነት መዳፋችንን አላቅቀን የተሸናፊነትን ወገብ ይዘን ወደ ውይይቱ አዳራሽ በነጻነት ከገባን ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ከአሸናፊዎች መዳፍ ሳይሆን ከተሸናፊዎች ወገብ መገኘት አለባት፡፡
አርኅው ኆኃተ መኳንንተ፡፡

No comments:

Post a Comment