ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዘውገኝነትንና[1] የዓለም-አቀፍነትን ያስተዳደር ርእዮተ ዓለም የሚያራምዱ አንጃዎች ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች መታጐርያ እስር ቤት ናት እያሉ የሚሰብኩት ስብከት ተደማጭነትን ከማግኘት አልፎ፣ ብዙዎችን አገርወዳዶች ሳይቀሩ ጭምር፣ እያወነበደም እየማረከም ነው። የሰባኪዎቹ አቋም የግል ጥቅማቸውን የማራመድ ዕቅድ ካላቸው ይጠቅማቸው ይሆናል እንጂ፣ በኢትዮጵያ ታሪክና በየጊዜው በተፈጸሙት ተጨባጭ የመንግሥት ተግባራትና መመርያዎች አይደገፍም። ለዘመናት በየጊዜው የተነሡት የርስ በርስ ጦርነቶችና የሕዝብ ፍልሰቶች፣ የሃይማኖቶች መስፋፋትና እነዚህም ድርጊቶትች ያስከተሏቸው ግጭቶች፣ በተለያየ ጊዜ የማዕከላዊ መንግሥት መፍረስና መልሶ መቋቋም፣ በብዙ መልክ አገሪቷን የጐዱ ቢሆኑም፣ በሌላው አኳያ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማቀራረብ አልፈው አዋህደዉታል። እነዚህ ክሥተቶች ከንግድ፣ የእምነት ማዕከላትን ለመሳለም በየጊዜው ከሚደረጉት የምዕመናን ንግደቶችና ከጋብቻ ጋር ሁነው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በታሪክ፣ በደም፣ በቋንቋ፣ በባህል አስተሳስረው እንደሰርገኛ ጤፍ ስለደበላለቁት፣ በዘሩ ጭንጩ የሆነ ዘውግ በርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ማለት እንደዘበት መቈጠር ይኖርበታል። እውነት ነው እያንዳንዱ ዘውግ ራሱን የሚገልጥበት የተለየ የአካባቢው ቋንቋ አለው። ቢኖረውም ግን ተናጋሪው ሕዝብ ካንድ እንጅላት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሁሉም ለሚኖርበት መጤ፣ አለበለዚያም ከሌላ አገር ከፈለሰ መጤ ጋር የተቀላቀለና የተዋሐደ ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላላ ሲታይ፣ አንዱ የሌላው የሥጋው ቊራጭ፣ የደሙ ፈሳሽ ነው ቢባል መቼም በምንም መልክ የማይካድ ሐቅ ነው።
አገሩን የገዛው እያንዳንዱ ተከታታይ ሥርወ መንግሥት የአገሪቷ የመሬት ቈዳ ይጥበብም ይስፋም ሕዝቧን በነፃነት፣ ለማንም ሳያደላ የበላይነትና የበታችነት ስሜት ሳያሳይ በእኩልነት አስተዳደሯል። ከዚያም ሕዝቡ ራሱ ከነጋሹም ክፍል ጋር ሆነ፣ እርስ በርሱ በመጋባትና በመወላለድ ተደባልቆ ተዋሀዷል። ከዚያም አልፎ፣ አንድ የኢትዮጵያውያን የጋርዮሽ ሀብት የሚያሰኝ የራሱን ቋንቋ ለመፍጠር ችሏል። ከነዚህም እሴቶች የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማንም የአፍሪቃ ሕዝብ በላይ የሥነ-ልቡና ኩራትና ከማንአንሼነት መንፈስ ለማዳበር በቅቷል። በዘመናዊ መልክም የተቋቋመችው ኢትዮጵያ ለሁሉም ሕዝቧ የነጻነትና የእኩልነት ማኅደር እንጂ የማንም እስርቤት አልነበረችም። ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔረሰብም ታይቶባት አይታወቅም ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ ከሌላው የዓለም አህጉራትና ሕዝብ በተለይም ከአፍሪቃዎቹ የምትለይበት አያሌ መሠረታዊ እውነቶች አሉ። አንደኛ፣ አብዛኛው፣ (እውነቱን ለመናገር ሁሉም ማለት ይቀላል) የዛሬ የአፍሪቃ አገሮችና መንግሥታት ህልውናቸውንና ምንነታቸውን ያገኙት በውጭ አገር መጤዎች ሲሆን፣ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አላንዳች የውጭ እርዳታ ባገሩ ተወላጆች እጅ የተገነቡ ናቸው። የአክሱም ሐውልቶችና ቤተመንግሥቶች፣ እንዲሁም በየጊዜው የተሠሩ ሕንጻዎች፣ የአሁኗ መናገሻዋ አዲስ አበባ፣ ሌሎችም ከተሞችና የግል ሕንጻዎች የታነጹት በራሳቸው በኢትዮጵያውያን እንጂ ከውጭ መጥተው አገሪቷን በያዙ ኀይሎች አይደሉም[2]። ይኸም ማለት የውጭ አገር ሰዎች በሠራተኛነት አልተቀጠሩም አይባልም። ከመሐንዲሶች እስከተራ ሠራተኞች ባገሪቷ ውስጥ ተቀጥረው ሠርተዋል።
ይልቅስ ይኸ ራሱ ማለትም ምዕራባውያንንና የሌላውን አገር ዜጋ ቀጥሮ ማሠራት፣ አንድ ራሱን የቻለ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መለዮ ነው ማለት ይቻላል። ያፍሪቃ አገሮች ነጻነታቸውን እስካገኙበት ጊዜ ድረስ፣ መጤዎቹ የውጭ አገር ሰዎች [ምዕራባውያኑም ሆኑ እስያዉያኑ] ባገሩ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የገዢና ያስተዳዳሪ አለበለዚያም የከበርቴ ክፍል ሁነው ነበር። በነዚህ አገሮች፣ ፈረንጆችን በአዛዥነት ቦታ እንጂ፣ ባገሩ ተወላጅ ሲታዘዙ ማየት ድንቅ ግሩም ስለነበር አይታሰብም፣ አይታለምም ማለቱ ይቀላል። ያገሩ ተወላጅ የተመደበው፣ የጊዜውን አነጋገር ብንጠቀም፣ ለውሃ ቀጂነት፣ ለዕንጨት ለቃሚነትና ፈላጭነት ብቻ ነበር ማለት ይቻላል። በኢትዮጵያ ግን ፈረንጅ በታዛዥነት እንጂ በአዛዥነት ቦታ ታይቶ አይታወቅም ቢባል ሐሰት አይደለም። ስለዚህም ባንድ የአፍሪቃ ክፍል በሆነ አገር ውስጥ ይኸ የሥልጣን ተገላቢጦሽ መፈጠሩ፣ አገሩን የጐበኙትን ፈረንጆች በጣም እንዳደናገራቸው ግልጽ ነበር። ጆን ቦይስ የተባለ እንግሊዛዊ ከእንግሊዝ ምሥራቅ አፍሪቃ (ማለትም ከዛሬዋ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛንያ) ወደአዲስ አበባ እንደደረሰ፣ በጣም እንግዳ የሆነብኝ ነገር ቢኖር፣ “አንድ አፍሪቃዊ [ማለትም ጥቊር] የሆነ ሰው ቤቱን እያነፀለት ያለውን ነጩን ሲያዘው” ማየቴ ነበር ይላል። ከአክሱም ሐውልት ጀምሮ አገሪቷን ሆነ፣ የአገሪቷንም ታሪክ ሠሪዎችና ገንቢዎች ኢትዮጵያኑ ራሳቸው ናቸው። ይኸ አባባል በዘመነ መሳፍንት ፈርሳ እንደገና በዘመናዊ መልክ የተገነባችውን የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከገናናው ከአክሱም መንግሥት እስከዘመነ መሳፍንት ድረስ የነበረውን መላውን ያገሩን ታሪክ ሁናቴ ጭምር ይመለከታል።
በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ግንባታና ታሪክ ካንድ ዘውግ ወይንም ካንድ አካባቢ በተወጣጡ ሰዎች የተካሄደ ሳይሆን ከብዙ ነገድና አካባቢ የመጣ ሕዝብ ድርጊት ነው። ታሪኩን በአክሱም መንግሥት ከጀመርን፣ አንደኛ አክሱም የኢትዮጵያ ክፍል መሆኗ በጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ልክ ሮም የተባለችው ከተማ ከኢምንትነት ተነሥታ የመላው የኢጣልያን ባሕረገብ ምድር የበላይ ሁና እንደተቈጣጠረች ሁሉ፣ አክሱምም በጊዜዋ ከከተማነት አልፋ፣ አብዛኛውን የዛሬዎቹን የኢትዮጵያን ግዛቶች እስከሱማሌ፣ ከዚያም ቀይ ባሕር አልፋ የመንንና ደቡብ ዐረብን፣ በሰሜን ደግሞ እስከግብፅ ወሰን ድረስ ትገዛ እንደነበር የአዱሊስ ዙፋን በሚል ሐውልት ላይ የተቀረፀው ጽሁፍ ይገልጥልናል[3]። ልክ ሮም የሮማዉያን መንግሥት መናገሻ ከተማ እንደነበረች ሁሉ፣ አክሱምም በስሟ የሚጠራው መንግሥት ዋናው ከተማ ስም ነበረች[4]።
የአክሱም ሥልጣኔና ግዛት የሚነግሩን ግልጥ ነገር ቢኖር በመንግሥታቸው ሥር የነበሩት ነዋሪዎች፣ ልክ እንደሮማው መንግሥት በቋንቋም ሆነ በሥልጣኔ ደረጃ የተለያዩ እንደነበርና፣ ንጉሥም እንደዋና ተልእኮው አድርጎ ይመለከት የነበረው በየቦታው ሰላም ማስፈን፣ ንግድ ማስፋፋት፣ ማንም በሌላው ላይ ግፍ እንዳይፈፅም ከበላይ ሁኖ መቈጣጠር ነበር። ግዛታቸው ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ፣ አገሩን በጸጥታና በሥነሥርዐት ስላስተዳደሩ፣ ግፍና ዐመፅ ስላራቁ፣ ንግድ እንዲስፋፋ ጥርጊያውን ስላመቻቹ፣ ከያንዳንዱ ኅብረተ-ሰብ ግብር ይጠብቃሉ። ይኸ ደግሞ በየትም ያለ የዜግነት ግዳጅ ስለሆነ የአክሱሞችን መንግሥት ሆነ፣ በነሱ ምትክ የመጡትን የኋለኞቹን ሥርወመንግሥታት፣ ጨቋኞች ወይንም በዝባዦች አያሰኛቸውም። መንግሥት ነዋሪዎቹ በኢትዮጵዊነታቸው በእኩልነትና በነፃነት [ማለትም በሌላ የውስጥ ኀይል ሳይጨቈኑ በባዕድም ሳይደፈሩ) እንዲኖሩ በማድረግ የዜግነት መብታቸውን እንዳስከበረ ሁሉ፣ ለእነሱም ግብር መክፈል የመንግሥትን ሥልጣን መቀበላቸውንና ላገሩ ሕግ የሚታዘዙ መሆናቸውን ከሚገልጡበት መሣርያዎች ዋነኛው ነው።
የአክሱም ሥልጣኔ በአፍሪቃ ክፍለአገር ከመላው ጥቁር ሕዝብ የሚለይበት ሌላም ነገር አለ። ሥልጣኔው ከራሱ ከአካባቢው ሕዝብ በሂደት የፈለቀና የመነጨ እንጂ ባዕዳን መጤዎች ከፈለሱበት እናት አገራቸው ይዘው የመጡት ወይንም በአክሱም ከሰፈሩ በኋላ የፈጠሩት እንዳልሆነ በእጃችን ያሉት ማስረጃዎች ይገልጡልናል። ይኸንን የሚፃረር አሳብ የሚደግፍ እስካሁን አንድም ማስረጃ የለም። በሌላው አንጻር፣ አክሱሞች ወደሌላው አገር ሂደው ሥልጣኔአቸውን እንዳስፋፉ የተውልን የሕንፃ፣ የጽሑፍ ቅርሶች ይመሰክሩልናል። ሐቁ እንደዚህ ሁኖ እያለ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ጥናት እየተቈጣጠሩት የነበሩት (አሁንም እየተቈጣጠሩ ያሉት ማለት እንችላለን) አውሮጳያን፣ ለጥቁር ሕዝብ ከነበራቸው ንቀት የተነሣ፣ “የአክሱም ሥልጣኔ ከየመንና ከደቡብ ዐረብ ወደኢትዮጵያ ፈልሶ ባገሩ ውስጥ በየጊዜው የሰፈረው ሳባውያን በተባለ ስም የሚጠራው የሴማዊ ሕዝብ ሥልጣኔ እንጂ ካገሩ ነባር ጥቁር ሕዝብ የፈለቀ አይደለም። ይኸም አስገራሚ ሥልጣኔ ሊሞት የበቃው፣ ፈጣሪዎቹ ሴማውያን ከአገሩ ጥቁር ሕዝብ ጋር ከመደበላለቃቸውና ከመወላለዳቸው የተነሣ ነው፤ መጤዎቹ የሰውነታቸው መልክ እየጠቈረ በሄደ ቊጥር፣ አእምሯቸው እየደነዘ፣ የመፍጠር ችሎታቸውም በዚያው ልክ አብሮ ሊደበዝዝና ሊጠፋ ቻለ” ይላሉ። እነዚህ ምሁራን ነን ባዮች፣ ከዚህ ዐይነቱ የተዛባ አስተሳሰብ ተነሥተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሴማውያንንና አፍሪቃውያን እያሉ ለመከፋፈል በቅተዋል። ሴማዉያን ከቀይባሕር ማዶ ከዐረብ አገር የመጡና፣ የአክሱምን ሥልጣኔ የገነቡ ናቸው። ጥቁሮቹን አፍሪቃውያን ደግሞ እነሱ ባወጡት መለኪያ፣ ኩሳውያንና አባይ-ሰሐራውያን ብለው ከፋፍለው ሲያበቃ፣ እነዚህ ለአክሱማውያን ሥልጣኔ ያደረጉት አስተዋፅኦ ኢምንት ነው ይላሉ። በከፍተኛ ዕውቀት የዳበረ የዛሬ ሰው ይኸንን ሲሰማ ነጮችን አምባገነንታቸው ምን ያህል እንዳሳበዳቸው ሊገነዘብና በነገሩ ሊያፌዝበት፣ ካልሆነም ሊስቅበትም ሆነ ሊያዝንበት ይቃጣ ይሆናል። ግን ባገራችን ሌላው ቀርቶ ተምረናል የሚሉትንም እንኳን ሳይቀር አሳምኖ፣ እነርሱም በበኩላቸው ሕዝቡን እስከማወናበድና እርስበርስ እስከማፋጀት አድርሰዋል ማለቱ የለዘበ አነጋገር ይመስለኛል።
ሮም በ፬፻፸፮ ዓ. ም. ላይ ስትወድቅ፣ የአውሮጳውያን የሥልጣኔ መሠረት ጥላ ነበር። አክሱምም በ፱፻ ዘመን አካባቢ ላይ ፍጻሜዋን ስታይ ለኢትዮጵያዉያን ያደረገችው ልክ ይኸንኑ ስጦታ ነው። ሁኖም ሮም የግዛቷ አካል ያደረገቻትና የሥልጣኔዋ ዋና ወራሽ የሆነችው ኢጣሊያ ግን፣ ከሮም ውድቀት በኋላ የፈረሰውን አንድነቷን እስከ፲፰፻፸፪ ዓ.ም. ድረስ መልሳ ማቋቋም አልቻለችም። ኢጣሊያን ከሮም ውድቀት በኋላ የተከተላት የብዙዎች ነገዶች[5] ወረራ ሲሆን፣ ውጤቱ አገሩን መከፋፈልና የአካባቢው የኀይለኞች መንግሥታት መፈንጫ ሜዳ ሁና መቅረት ነው። በኢትዮጵያ፣ የአክሱማውያን መውደቅ ያስከተለው የድብልቅልቅና የጨለማ ዘመን የብጥብጥ፣ የሕገ-አልባነትና የሁኬት ጊዜ እንደነበር ቢነገርም፣ በሌላው በኩል ደግሞ ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ፣ መፈላለስና መዘዋወር የታየበት ወቅት ነበር። ሁናቴው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደበላለቅና ርስበርሱ እንዲተሳሰር በጣም ረድቷል ቢባል ሐቅ ነው። ቀጥሎም ሥልጣኑን የተረከበው ዛጐ በመባል የሚታወቀው የአገዎች ሥርወ መንግሥትም፣ የአክሱማውያንን ሥልጣኔ እንደባዕድ ሳያይ፣ ልክ የራሱ እንደሆነ አስመስሎ ከመቀጠል አልፎ የግሉን ጨምሯል። አገዎች ግብርናን በማዳበር ረገድ፣ ለመጀመርያ ጊዜ አላምደው ወይንም ከሌላ ጋ አምጥተው ለድፍኑ ዓለም ያበረከቷቸው እንደጤፍ፣ ዘንጋዳ፣ ስንዴ፣ ገብስና ባሕርማሽላ የመሳሰሉ የእህልና የዕፀዋት ዐይነቶች በአፍሪቃ ክፍለአገር ውስጥ በመፍጠር ችሎታቸው ወደር የሌለው ሕዝብ ነው አሰኝቷቸዋል[6]። እንደላሊበላ የመሰሉ የነገሥታቱ ሕንጻም ቢሆን የድፍኑ ዓለም መደነቂያና መገረሚያ ሁኗል። በአዱሊስ ሐውልት ላይ እንደተጻፈው፣ የአገው ምድር የአክሱሙ ንጉሥ ካስገበራቸው አገሮች አንዱ ቢሆንም፣ አገዎች የተረከቡት ግዛት ከአክሱም ያነሰ ነበር። ሰለሞናዊ በተባለው ሥርወ መንግሥት እስከተተኩ ጊዜ ድረስ፣ አገሩን ያስተዳደሩት፣ እንደአክሱሞቹ ሕዝቡን በጐሣና በእምነት ሳይለዩ፣ በፍትሕና በርትዕ ነበር። ንግድ እንዲስፋፋ፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሌላው ቀርቶ፣ አማኞች ንግደታቸውን አለችግር እንዲወጡ ማመቻቸት[7]ና የበላይ ሁኖ መቈጣጠር እንደዋና ተግባራቸው ያዩ እንደነበር ታሪካቸው ይመሰክራል።
የዛጐ መንግሥት በአገዎች እንደተቋቋመ፣ የሰለሞኖች መንግሥት የተመሠረተው ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ አማራ[8]ከተባለው አገር በመጣ ንጉሥ ነው[9]። አማራ ደግሞ ያነ የሚያመለክተው የተወሰነ አካባቢ ሲሆን፣ ክልሉም በምዕራብ በአባይና በመጋቢው የበሽሎ ወንዝ፣ በሰሜን በአንጎትና ላስታ፣ በደቡብ በወንጭት ወንዝ፣ በምሥራቅ ደግሞ ወደደንከል በረሃ በሚደርሰው ሰፋፊ ገደላንገደል የተከበበውን ምድር ነው። ከዚህ የምንማረው አሁን አማራ ብለን የምንጠራቸውን እንደነጐጃም፣ በጌምድር፣ ሸዋ እንዲሁም የወሎን አንዳንድ ክፍል እንደማያካትት ነው። በዚህ ግዛት ውስጥ በሚኖሩት የአገሩ ተወላጆች [ማለትም የአማሮች] አፈታሪክ መሠረት የአማራ ሕዝብ አሁን ወዳለበት የመጣው በቀጥታ ከአክሱም ነው። የቃሉም ትርጒም “ነፃ ሕዝብ” ማለት እንደሆነ ይነገራል። ይሁንና አፄዎቹ “ንጉሠ አምሐራ” የሚል ስያሜ ቢኖራቸውም፣ ጐንደር የኢትዮጵያ ቤተመንግሥት ቋሚ መናገሻ ከተማ ሁና እስከተቈረቈረችበት እንደአ.አ. እስከ ፲፮፻፴፪ ዓ. ም. ጊዜ ድረስ፣ ነገሥታቱ ይኖሩት የነበረው ከቦታ ወደቦታ እየተዘዋወሩ፣ አብዛኛውን ጊዜ በደቡብ ባሉት እንደነይፋት፣ ሸዋ፣ ደዋሮና ፈጠጋር በመሳሰሉት አገሮች እንጂ፣ መናገሻቸውን ክልሉን በዘረዘርነው የአማራ አገር አድርገው አያውቁም። ምናልባትም ከመጀመርያዎቹ በስተቀር፣ የአብዛኞቹ ነገሥታት አማራነትም ቢሆን እጅግ በጣም አጠያያቂ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ አማርኛ የተባለው ቋንቋው ራሱ ምንጩና መነሻው አማራ ከተባለው ግዛት ውስጥ ይሁን እንጂ፣ ያደገውና የዳበረው ግን በጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው አስተዋፅኦ ነው። አማርኛ በመባል ከተወለደበት አገር ጋር ተቈራኝቶ ቢቀርም፣ እውነቱ ግን በየአካባቢው የሚገኙትን የተለያዩ ቋንቋዎች ቃላትንም ሆነ ሰዋስዋዊ አገባብ በመከለስና በመደቀል፣ በማዳበልና በማቀያየጥ አዋህዷቸውና አመሳስሏቸው የተውጣጣ የኢትዮጵያውያን የጋርዮሽ ቋንቋ ነው። የቋንቋ ጥናት ምሁራን አነጋገር ብንጠቀም፣ አማርኛ ጥንተ ዘሩ የሴማውያን ቋንቋዎች ከሚባሉት ክፍል ቢሆንም፣ ሐቁ ግን በኩሻውያን ቋንቋዎች ቃላትና ሰዋስዋዊ አገባብ ከሚጠበቀው በላይ ተበርዟል። ስለዚህም ከማንኛውም የኢትዮጵያውያን ቋንቋ ይበልጥ፣ የመላው ያገሪቱ ሕዝብ የትብብር ፍሬ ስለሆነ፣ እውነተኛ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት ነው ማለቱ የሚቀል ይመስለኛል። ይኸንንም በመገንዘብ ነው እንግዴህ ቋንቋው ባገሪቷ ውስጥ ያሉትን የልዩ ልዩ ብሔረ-ሰቦችን ድምፅ ለማስተናገድ ሲል ጥንት ከአባቱ ግእዝ በወረሳቸው ፊደላት ላይ አስፈላጊነቱን እያየ ሌሎች አዳዲስ ሊፈጥርና ሊጨምር የበቃው። ስለዚህም አብዛኛው የአማርኛ ተናጋሪ የሚገኘው ከጥንት ትውልዱ ክልል ውጭ ነው። በላስታ፣ በሸዋ፣ በበጌምድር፣ በወሎና፣ በጐጃም ግዛቶች የኩሳውያንን ቋንቋዎች ተክቶ ይገኛል። ቋንቋዎቻቸው የሴማውያን ነበር በተባሉት አርጐባና ጋፋት በመባል በሚታወቁት አገሮች ደግሞ የአፍ መክፈቻቸው ሁኖ ቀርቷል።
በእነዚህ አገሮች አማርኛ እናት ቋንቋቸው ቢሆንም፣ እንደአ.አ. በ፲፱፻፺ዎቹ ዓ.ም. ላይ፣ አማሮች ናችሁ የሚል ስያሜ በግድ በላያቸው ላይ እስከተለጠፈባቸው ጊዜ ድረስ፣ ራሳቸውን ይጠሩ የነበሩት በሚኖሩበት የአገርና የቦታ ስሞች ጐንደሬ፣ ጐጃሜ፣ ሸዌ፣ መንዜ በመባል እንጂ አሁን በተሰጣቸው አማራ በሚል ብሔረሰብነታቸው አልነበረም። ታሪክም ራሱ የሚያመለክተው ይኸንኑ ነው። ከ፲፬ኛ ዘመነ ምሕረት ጀምሮ እስከ፲፰ኛ ዘመን ድረስ ባሉት ጊዜ ውስጥ በተጻፉት በታሪከ ነገሥታትም ሆኑ፣ እስከ፲፱ኛ ዘመነ ምሕረት ድረስ በተደረሱት በክርስቲያኖቹና በእስላሞቹ መዛግብት ውስጥ “አማራ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው አሁን ጊዜ በወሎ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የቦታ ስም ብቻ ነው። በምንም መንገድ ካንድ ከተወሰነ ብሔረሰብ ጋር የሚያይዝ ምንጭ የለም።
እንዲሁም ከዚሁ ጋር በማያያዝ የምጨምር ነገር ቢኖር፣ ባሁኑ አጠራር ኦሮሞ፣ ድሮ ደግሞ ጋላ በመባል የሚታወቀው ሕዝብ ሁናቴም ልክ ይኸንኑ ይመስላል። የወያኔ መንግሥት በአፄ ምኒልክ ዙፋን እንደተቀመጠ ቦረን፣ ሜጫ፣ ቱለማ፣ ኢቱና ጉጂ በመሳሰሉት ስሞች ራሳቸውን ይጠሩ የነበሩትን ብሔረ-ሰቦች ፣ የፈጠራ ስም ሰጥቷቸው ኦሮሞ በሚባል በጋራ መጠርያ ስም ሥር እንዲካተቱ አስገድዷቸዋል[10]። ይኸ ጥንት ጋላ በአሁኑ መንግሥት አጠራር “ኦሮሞ” የተባለ እረኛ ሕዝብ ለከብቱ ግጦሽ ፍለጋ ሲል፣ በተለመደው አነጋገር “ኢትዮጵያን መውረር” ጀመረ ከተባለ ወደ፭፻ ዓመታት ሊያስቈጥር ነው። ወረራው የጀመረው የእስላሞች ንጉሥ ኢትዮጵያን ሊቈጣጠር ሲል፣ በክርስቲያኖቹ ንጉሠነገሥትና በአገሪቷ ላይ እንደአ.አ. በ፲፭፻፳፱ ዓ.ም. ያወጀው ጦርነት ከ፲፭ ዓመት ከፍተኛ ዕልቂት በኋላ፣ በክርስቲያኖች ድል በተደመደመው ማግሥት ነበር። ጉልበቱ በረጅም ጊዜ ጦርነት ስለተዳከመ፣ በየቦታው የነበሩት የመከላከያ ተቋማትና መዋቅርት ፈራርሰው ስለነበር፣ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥት ወረራውን የመመከትና፣ ሕዝቡንም የመጠበቅ ችሎታው እምብዛም ስላልነበር፣ዘላኖቹ በየሄዱበት በአሬመናዊ ጭካኔአቸው ባደረሱት ለሰማው ሁሉ የሚዘገንን የሰው ዕልቂት፣ የንብረት ውድመት እንደፈጸሙና፣ እግራቸው የረገጠውን አካባቢ በሙሉ ወደጫካና ዱር እስከመለወጥ ደርሰው እንደነበር፣ የጊዜው ሰነዶች አበክረው የሚናገሩት ነገር ነው[11]። ያደረሱትን ጥፋት ባይናቸው ያዩት የውጭም ሆኑ ያገር ውስጥ ጸሓፊዎች፣ ‘ጋላ” ፈጸመ ከሚሉት ግፍና ጭካኔ የተነሣ ድርጊታቸውን አገሪቷን ለመቅጣት ሲባል የተላከ “የእግዚአብሔር መቅሠፍት” ነው በማለት ገልጸውታል።
ሁኖም ግን ኦሮሞች ወረራቸውን በጀመሩት ግማሽ ዘመን እንኳን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሊጠብቁ ሲሉ በጦር ሜዳ ላይ እንደሌላው እንደቈየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብርቅ ሕይወታቸውን ሲሠውና ሲሞቱ ይታያሉ[12]። ነዋሪውን ገድለው ጨርሰው፣ ወይንም ለገባርነት ዳርገው መሬቱን በጉልበት ወስደው በየሰፈሩበት አካባቢ፣ አብዛኞቹ ኦሮሞች የጥንት የእረኝነት ኑሯቸውንና የዘልማድ እምነታቸውን ትተው፣ በግብርና ሕይወት በመሰማራትና፣ የሰፈሩን እምነት በመቀበል፣ የቀረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ መስለዋል። እንደየአሰፋፈራቸው ክርስቲያን ወይንም እስላም ሁነው አብዛኞቹ እንደየእምነታቸው ስማቸውንም እስከመቀየር ደርሰዋል። በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ገብተው ልክ እንደሌላው ብሔረሰብ ተወላጆች በሥልጣን ሲሻኰቱ ማየት የተለመደ ገጽታቸው ሁኖም ይታያል። አፄ ሱስንዮስ ተቀናቃኞቹን ሁሉ አሸንፎ ለንጉሥነት የበቃው በኦሮሞች ድጋፍና የነሱን የጦር ስልት በመጠቀም እንደሆነ ታሪከ ነገሥቱ ይገልጥልናል። ሚስቱም ከርስትና ወልድሠዓላ በሚል በክርስቲያን ስም ብትጠራም፣ በትውልዷ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል እንደነበረች ይነገራል። ይኸም ማለት ጐንደርን ከቈረቈረው ከልጇ ፋሲለደስ ጀምሮ እስከ ዘመነ-መሳፍንት ድረስ በኢትዮጵያ ዙፋን ይቀመጡ የነበሩት የሷ ልጆችና የልጅ ልጆቿ እንደነበሩ ነው የሚያሳየው። ዘመነ መሳፍንት ማለት ደግሞ የኦሮሞ ዝርያ ናቸው የተባሉት የየጁ መኳንንት ላንድ መቶ ዓመት ያህል የጐንደርን መንግሥት ሙሉ በሙሉ የተቈጣጠሩበት የኢትዮጵያ ታሪክ ዘመን ነው ማለቱ እውነትን ያንፀባርቃል ብዬ አምናለሁ። የጁዎች በክርስቲያን ቤተመንግሥት ተቀምጠው እስላሞችን ሲያገቡ ያከረስትኗቸው እንደነበረ ሁሉ፣ የወሎዎቹ ሙሐመዶች ደግሞ እስላሞች እንደመሆናቸው ከክርስቲያን ሚስቶቻቸው ይጋቡ የነበሩት እያሰለሟቸው ነበር። ሁለቱም በዝርያቸው ከኦሮሞ ብሔረሰብ እንደመሆናቸው ሁናቴው የሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደምና በሥጋ ብቻ ሳይሆን በእምነትና በባሕል ወወራረሱንና መዋሐዱን ነው።
ዘመነመሳፍንትን ያከተሙት አፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊ የቋራ ብሔረሰብ ተወላጅ ናቸው። ቋራ የአገው እንጂ የብሔረ አማራ ዝርያ አይደለም። በሌላው በኩል ደግሞ፣ ከልክ በላይ የሚወዷት ሚስታቸው የኦሮምኛና የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰብ ልጅ እንደነበሩ ምንም አያጠያይቅም። እንዲሁም ከአፄ ዮሐንስ ቀጥለው በኢትዮጵያ ዙፋን በየጊዜው ከነገሡት ነገሥታት በቀጥታ ኦሮሞ ያልሆነ ወይንም የኦሮሞ ደም የሌለው አንድም ገዢ አልነበረም ማለት ይቻላል። በሌላው ጐን ደግሞ ኦሮሞች በወረራቸውም ወቅት ቢሆን፣ ያካባቢውን ሕዝብ ወንድና ሴት፣ ዐዋቂና ሽማግሌ ሳይለዩ በጅምላ ሲገድሉ፣ ብዙውን ጊዜ ሕፃናቱን ማርከው ወስደው እንደሚያሳድጓቸው መታወቅ ይገባል። በዚህ መልክ ከተማረኩት ሕፃናት መካከል አፄ ሱስንዮስ አንዱ ነበሩ። እነዚህ ሕፃናት የብሔረሰቡ አባላት ሁነው ላቅመአዳም ሲደርሱ፣ ከኦሮሞው ጋር ተጋብተው ልጅ መውለዳቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያልተዳቀለ በዘሩ ጭንጩ ኦሮሞ የሆነ ሰው፣ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ አለ ማለት በፍጹም ዘበት ነው። ከኔ ምርምር እንደምረዳው ከሆነ፣ የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ያሰከረው ግለሰብ ወይንም ቡድን ብቻ ነው በዚህ ዐይነት ቅዠት የሚጠቃው።
ይኸ ሁናቴ ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ የሚመለከት ነው። የዛጐን ሥርወ መንግሥት የተኩት ሰለሞናውያን ነገሥታት፣ ከቀይባሕር ማዶ ያሉትን የድሮዎቹን የአክሱማውያንን ግዛት መቈጣጠር ባይችሉም፣ እስከዘመነ-መሳፍንት ድረስ በበላይነት ይገዙት የነበረው የኢትዮጵያ የቈዳ ስፋት ከመላጐደል እንደኣ.አ. እስከ፲፱፻፹ ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ያለውን ያጠቃልላል። የእነሱም አስተዳደር የተከተለው ልክ ቀድመው የመጧቸውን የአክሱሞቹንና የዛጐዎቹን ፈር ነበር። በእምነታቸው ክርስቲያን ቢሆኑም፣ ሕዝቡን በዘውጉና በሃይማኖቱ ምክንያት ሳይለዩ፣ በፍትሕና በርትዕ ማስተዳደር፣ ንግድ ማስፋፋት፣ ሰላምና ጸጥታ ማስፈን ዋነኛ ዓላማቸው ነበር። እንደማንኛውም የገዢ ክፍል ሥልጣናቸውን የሚቀናቀን ወይንም የሚደፍር ለነሱ ጠላት ነበር። ይኸንን ሐቅና የኢትዮጵያ ነገሥታት ምን ያህል ለማንም ሳያዳሉ ሁሉንም እምነት በደምብ ማስተናገድ ሥራቸው እንደነበር፣ ታላቁ አፄ ዐምደጽዮን [1314-1344]፣ “እኔ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር የመላው እስላም ንጉሥ ነኝ” ያሉት ንግግር መርሀቸውን ጥርት አድርጎ ይገልጻል። ይኸም ኢትዮጵያን ከአብዛኛው የክርስቲያን ዓለም በጣም ልዩ አገር ያደርጋታል። ከሳቸው በኋላ ወደመቶ ዓመት ያህል ቈይተው የነገሡት ያውሮጳ ነገሥታት መቻቻልና አብሮ መኖር የሚባለው ሐሳብ በቋንቋቸው ስላልነበር፣ እንኳን እስላም ይቅርና፣ ክርስቲያን የተባለውን ሕዝባቸውን በፀረማርያምና በካቶሊክ ጐራ ለያይተውት አላንዳች ምሕረት ሲጨፈጭፉትና ሲያስጨፋጭፉት፣ ካዘኑለት ደግሞ ከግዛታቸው ሲያባርሩት እናያለን። እውነት ነው በኢትዮጵያም ውስጥ ቢሆን ዘመናዊ አስተዳደር እስከተዘረጋ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ክርስቲያን ሁኖ የእስላምን አገር ማስተዳደር እንደማይቻል ሁሉ፣ እስላም ሁኖ የክርስቲያንን አገር ማስተዳደርም አልተለመደም። ሕዝቡም ቢሆን የሚቀበለው ሥርዐት አይደለም። የኢትዮጵያ ነገሥታት ይኸንን በመረዳት ነው እንግዴህ የመላው ኢትዮጵያ ማለትም የክርስቲያኑም፣ የእስላሙና የባህላዊ እምነቶች ተከታዩም ሕዝብ መሪዎች መሆናቸውን ለማስታወቅ ባፄነታቸው ላይ “ንጉሠ ጽዮን ወንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ[13]” የሚል መፈክር በማኅተማቸው ላይ ያኖሩት የነበረው።
አስተዳዳሪዎቹን በተመለክተ፣ ከሰለሞናውያን እስከ ዘመነ መሳፍንት ባሉት ዘመናት ጊዜ ውስጥ በክርስቲያኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ እከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩትን ሰዎች ብሔረሰብነት ለመመርመር ብዙ ሰነዶች የሉንም። በእጃችን ያሉን ጥቂቶቹ የሚያመለክቱት፣ ግለሰቦቹ ከሁሉም ብሔረሰቦች የተወጣጡ መሆናቸውን ብቻ ነው። በነገሥታት ደረጃ፣ ያብዛኞቹ ነገሥታት እናቶቻቸው ከሐድያና ከአካባቢዎቹ ብሔረሰቦች የተወለዱ ነበሩ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወደር የሌለ ሚና ተጫውተዋል ተብለው ከሚደነቁት ሴቶቹም ወንዶቹ መካከል በገናናነትና በስመጥሩነት ስሟ ዘወትር የሚነሣው ንግሥት እሌኒ[1431-1522][14] የሐድያው መሪ የሙሐመድ ወይንም የቦያሞ ልጅ ነበረች። በሥልጣን ሽኩቻ በንጉሥ ሱስንዮስ እጅ የተገደሉት አፄ ያዕቆብም ሆኑ፣ ኋላ ንጉሥነገሥትነቱን በጦር ኀይል የተጐናፀፉት አፄ ሱስንዮስ ራሳቸው ጭምር በእናቶቻቸው ከቤተእሥራኤል ናቸው። የአፄ ሱስንዮስ ታሪክ እንደሚገልጥልን ከሆነ ያነ በጣም ታላቅ ሁኖ የሚታሰበውን የጐጃምን ግዛት፣ “ጐጃም ነጋሽ” የሚለውን ከፍተኛና ክቡር የሆነውን ያገሩን የገዢ ማዕርግ ተጐናፅፎ ለብዙ ዓመታት ያስተዳደረው የጉራጌው ተወላጅ ስልቡ“ጐጃም ነጋሽ ክፍሎ” ነበር። ያፄ ሠርፀድንግልን ሁለት ልጆች አግብቶ፣ አገሩን በበላይነት ይገዛ የነበረው በጊዜው የመንግሥት ፈላጭ-ቈራጩ መኰንን፣ የወለጋው ተወላጅ ራስ ዘሥላሴ[15] ነበር። በ “ዳሞት ጸሓፊላምነት” ማዕርግ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብም ሆነ፣ ወሰንና ድንበር ለማስጠበቅ ሲል ብዙ ጦርነት በጀግንነት በመዋጋት፣ ንጉሠነገሥቱን እንደአ.አ. ከ፲፮፻፲፯ እስከ ፲፮፻፳፯ ዓ.ም. በታማኝነት አገልግሎ፣ በመጨረሻም የዳሞት ግዛቱን “ከጋላ ወረራ” ሊከላከል ሲል በጦር ሜዳ ላይ ሕይወቱን የሠዋው ደጃዝማች ቡኮ፣ ከመጀመርያዎቹ የኦሮሞች ታላላቅ ገዢዎች አንዱ ነበር። እንዲሁም ንጉሠነገሥቱ “እንደልቤ ታማኝ” ያሉት፣ ዋናው አማካሪያቸውና፣ ከቁመታቸው ማጠር የተነሣ በኦሮሞኛ ቃል “ጢኖ” በመባል የሚታወቁት፣ ጸሓፈ ትእዛዙ አዛዥ ተክለሥላሴ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ነበሩ። ጽሑፋቸው እንደሚያመለክተው፣ አዛዥ ጢኖ ከኦሮሞ ቋንቋና ባህል በተጨማሪ፣ አማርኛና ግእዝ አሳምረው የሚያውቁ፣ ቅኔ የሚቀኙ፣ አንደበታቸው የተባ፣ ብዕራቸው የሰላ ጸሓፊ ናቸው። እነዚህ ለእንደዚህ ዐይነት ወግና ማዕርግ ሊበቁ፣ ዕውቀትንም ሊገበዩ የቻሉት፣ “ጋላ” በኢትዮጵያ ፈጸመ የተባለው ወረራ ግማሽ ዘመን ማለት ዐምሳ ዓመት እንኳን ሳይሞላው ሲሆን፣ እስከኛ ጊዜ ድረስ ባሉት ዐራት መቶ ዓመታት ውስጥማ ምን ያኽል መቀራረብና መዋሐድ እንደተካሄደ መገናዘብ የሚያዳግት አይሆንም። እንግዴህ የአክሱማያኑን እንኳን ብንተው፣ ከሰለሞናውያን ሥርወ መንግሥት ጀምረን የኢትዮጵያን መዝገበ ታሪክ፣ በፖለቲካ ጥቅም ተገፍተን ሳይሆን ታሪክ በሚጠይቃቸው በምርምር መስፈርቶች[16] ተመሥርተን ብናሰላስል፣ በመጀመርያ ደረጃ ስለቋንቋ እንጂ ስለብሔርና ብሔረሰብ[17] ልዩነት መናገር አንችልም። ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ የቋንቋ እንጂ የዘር ልዩነት ከቶውኑ የለም ማለት የማይካድ ሐቅ ነው ማለት ይቻላል። እንግሊዝኛ የሚናገር የእንግሊዝ ዘር እንዳልሆነ ሁሉ፣ ኦሮሞኛንም የሚናገር ሁሉ የኦሮሞ ዘር አይደለም። ታሪክ የሚያስተምረን ታላቅ ነገር ቢኖር፣ ቋንቋዎች ይጠፋሉ፣ በሌሎች ቋንቋዎች ይተካሉ። የአርጐባ ተወላጆች ነን ባዮች፣ ዛሬ እንደአፍ መክፈቻቸው የሚናገሩት ቋንቋ አርጐበኛ ሳይሆን እንደየአሰፋፈራቸው አካባቢ ልዩነት፣ አማርኛ፣ አፋርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ ነው። በምዕራብ ወለጋ የሚኖሩት አንፊሎች ቋንቋቸውን ረስተው አሁን የሚናገሩት ኦሮምኛ ነው።
ነገሩ እንደዚህ ከሆነ ታዲያ፣ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እኩልነትና ነፃነት ተነፍገው የሚኖሩባት እስር ቤት ናት የሚለው አስተሳሰብ ከየት መጣ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል። ባጭሩ ለመመለስ፣ አሳቡ ብቅ ያለው ኢትዮጵያ ኢጣሊያንን በአድዋ ጦርነት ድል አድርጋ ለአውሮጳውያን ከፈጠረችው ውዝግብ ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል። ኢጣሊያም ቢሆን እንደ አ.አ. በ፲፰፻፸፪ ዓ.ም. ዓመት ላይ መልሳ አንድ አገር ስትሆን፣ እንደኢትዮጵያ በብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተጥለቀለቀችና የተወጠረች አገር ነበረች። ከኢትዮጵያ በተለየ መልኩ ደግሞ ቋንቋዎቹን ተናጋሪዎች ሕዝቦች ከተለያዩ አገሮች የተሰባሰቡ ጥርቅምቅም ከመሆናቸውም በላይ፣ ገዢዎቻቸውም የተለያዩና እንደየጊዜው ይለዋወጡ ስለነበር፣ ሕዝቦቹ ርስበርሰ ለመደባላለቅ፣ ከቦታ ወደቦታ ለመዘዋወር ዕድል አልገጠማቸውም። ስለዚህም አገሪቷ አንድ እስከሆነችበት ጊዜ ድረስ ለዐራት መቶ ዘመናት[18]ተለያይተው ሲኖሩ፣ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር፣ ሁላቸውም የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሆናቸው ብቻ ነው። ኢጣሊያኖች በኢትዮጵያ ላይ ማትኰር የመረጡት አንድነታቸውን ለማጐልበት፣ ልዩነታቸውን ለማስረሳት ሊረዳ ይችላል ብለው ከተለሙት ጥንስሶች አንዱ ስለነበር ነው። ስለዚህም፣ የሆነ ያልሆነ ምክንያት በመፍጠር፣ እጃቸውን በኢትዮጵያ ላይ ከመቅሰር መቼም ሊቈጠቡ አልቻሉም። የአድዋ ድል ጥሩ ትምህርት አስተምሯቸው ለጊዜው ተወት ቢያደርጉትም፣ ልክ አፄ ምኒልክ እንዳረፉ፣ ወደጥንት አሳባቸው ተመልሰው መጡ። የያኔ መርሃቸው “የዳር ፖሊትካ[19]” በመባል ይታወቃል። ከቅድመ አድዋው ዘዴያቸው የሚለየው፣ ይኸኛው “የሸዋና የትግራይ ፖሊትካ[20]” በመባል ሲታወቅ፣ ዐላማው የትግራይንና ባካባቢዋ ያሉትን የባላባቶችን ግዛቶች ከማእከላዊው የአዲስ አበባው መንግሥት ጋር በማጋጨት፣ ያገሪቷን አንድነት በማናጋትና የርስበርስ አለመግባባት በማጠናከር፣ አገሪቷ ተበታትና በኢጣሊያን እጅ እንድትወድቅ ማዘጋጀት ነበር[21]።
በኢጣሊያን ባለሥልጣኖች አገላለጽ፣ “የዳር ፖሊትካ”ም ግቡ ይኸው ነበር። ዋና ትኩረቱ ግን ባንድ በኩል የኢትዮጵያን መኳንንት በገንዘብ በመግዛት፣ ተራ ሕዝቡን በሕክምናና በትምህርት ቤቶች ስጦታና በመሳሰሉት ነገሮች ስም በማታለል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ላለው መስተዳድር ወዳጅ በመምሰል፣ ማእከላዊው መንግሥት ያገሩን አንድነት ለማጠንክር የሚያደርገውን እርምጃና ጥረት በተቻለ መጠን በሙሉ ማክሸፍ ይገባል የሚል ነበር። ሁኖም እንደአ..አ. በ፲፱፻፴ ላይ የኢጣሊያን ባለሥልጣናት የጻፉት ዘገባ፣ “ኢጣሊያ እንዳቀደችው ኢትዮጵያ ደካማ ከመሆን ይልቅ”፣ አፄ ኀይለሥላሴ ከተጠበቀው በላይ አገሩን በዘመናዊ መልኩ እንዳዋሃዱትና አንድነቱን እንዳጠናከሩት፣ የኢጣሊያንም መርህ ልክ እንደቅድመ አድዋው መክኖ እንደቀረ ይናገራል[22]።
አፄ ኀይሌ ሥላሴ ያመጡት ለውጥ ያስተሳሰበው ኢጣሊያንን ብቻ አልነበረም። በኢትዮጵያ ውስጥ ለጥቂት ዓመታት ከሠራ በኋላ ካገር የተባረረው ሮማን ፕሮቻዝካ የተባለ የነምሳ ተወላጅ፣ ሁናቴው የሌሎችም አውሮጳውያን ዋና ሥጋት እንደነበር ይገልጣል። ፕሮቻዝካ አደጋውን ከጅምሩ ለመቅጨት ሲል፣ እንደአ.አ. በ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. ላይ “ኢትዮጵያ የባሩድ በርሚል” የሚል መጽሐፍ አሰራጨ። በዚህ ወዲያዉኑ በብዙ ቋንቋ በተተረጐመው መጽሐፍ አባባል፣ የኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት፣ እንዲሁም ከአውሮጳ አገሮች ተምረው የተመለሱት ወጣቶች ሥራቸውን በዚህ መልክ ከቀጠሉ፣ ያፍሪቃ ቅኝ ገዢዎች ለሆኑት አውሮጳውያን እጅግ አስጊ ሁናቴ ስለሚፈጠር፣ ኢትዮጵያ እንዲትበታተን፣ ሕዝቦቿን “በነገድ፣ በዘር፣ በቋንቋና በባህል መከፋፈልና” ሁሉም ነገዶች በአምባገነኑ አማራ እየተጨቈኑ እንዳሉ መስበክ ያስፈልጋል[23]”። ኢጣሊያም አገሩን ወርራ እንደያዘችው፣ ሥራዬ ብላ የለፋችው፣ ኢትዮጵያ የሚል ስም ካለም ካርታ እንዲፋቅ[24]፣ ሕዝቡ በጋራ ቋንቋ አማካይነት ርስበርስ እንዳይገናኝ አማርኛን ማጥፋት፣ የአንድነት መንፈስ እንዳያዳብር አስተዳደሩን በቋንቋና በጐሣ መሠረት አወቃቅሮ መከፋፈል ላይ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነገር ስለሚመስለኝ እዚህ ላይ መተንተኑ አስፈላጊ ሁኖ ስለማይታየኝ እዘለዋለሁ። ዋናው ነገር ግን፣ እንዳለፉት ሌሎች ጥንስሶችዋ ሁሉ፣ ይኽንንም በተግባር ሊታውለው አልቻለችም። የኢትዮጵያ አርበኞች የሰነዘሩት የጥቃት ወላፈን እስከአገሯ መጥቆ ደርሶ፣ ኢጣሊያን ራሷን ባለም ጦርነት ውስጥ በመዝፈቅ ለህልውናዋ እስከማስጋት ደረሰ። ፕሮቻዝካም ኢትዮጵያን ለማጥፋት የቀየሰው ንድፍ ከኢጣልያን ሽንፈት ጋር አከተመ። ለኢትዮጵያ የቃጣው ዱላ ለራሱ አገር ለነምሳ ተረፈ[25]።
ይሁንና እንደአ.አ. በ፲፱፻፷ቹና ሰባዎቹ ለመጀመርያ ጊዜ ባገር ውስጥ ከፍተኛ ትምህርት በመቅሰም ላይ የነበሩት ተማሪዎች የፕሮቻዝካን ቅያስ ከተቀበረበት አንሥተውት እንደገና ለአዲስ ሕይወት አበቁት። በጊዜው ባለም ደረጃ ደርቶ የነበሩት በወጣቶች ፊታውራሪነት የሚመሩት ፀረቅኝ ግዛትና ፀረ-ቄሳርያዊነት እንቅስቅሴዎች፣ ለኢትዮጵያም ተማሪዎች ተረፉ። እነዚህ ተማሪዎች፣ አገራቸውን ኢትዮጵያን በውጭ አገር ካዩትና በትምህርት ገበታ ከቀሰሙት ፅንሰአሳቦች ላይ በመመሥረት ሲመረምሯት፣ በምጣኔ ሀብት ዕድገት አኳያ በጉልተኛ ባላባት[26] ሥርዐት ደረጃ ያለች ኋላቀር አገር ትሁን እንጂ፣ እሷም ብሔር ብሔረሰቦችን በመጨቈን፣ ቅኝግዛትን በማስፋፋት የነጮች አውሮጳውያን አጋር ነበረች ብለው ደመደሙ። ለነዚህ ብዙውን ጊዜ ከወጣትነት ዕድሜ ጋር አብሮ በሚመጣው በኀልዮ ኑሮ በተበረዘው ጭንቅላታቸው፣ በጥራዘ-ነጠቅነት ላይ የተገነባ ማራኪው የኅብረተሰባዊነት አስተሳሰብ ሲጨመርበት የግንዛቤአቸው ሐቀኝነት እየጐላ እንደሄደ አይካድም። ጊዜው ደግሞ የቀዝቃዛ ጦርነት ወቅት ስለነበር፣ ብዙዎቹ የፖሊትካ ጥቅማቸውን የሚያራምዱ ኀይሎችና ግለሰቦቻቸው ሰለባ እንደነበሩ አይካድም[27]። ዋናው ነገር ግን የተራማጅነት ጨንበል አጥልቀው በሰላቢ ድምጻቸው፣ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ለከፍተኛ ትምህርት ሲሉ በተሰማሩበት ዓለም ውስጥ ይንጫጩ የነበሩት ሁሉ፣ ባይን ዐዋጅ ተመርተው ያዩትን አሜን ብሎ ከመቀበልና በለብለብ ዕውቀታቸው ላይ ከመመሠረት ውጭ፣ ያገሩን ሁነኛ ታሪክና ባህል፣ የምጣኔውንና የማኅበራዊውን ዕድገት ደረጃና መጠን ባገናዘበ በረቀቀ ጥናትና በጠለቀ ምርምር የተመረኰዘ አልነበረም። እውነት ነው እንቅስቃሴዎቹ በርከት ላሉት መሪዎቻቸው ባገርና በዓለም ደረጃ ጐልተው እንዲታዩ፣ ዕድልና ምቹ መድረክ ሰጥቶዉአቸዋል። በጥራዘ-ነጠቅነታቸው በየቦታው እየሄዱ የነበነቡት ግራዘመም ስብከታቸው ግን፣ አገሪቷን ህልውናዋን እስከመፈታተን ድረስ ለታላቅ መከራና ሥቃይ ዳርጓታል። የጥፋት አደጋው አሁንም ቢሆን እላይዋ ላይ እያንዣበበ እንዳለ ሁላችንም ስለምናውቅ እዚህ ላይ በማተት ላሰለቻችሁ ምኞቴ አይደለም።
የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትልቁ ችግር ኢትዮጵያ አንድ ከመሆኗ በፊት ባገሩ ውስጥ የነበረውን ያገዛዝ ሥርዐትና ሁናቴ አለማመዛዘናችውና በዙርያዋም ይካሄዱ ከነበሩት ከአውሮጳውያን ተግባራት ጋር አለማያያዛቸው ነው። ካንድነት በፊት አገሪቷን ከጫፍ እስከጫፍ ይገዙ የነበሩት፣ በተለያየ የማዕርግ ስም ይጠሩ የነበሩት የየአካባቢው ባላባቶች ነበሩ። እነዚህ አገራቸውን ወደርስበርስ ጦርነት እንደቀየሩት፣ ነዋሪዎቹን በለየለት ዐይንባወጣ ብዝበዛና ሥቃይ እያተራምሱ እንደነበርና፣ ሕዝቡ ሰላምና ዕረፍት ከማጣት አልፎ፣ የነበረው ያስተዳደር ሥርዐት ከባርነት የተለየ እንዳልነበረ ተማሪዎቹ የተረዱ አይመስልም። ሁሉንም በየዘርፉና በየቦታው መዘርዘር አስፈላጊም አይደለም። ጊዜም አይፈቅድም። ግን ለምሳሌ ያህል ብቻ ሌላውን ትቼ ሁለት አካባቢ ልጥቀስ። የጋዳን ሥርዐት አድናቂዎች፣ ሩቅም ሳይሄዱ በኦሞ ሸለቆ አካባቢ ቊብ ቊብ ያሉትን የጂማ አባጅፋርን፣ የሊሙ እናርያን፣ የጐማንና የጉማን፣ እንዲሁም የለቃ-ነቀምቴንና የለቃ-ቄለምን መንግሥታት ሊያዩ ይገባል። እነዚህ መንግሥታት አካባቢውን የያዙት፣ ነባሩን ሕዝብ በመፈንቀል፣ ወይንም በመግደልና ለባርነት በመዳረግ መሆኑ መረሳት የለበትም። አልፎ አልፎ አንዳንድ ጥሩ ገጽታ ቢኖራቸውም፣ ከመላጐደል የሚያማዝነው አስቀያሚ ጐናቸው ነበር ቢባል የሚካድ አይደለም። የደሞክራሲ ሥርዐትን ያቀፈ ነው ተብሎ የሚወራውን የጋዳ አገዛዝ አፍርሰው፣ ገዢዎቹ አምባገነኖች ሁነው በዘፈቀደ ይገዙ ነበር። ሕዝባቸውንም ሆነ፣ ከሌላ አካባቢ የሚመጣውን እንደባዕድ የሚቈጥሩትን ሌላውን መጤ መፈንገል ልማዳቸው ነበር። የእስላም ሃይማኖት በግድ ያልተቀበለ አንገቱን ለሳንጃ አሳልፈው ይሰጡ ነበር። አለበለዚያም ለስደትና ለባርነት ይዳረግ ነበር። ድንበር ለማስፋት የሚደረገው ጦርነት መቆሚያ አልነበረውም።
ከነዚህ ወጣ ብለን ሌሎችን ብናይ የከፋ እንጂ የተሻለ አስተዳደር አናገኝም። ዎማ ወይንም ንጉሥ በመባል የሚታወቅ የከምባታ ገዢ ለምሳሌ፣ በየጊዜው ባካባቢው ካሉት ሕዝቦችና ባላባቶች ጋር ባካሄዳቸው አስከፊ ጦርነቶች፣ መንግሥቱን እያስፋፋ በሄደ ቊጥር አምባገንነቱም በዚያው ልክ አሻቅቦ ነበር። ኦያታ በመባል ለሚታወቀው የራሱ የገዢው መደብ፣ ኮንቶማ የተባለውን ተራውን ሕዝብ እንዲበዘብዝና እንዲያዋርድ ሥልጣን በሥልጣን ላይ ካበላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ኦያቶች ገደብ የለሽ ሚስቶች ሊያገቡ ሲችሉ፣ ተራው ኮንቶማ ግን ካንድ ሚስት በላይ አይፈቀድለትም ነበር። ኦያታ ምርጥ ምርጥ መሬት እየነጠቀ ከተራው ኮንቶማ ወስዶ ሲያበቃ፣ ኮንቶማውን መሬት አልባ ገባር ማድረግ መብቱ ነው። ከዚያም አልፎ ኮንቶሞች አጥር ማጠር፣ በቅሎ መጋለብ አይፈቀድላቸውም፡፡ ጥሰው ከተገኙ የሚጠብቃቸው ጥቃት ቅጥ ያጣ ነበር። ንጉሡም ሲሞት ከባሮቹ ተመርጠው ቆንጆ ሴቶችና ሀብቱም አብረው ይቀበሩ እንደነበር ይነገራል።
አፄ ምኒልክ በጦር ኀይልም ሆነ፣ “ሕዝብ በከንቱ እንዳያልቅ፣ ሀገር እንዳይጠፋ በሰላም ግበር” የሚለውን ጥሪያቸውን ተቀብለው በፍቅር በተዋሀዱት አገሮች፣ ከእነዚህ አስከፊ ገጽታ ካላቸው ያስተዳደር ሥርዐት አብዛኛውን ሽረው፣ ሕዝቡ እፎይ እንዲል አድርገዋል። በቦታቸው የዘረጉትም አስተዳደራቸው መዋቅር ሁለት የተጠማመሩ ግቦችን ያካተተ ነበር ማለት ይቻላል። አንደኛው ሕዝብን በግድ ሳይሆን በፍቅርና በዘዴ መግዛት ሲሆን፣ ለዚህም በሕዝቡ ዘንድ እሱ የለመደውና የሚያውቀው ያገሩ ባላባት ተቀባይነት ይኖረዋል ብለው ስላመኑበት፣ የተማረከዉን ገዢ መልሰው በቦታው ይሾሙ ነበር። ካልሆነም ልጁን ወይንም ሕዝቡ ተሰብስቦ የመረጠውን ያስቀምጡ ነበር። መዋጋትንም ይመርጡት የነበረው ባላባቱ፣ በሰላም ግበር ብለው አስቀድመው ደጋግመው ለላኩት ጥሪ፣ አሻፈረኝ ሲላቸውና፣ ሌላ አማራጭ ሲያጡ ብቻ ነበር።
ሁለተኛው ዓላማ፣ ዘመኑ አውሮጳዉያን፣ ነጭ ያልሆነውን ዓለም የሚቀራመቱበት ወቅት ስለነበር፣ ቅኝ ገዢዎቹ አገሩን ለመያዝ ልባቸው እንዳይዳዳ፣ ንጉሠነገሥቱ በግዙፉ በይፋ ማስታወቅ ነበረባቸው። ለዚህም ሲባል፣ ቅኝገዢዎቹ አገሩ በአፄ ምኒልክ ሥር እንዳለና፣ ቢዳፈሩም ጦርነቱ በቀጥታ ከሳቸው ጋር መሆኑን እንዲረዱ፣ ከማዕከላዊ መንግሥት የተሾመ የታጠቀ የጥበቃ ኀይል በያገሩ ተመደበ። የውስጡ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በባላባቱ እጅ ስለሆነ፣ ሕዝብ ተበደልሁ ካላለ በስተቀር፣ የጥበቃው ክፍል ባስተዳደሩ ጣልቃ አይገባም። ሁኖም ግን የሥልጣን አጠቃቀም ውስብስብነት ስላለው መቼም ቢሆን ችግር እንደሚኖር አይካድም፤ የሚጠበቅም ነው። ይሁንና በዚህ መልክ የተዋቀረው አስተዳደር ራሱን የቻለ እንዲሆን ሲባል፣ እያንዳንዱ ባላባት ዓመታዊ ግብር ይከፍላል። ከዚህም ግብር፣ የጥበቃው ክፍል ለራሱ የሚበቃውን ቀንሶ፣ የቀረውን ለመንግሥት ግምጃ ቤት ያስተላልፈዋል።
ሁኖም ግብሩ የተጣለበት የደቡቡ ሕዝብ ከዉህደቱ በፊት፣ ከዚህ በላይ ራሳቸውን በቻሉ በጥቃቅን የባላባቶች መንግሥታት ቢጤ ሥር ስለነበር፣ እንደሰሜኑ ሕዝብ ለማዕከላዊ መንግሥት ለብዙ ዘመናት ገብሮ አያውቅም። ስለዚህም ትውፊቱ በሌለበት አካባቢ ግብር በመጣሉ፣ እንደግፍ ተቈጥሮ በመተቸት፣ ያፄ ምኒልክን ሥራ በቅኝ-ገዢነት እስከመተርጐም አድርሷል። እንዲህ ዐይነቱ አቃቂር መሠረተ ቢስ ከመሆን አልፎ፣ በታሪክም ቢሆን በምንም መልኩ የማይደገፍ ነው። እንግሊዞች “ግብርና ሞት ሁለት አይቀሬ የመኖር ዕዳ ናቸው” እንደሚሉ ሁሉ፣ አፄ ምኒልክ በግዛታቸው ሰላም ለማስፈር፣ ጸጥታ ለማስከበር፣ የሚወጣውን ወጪ ለመሸፈን፣ እንደማንኛውም መንግሥት ግብር የማያስከፍሉበት ምክንያት የለም። እንደእንግሊዞቹ ባገራችንስ ቢሆን “ግብር ይውጣ፣ የማይቀር ዕዳ” ወይንም “ግብር፣ እስከመቃብር” ይባል የለም። ይልቅስ ግብሩ፣ ጊዜውንና የሕዝቡን አኗኗርና ችሎታ ያገናዘበ በመሆኑ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ምን ያኽል አስተዋይና፣ የአገራቸውንና የሕዝባቸውን የዘለቀታ ጥቅም በደምብ የተረዱ መሆናቸውን ፍርጥ አድርጎ ያመለክታል።
ግብሩ በጠቅላላ ከሕዝቡ ዐቅም ጋር የተመጣጠነ ሁኖ፣ የክልሉን አስተዳደር ወጪ ችሎ፣ ቀሪው ለመንግሥት ግምጃ-ቤት ገቢ ይደረግ ነበር። ይኸም ኢትዮጵያ ከውጭ አገር መንግሥታትና ከዓለም-አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ገንዘብ ሳትበደር፣ ባላት ገቢዋ ብቻ ተቈጥባ፣ እጅግ በጣም ሰፊ አገር እንድታስተዳድርና፣ አንዳንድ የልማት ሥራዎች እንድታካሄድ አበቅቷታል። አለመበደሯ ለአብዛኞቹ የእስያና የአፍሪቃ ሀገሮች ከደረሰባቸው መጥፎ ጽዋ (በተለይም ግብፅን የገጠማት ዐይነት)፣ ማለትም አበዳሪዎቹ ኪሳራቸውን ለመሸፈን በሚል ሽፋን አገሯን በዋስትና ከመያዝ አድኗታል። አካባቢው የታወቀ የተፈጥሮ ምርት ከሌለው፣ በሰሜኑ ክፍል እንደተለመደውና ከጥንት ይሠራ እንደነበረው፣ መሬቱ ተሸንሽኖ በተወሰነ ሰው ቊጥር ይደለደልና በሰው ልክ ግብር ይጣልበታል። በተራ ቋንቋ ገባር የሚባል ቃል ከዚህ የመነጨ ነው። ትርጒሙም “ግብር የሚከፍል” ማለት ነው።
ባህሉንና አሠራሩን ባልተረዱትና፣ ከአገራቸውና ከራሳቸው ጥቅም አንጻር በሚያዩት የፈረንጅ ጸሓፊዎች ላይ በመመርኰዝና ከታሪክ ሂደት ጋር ካለማገናዘብ የተነሣ ነው እንግዴህ፣ ብዙዎች ተማርን ባዮች ኢትዮጵያውያን ለገባር መጥፎ ትርጒም ይሰጡ የነበሩት። ይባስ ብሎ፣ ከፀጥታ ጥበቃው ክፍል በማያያዝ “የነፍጠኛ ሥርዐት” ብለው የሚጠሩትም አሉ። ታሪክ ማጣመም ካልተፈለገ በስተቀር ትርጒሙ እውነቱን አያንፀባርቅም። ከጊዜው የአገሩ ምጣኔ ሀብትና ከሕዝቡ የዕድገት ደረጃ፣ እንዲሁም ከዓለም ዐቀፍ ሁናቴና ከዘመኑ መንግሥታት ኀይል አሰላለፍ አንጻር ሲታይ፣ ምንም ብንል፣ ያኔ ከገባር የተሻለ አማራጭ ከቶውኑ አልነበረም። ቢኖር ኖሮ፣ አፄ ምኒልክ በደስታ እንደሚቀበሉት በምንም አይጠረጠርም። ለዚህም ያኔ በመጠኑ በሥልጣኔ ደረጃ ከሌላው ክፍለ አገር ሻል ብላ ለሚትገኘው ለድሬዳዋ ከተማ በ፳፰ ሠኔ ፲፰፻፺፰ ዓ.ም. አስተዳደርዋ እንደሌላው አካባቢ በባላባት መሆኑ ቀርቶ በቤተ መማክርት፣ ማለትም በሥራ አስኪያጅ ቡድን እንድትተዳደር ብለው ያወጡት ሕግ እንደማስረጃ ሊጠቀስ ይችላል። እንደዚሁም የወላይታ ባላባቶች በተራው ሕዝብ ላይ በደል ቢያበዙ፣ ሽረውዋቸው ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር በ፪ ሠኔ ፲፱፻ ዓ.ም. ያቋቊሙት የሹማምንቶች መማክርትም ሌላ ምሳሌ ነው5 ።
የገባር ሥሪት ባሕርይ በሰሜንም በደቡብም አንድ ዐይነት ሁኖ ሳለ፣ በኻያኛው ዘመን ላይ በደቡቡ ሥርዐት ሰፊ ለውጥ ታይቷል። ስለዚህም ልዩነቱ በአካባቢው የተከናውኑ የሥራዎች ውጤት እንጂ ከመንግሥት የታወጀ አዋጅ ወይንም የተወሰደ ያስተዳደር እርምጃ ያመጣው አልነበረም። የሰሜኑ ክፍል በሥልጣን ሱስኞች ባላባቶች በመበጥበጡ፣ ምንም ዐይነት የልማት ሥራ ሳይካሄድበት በቁመናው ሲቀር፣ በደቡብ የባቡር ሐዲድ መዘርጋትና የዘመናዊ እርሻ መስፋፋት ያመጡት ሀብትና ድሎት ባላባቱንም ሆነ የማእከላዊ መንግሥት ሹሞችን ስለተፈታተነ፣ ሁለቱ አንዳንዴ በመተባበር፣ አንዳንዴ ደግሞ በተናጠል ተራ ሕዝቡን እያባበሉም ሆነ እያዋከቡ፣ ወይንም ኀይል በመጠቀም መሬቱን እስከመንጠቅና ጥሎላቸው እስከሚሄድ አድርሰዉታል። ለምሳሌ አሩሲዎች ለከብታቸው ግጦሽ እስከሚያጡ ድረስ መሬታቸዉን አጥተዉት ነበር። አፄ ምኒልክና ተከታዮቻቸው ጊዜውና ዐቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን ከሕዝቡ ጐን ተሰልፈው፣ አንዳንዴ በአዋጅ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባለሥልጣኖቹን ሽረው ሌላ በመተካት፣ ሳይታክቱ እንደተዋጉ ሰፊ ማስረጃዎች አሉ።
አንድነትን ከመፍጠራቸው በፊት፣ ከላይ እንዳየነው፣ በየቦታው ይገዛ የነበረው የባላባቶች መንግሥት፣ የራሱን ሕዝብ ከታጐረበት ክልሉ ውስጥ እንዳይወጣ ሲያስገድድ፣ ከሌላው አካባቢ ወደሱ አገር የሚገባውን ደግሞ ብዙውን ጊዜ ለባርነት ስለሚፈልግ ተመልሶ ካገሩ እንዳይወጣ ይከለክል ነበር። አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዚህ ሁሉ የክልል መንግሥት አሰቃቂ ጭቈናና እሰር ነፃ አስወጥተው፣ በወደደበት እንደፈለገ እንዲኖር አድርገዋል። መጥፎ ልማዳቸውንም አንለቅም ላሉት እንደነጂማ አባጅፋር ዐይነቶቹ ባላባቶች ደግሞ፣ “ማንም ሰው እወደደበት ቦታ ላይ ይኖራል እንጂ … በምንም መልክ ልትይዘው አይገባም፤ ድኻው እወደደው፣ እተመቸው ቦታ ይደር[28]” ብለው የሰጡት ትእዛዝ ማንኛዉም የቅኝ ገዢ ያራምድ ከነበረው መርህ ጋር በጣም ተፃርራሪ ነበር ማለት ይቻላል።
እንግዴህ አፄዎቹ ይልቁንም አፄ ምኒልክ ያደረጉት ታላቅ ሥራ ቢኖር፣ በየቦታው በነዚህ አምባገነን ባላባቶቻቸውና፣ ንጉሥ ነን ባዮች ገዢዎቻቸው ሥር፣ እንደእስረኞች ከጠባቡ ግዛታቸው ውስጥ ታጉረው፣ በሚዘገንን ጭቈና ይማቅቁ የነበሩትን ኅብረተ-ሰቦች ነፃ አውጥተዋቸው፣ የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው ባሰኛቸው ቦታ እንዲኖሩ፣ የመላዋን ኢትዮጵያን ምድር ሀብታቸው ማድረጋቸው ነው። አፄ ምኒልክ ያዋሀዷት ኢትዮጵያ “የኅብረተ-ሰቦች እስር-ቤት ናት” ማለት ታሪክን ካለማወቅ ወይንም ከማጣመም የመነጨ ሲሆን፣ እውነቱ ግን ንጉሠነገሥቱ በባላባቶች ክልል ውስጥ ታስሮ የነበረውን ሕዝብ ነፃነት አቀናጅተውለት፣ በፈለገበት ሄዶ በእኩልነት እንዲኖር፣ በወደደውም የሥራ መስክ እንዲሰማራ አድርገዋል። በዚህም ሥራቸው መደነቅና መከበር ይኖርባቸዋል። በፈጠራ ታሪክ በመመሥረት ስማቸውን ማጒደፍ ደግሞ በታሪክ ያስጠይቃል[29]።
ይሁንና በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ደረጃ አንዳንድ ያስተዳደር ጕድለቶች መኖራቸው አይካድም። ቢሆንም ግን ያንድ የተወሰነ ዘውግ ወይንም የዘውግ አባል በመሆኑ ብቻ በይፋ የተንቋሸሸ፣ የተጨቈነና ዜግነቱን የተከለከለ፣ ከሥልጣንም ከዕድገትም የታገደ፣ ግለሰብም ሆነ ብሔርና ብሔረሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የለም። ከዚያም ባሻገር የኢትዮጵያ ሥልጣኔና መንግሥት ካንድ ብሔረሰብ ወይንም አካባቢ ጋር የተቈራኘ ሁኖም አያውቅም። ሌላው ቀርቶ በዘመነ-መሳፍንት ፈርሶ የነበረው የሕዝቡና ያገሩ አንድነት መልሶ በዘመናዊ መልኩ እንደ አንድ አገረ-ግዛት የተቋቋመው፣ በብዙ ጐን በተለያየ መልክ የተወጣጣና የተሰለፈ ብሔርንና ብሔረሰቦችን ባቀፈ ኀይል እንጂ፣ ካንድ ከተወሰነ አካባቢ ወይንም ጐሣ በመነጨ ጦር አልነበረም። አገሪቷና ሕዝቧም ይመሩ የነበሩት ለማንም ሳያዳላ ገንዘቡና ዐቅሙ በፈቀደው መጠን ሁሉንም በእኩል በሚያስተዳድር መንግሥት ስለነበር፣ አንዱን ዘውግ ከሌላው በተለየ፣ በላቀና በሞለቀቀ መልክ የሚገዛ ሕግም ልምድም ሁናቴም ባገሩ ውስጥ ከቶውኑ አልታየም።
ኢትዮጵያ ያቀፈችው አሁንም ቢሆን እንደጥንት የተለያየ ቋንቋ የሚናገርና ሃይማኖት የሚያመልክ የሕዝብ ሙዚዩም” ስትሆን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በበኩሉ የዚሁ ሕዝብ ጒንጒን ነው ማለት ይቻላል። አሁን ለሀገሬ ተቈርቋሪ ነኝ ከሚል ትውልድና ግለሰብ የሚጠበቀው፣ ባለፉት ያስተዳደር ጉድለቶችና በተደረጉት አለመግባብቶች ማትኰርና መወቃቀስ ፋይዳቢስ መሆኑን ዐውቆ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ነው። ጃገማ ኬሎ የተባሉት ሰመጥሩ ጄነራል አንዴ እንዳሉት፣ በአስተሳሰብም ሆነ በሙያ ዘርፍ ጠባብ በነበረው በጐሦችና በባላባቶች ዓለም ይኖሩ የነበሩት አባቶች፣ የጀብዱነታቸው መለኪያና ምልክት በሚጥሉት ግዳይ በሚያስቈጥሩት ሚርጋ የተመጠነ ነበር። በዛሬ ዘመን ግን የጀብዱ ሚርጋ የሚቈጠረው እያንዳንዱ ግለሰብ ለአገርና ለኅብረተ-ሰብ ዕድገትና ልማት በሚሠራው ሥራና በሚያበረክተው አስተዋፅዖ ነው። ከዚያም አልፎ በተሰማራው የሙያ ዘርፍ በሚያደርገው ፍልሰፋና ምርምር እኩዮቹን ሲያስከነዳና፣ ለዓለም ሕዝብ በጠቅላላ ጠቃሚ አገልግሎት ሲሰጥ ነው። አፄዎቹ ኢትዮጵያን አንድ አገር በማድረግ፣ ይኸንን ዓላማችን አድርገን ባገር ውስጥም ሆነ በዓለም መድረክ ላይ እንድናበረክት ዕድሉንና በሩን በሰፊው ከፍተዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እውድድሩ ሜዳ ውስጥ ገብቶ ድርሻውን ለገዛ አገሩም ለዓለምም መክፈል እንዲችል፣ ነገሥታቱ አመቺ ሁናቴ አደራጅተዋል። አገሩን አደላድለው ካበቁ በኋላ የዘመናዊ ሥልጣኔን መሠረት ጥለው ሜዳውን አመቻችተዋል።
ካርል ማርክስ እንዳለው ጐሣነት የበግ ዐይነት ስሜት ነው። በደመነፍስ ብቻ አንዱ ሌላውን ይከተላል። ሰው ግን የመራቀቅና አስፍቶ የማየት ልቡና አለው። እኔ ሁለዬ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፣ የዘውግና የክልል መስተዳድር አራማጆች ስብከታቸውን የሚያቀነቅኑት፣ ብዙዎቹ ወደፈለጉበት ሂደው እንዳሰኛቸው በሚኖሩበትና በሚሠሩበት በምዕራብ ዓለም ተቀምጠው ነው። እንዴት ነው እንደነዚህ ዐይነቶቹ በሰብኣዊ ልቡና የማይመራውን የጐሣንና የባላባቶችን ዓለም የሚያደንቁት። ለኔ እነዚህን ሁለቱን ማድነቅም ሆነ ከሞቱበት ለማንሣት መሞከር ከታሪክ ጋር ግብግብ መያያዝ ነው። አያዋጣም። እንዲሁም አፄዎቹን ራሳቸውን መውቀስ፣ ከሙት ጋር መሟገት ሰለሆነ ርባን የለዉም። የራስን ድርሻ መወጣትና ከአባቶችና ከፊተኛው ትውልድ የተረከቡትን አሻሽሎ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ግን በታሪክ የሚያስጠይቅ የያንዳንዱ ሰው ግዴታው ነው።
=====================
[1] . ዘውገኝነት ስል የጎሣ ፖሊትካን፣ በዓለም አቀፍነት ደግሞ የካርል ማርክስንና የቪላድሚር ሌኒንን ር እዮተ ዓለም የሚያተናፍሱትን ነው የማመለክተው። አብዛኞቹ ዛሬ ባገራችን ያሉት ጐሠኞችና ጐጠኞች [ወያኔዎችንና የፓለቲካ አጫፋሪያቸውን ኢሕአደግን ጭምር] የግራዘመም ፖሊትካ አራማጆች ነበሩ ማለት ይቻላል። ወደጠባብ ብሔርተኝነት የፈለሱት የግራው ርእዮተ ዓለማቸው ክሽፎባቸው ሲቀር ነው።
[2] . ይኸንን በመላዋ ጥቁር አፍሪቃ ውስጥ ከታነጹት ከተሞች ጋር ማነጻጻር ነው። ከኤርትራ ከተሞች ጀምሮ በመላዋ አፍሪቃ የተገነቡት ከተሞች በፈረንጆች እጅ ናቸው ማለት ይቻላል።
[3] . ይኸ ከአናቱ ላይ ያለው የንጉሡን ስም የሚገልጸው ወገን ከመግቢያ ተጐምዶ የጠፋበት ጽሑፍ በሦስተኛ ዘመን አካባቢ የተጻፈ ሲሆን፣ ንጉሡ በኻያ ሰባተኛ ዘመነ-መንግሥቱ ስፊ ድል የሰጡlለትን አማልክቱን ማለትም ዜውስን፣ ኤራስ [ጨረቃ]ንና፣ ጳሰይዶስን ሊያመሰግን ሲል ባቆመ ባንድ የዘውድ ቅርጽ ባለው ድንጋይ ላይ የተጻፈ ሐውልት ነው;፡ ንጉሥ አስገበርኋቸው የሚላቸው የአገሮች ዝርዝር በቅርብ ጊዜ ሊቅ ላጲሶ ድሌቦ [የድሮው ጌታሁን ድሌቦ] ለኢሳት ሬድዮ ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለምልልስ “የአክሱማያን ግዛት ከዛሬው ትግሬና ኤርትራ ክልል አያልፍም ብለው የተናገሩትን ያስተባብላል።
[4] . ያገሩ ስም አክሱም ይሁን ወይንም ሌላ ስም ይኑረው በግልጥ የሚታወቅ ነገር የለም። ግን በድሮ ዘመን ብዙውን ጊዜ አንዳንድ መንግሥታት የሚጠሩት በሚገዙት አገር ስም ሳይሆን ታዋቂነት ባላቸው መናገሻ ከተሞቻቸው እንደነበር፣ ባሁኑ ጊዜ በሱዳን ስም በሚጠራው ጥንት በግእዝ ካሱ፣ በዕብራይስጡ ኩሽ፣ በጽርዕ ደግሞ ‘ኢትዮጵያ” ከሚባለው አገር ልንገነዘብ እንችላለን። ካሱ በብዛት የሚታወቀው በየጊዜው በተከታታይ ገናናነትን ባተረፉ መናገሻ ከተሞቹ በቄርማ (2400-1570 ዓመተ ዓለም [ዓ.ዓ.)፣ በናጳታ (900-590 ዓ.ዓ.)ና በመርዌ (590 ዓ.ዓ. – 350 ዓመተ ምሕረት [ዓ.ም.] ነበር። የአክሱምም አጠራር ከዚህ ልምድ የተለየ ላይሆን ይችላል የሚለውን ግምት ከንግግሩ ውስጥ ማስገባቱ ተገቢ ይመስለኛል።
[5] . አረመኔ ጐሣዎች ወራሪዎቹ መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል ጀርመናውያን ቭሲጎቶችና ሂሩሎች፣ ሃኖችና ኦስትሮጎቶች፣ ዐረቦች ነበሩ። ወረራዎቹ ገብ እንዳሉ ኢጣሊያ በተለያዩ የየራሳቸው ገዢ ባላቸው ግዛቶች ተከፋፍላ ሕዝቡ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር በሰፊው ለመደበላለቅና ለመወላለድ እስከ፲፰፻፸፪ ዓ. ም. ድረስ ዕድል አልገጠመውም። ስለዚህ አሁንም ቢሆን ይልቁንም የሰሜኑና የደቡቡ ሕዝብ ሃይማኖቱ አንድ ቢሆንም በቋንቋና በባህል ባስተሳሰብ በጣም ይለያል።
[6] . የዱር አህያን ያላመዱት በቅሎንም ያስገኙት አገው ናቸው ተብሎ ይታመናል።
[7] . ጊዜው በፈረንጆች ታሪክ አገላለጽ
[8] . አማራ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ስሙ የሚነሣው ድግናጃን፣ ደጋዛንና ግዳዣን በመባል በተለያየ ስም የሚታወቅ የአክሱም ንጉሥ ከመናገሻው ወደመቶ ዐምሳ ሰባኪዎች ደብተራ ብሎ ከሠየማቸው በኋላ ሕዝቡን ወደክርስትና እምነት እንዲመልሱት ወደ”አማራ” ላከ በሚል ሰነድ ነው።
[9] . አገዎቹን የተካው ሰለሞናዊ ሥርወ-መንግሥት በሥልጣን ላይ በቈየው የዘመን ርዝመት አኳያ ለጊኒስ ቡክ ቢመረጥ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ያለምንም ክብረወሰን እንደሚያሸንፍ እርግጠና ነኝ። ያገዎች መንግሥት በጦር ሜዳ ቢሸነፍም፣ ታሪክ እንደሚነግረን ሥልጣኑን ለሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የለቀቀው በሽምግልና ተደራርድሮ ነው። ድርድሩም እንደ አ.አ. በሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዐምስት ዓ. ም. የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት እስከፈረሰ ድረስ ከመላጐደል ተከብሮ ቈይቷል።
[10] . ከደቡቡም ሕዝብ የወያኔ መንግሥት ይመሳሰላሉ ብሎ ያመናቸውን አንዳንድ ብሔረሰቦችን አጠራቅሞ “ወጋጋዳሶ” የሚል ቋንቋ ፈጥሮ የወል መታወቂያቸውና መጠሪያቸው እንዲሆን ሞክሮ ነበር። ግን ሕዝቡ በከፍተኛ ደረጃ በመቃወሙ ምርጫ አጥቶ ዕቅዱን ለሟሟላት ዐርባ ሚሊዮን ብር ቢያጠፋም ወደኋላ ማፈግፈግና መሰረዝ የግድ ሁኖበታል።
[11] ሊቅ ሙሐመድ ሐሰን በቅርቡ ባወጡት “ኦሮሞና ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ 1300-1700.” [Mohammed Hassen, The Oromo & The Christian Kingdom of Ethiopia, 1300-1700] መጽሐፋቸው የኦሮሞ ወረራ የተፈጸመው በሰላማዊ መንገድ ነው። በግራኝ ጦርነት አገሩ ተራቁቶ ስለነበር፣ ኦሮሞች በባዶው መሬት ሰተት ብለው ገቡ ይላሉ። ይሁንና አቋማቸው በጊዜው የነበሩት የውጭም የውስጥም አገር ጸሓፊዎች ከተውት ምስክርነት ጋር በግልጽ ይጋጫል ብቻ ሳይሆን እሳቸውም በተለያዩ በሌሎች ጽሑፎቻቸው እንዳደረጉ ሁሉ አሳማኝ የሆነ ተጨባጭ ማስረጃ አያቀርቡም።
[12] . አፄ ሠርፀድንግል እንደ አ.አ. በ፲፭፻፹ ዓ.ም. ድባርዋን የያዘውን ቱርክ እስተነአካቴው ከኢትዮጵያ ምድር ሊያባርሩት ይዘው ከሄዱት ጦር መካከል “የሰውን ደም ማፍሰስ የጠማው” የጋላ ጦር ነበር። Conti Rossini, trans. Ed., The Chronicle of Emperor Sarsa Dengel [Malak Sagad], p. 129
[13] . ትርጒሙ “የጽዮን ንጉሥና የኢትዮጵያ ነጉሠ-ነገሥት” ማለት ነው። ጽዮን የክርስቲያን እምነት የሚከተለውን የኢትዮጵያን ክፍል ሲያመለክት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የተለያየ እምነት የያዘውን አገር በሙሉ ያካትታል።
[14] . የንግሥ ስሟ አድማስ ሞገሳ የአፄ ዘርዐ-ያዕቆብ ባለቤት ነበሩ
[15] . ጸሓፊው አባቱ ከወረብ፣ እናቱ ከጐናን ምድር ሲሆን የተወለደው በመጤንት በደርኀ ምድር ነው ይላል። አንዳንድ ጸሓፊዎች ቦታዎቹ በወለጋ ውስጥ ይገኛሉ ቢሉም የተረጋገጠ ነገር የለም።
[16] . ገብረሕይወት ባይከዳኝ የማስተዋል ጸጋ የታደላቸው ታላቅ ምሁር ናቸው። ሕይወታቸው ባጭሩ ባይቀጭ ኖሮ፣ ላገራችን ብዙ ዕውቀት ባበረከቱ ነበር። ስለታሪክ ጸሓፊነት አስፈላጊ መስፈርቶች ሲናገሩ፣ ታሪክ መጻፍ በጣም አስቸጋሪ ሙያ ነው ብለው አበክረው ካስገነዘቡ በኋላ፣ መሟላት አለባቸው የሚሉትን ሦስት የሚቀጥሉትን ነገሮች ያማጥናሉ። አንደኛ፣ ድርጊቱን ለማስተዋል አመዛዛኝ ልቡና፤ ሁለተኛ፣ ድርጊቱን ለመፍረድ የማያዳላ አእምሮ፤ ሦስተኛ፣ያመዛዘኑትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ የጠራ የቋንቋ አገባብ ናቸው ይላሉ። የሚያሳዝነው ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁራን ነን ባዮች የገብረሕይወትን ምክር ለማሟላት ተቸግረዋል።
[17] . በቅርቡ ሊቀማእምራን (ዶር.) ሕዝቄል ኢብሳ “Ethiopia: An Oromo Dilemma. The National Question and Democratic Transition” በሚል ርእስ በድረገጾች ያሰራጩት ጽሑፍ፣ ባንድ በኩል በልጅ ኢያሱና በአባታቸው ንጉሥ ሚካኤል በሌላው ደግሞ በልጅ ተፈሪና (ኋላ አፄ ኀይለሥላሴ) በደጋፊዎቻቸው መካከል የተካሄደውን የሰገሌ ጦርነት በሚገርም መንገድ በወሎ ኦሮሞችና በሸዋ አማሮች እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። በሁለቱም በኩል የሚዋጉት አብዛኞቹ ኦሮሞች ወይንም የኦሮሞ ደም ያላቸው ሲሆን፣ ምሁሩ እንዴት አድርገው እንደዚህ ለመደምደም እንደበቁ አይናገሩም። ሊቁ በጀርመን አገር በታተመው በEncyclopedia Aethiopiaca ይልቁንም በኦሮሞ ታሪክ ዐምድ [vol. 4 O-X] ላይ በተጻፈው ብዙ የተዛባ ግንዛቤና አስቀምጠዋል። ጽሑፎቹ የሚከተሉት እንደነጆን ማርካኪስን [John Markakis] የመሰሉ ያገሩን ባህል ቀርቶ ቋንቋውን በፍጹም የማያውቁ ግራዘመም ምሁራንን ነው። እንደዚህ ዐይነቱ የታሪክ አተረጓጐም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ምሁራን ታሪክን የፖለቲካ ደንገጡር እንዳደረጓትና ምንስ ያህል የባዕዳን ቃል አስተጋቢዎች መሆናቸውን ነው።
[18] . ልክ ለ፲፫፻፹፰ ዓ. ም. ተለያይቶ የኖረ ሕዝብ ነበር ማለት ይቻላል።
[19] በኢጣሊያንኛ “politica periferica” ይሉታል።
[20] . በኢጣሊያንኛ “politica scioana e politica tigrina” በመባል ይታወቃል።
[21] . በአፄ ምኒልክ ብልሃትና ችሎታ “የትግሬና የሸዋ ፖሊትካ፣” ኢትዮጵያን ከመበታተን ይልቅ ኢጣሊያንን እትልቅ ሽንፈት ላይ ጣላት።
[22] . ዘገባው “ኀይሥላሴ እያካሄዳቸው ያሉት ሥራዎች እጅግ አስደናቂ ከመሆናቸው የተነሣ፣ ሁናቴው በዚህ መልኩ ከቀጠለ እስካሁን የምናውቃት ትላንት በጥንት ባህሏ ተዘፍቃ የነበረችው [ኢትዮጵያ]፣ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ወደከፍተኛ ዘመናዊ ሥልጣኔ ትደርሳለች” ብሎ ከደመደመ በኋላ፣ የዳር ፖሊትካ እንዳልሠራና በትጋት አጠናክሮ በግብር መተርጐም እንዳለበት ይናገራል።
[23] . መጽሐፉ ተሰሚነት ለማግኘት፣ “ኢትዮጵያውያን ግብረ-ገብ የሌላቸው፣ ክብረኅሊና የጐደላቸው፣ ምግባረ ብልሹና በተፈጥሯቸው ብስብስ የሆኑ ሕዝብ ናቸው። … የሚኖሩት በጉልተኛ ባላባት ሥርዐትና በባርያ ፍንገላ ነው። … አማሮች የተለያዩ ነገዶችን በብርቱ በመጨቈን ላይ ይገኛሉ፤ አገሪቷ የብዙ ሕዝቦች እስርቤት ናት” በማለት ኢጣልያኖች ይነዙ የነበሩትን ስብከት ያሰራጫል።
[24] . ሌሎቹ የኢጣሊያን ቅኝ ግዛቶች ባዲሱ መዋቅር ገብተው ከነስማቸው ሲቀጥሉ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ጠፍቶ፣ በካርታው ላይ የነበረው ስም የኢጣሊያን ምሥራቅ አፍሪቃ “Africa Orientale Italiana = አፍሪቻ ኦሪየንታሌ ኢታሊያና” ነበር።
[25] . በታሪክ እንደምናውቀው ሒትለር በአውሮጳ ወረራው ከያዛቸው አገሮች መካከል ነምሳ የመጀመርያዪቷ ነበረች።
[26] . “የጒልተኛ ባላባት” ሥርዐት ስል አውሮጳውያን ፊውዳሊዝም [feudalism] የሚሉትን ከሮማውያን ውድቀት ማግሥት ላይ የታየውን ሥርዐት ነው። የተማሪዎቹ ታላቁ ስሕተት አንደኛው የማኅበረሰብን ጥበብ [science] ልክ እንደሌላው የተፈጥሮ ጥበብ መልክ ማየታቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ በመምሰልና በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ባገባቡ አለመገንዘባቸው ነው። የኢትዮጵያ የመሬት ሥሪትና የምጣኔ ሀብት ቅርጽ ባንዳንድ ነገር ከአውሮጳውያኑ የጉልተኛ ባላባት ሥርዐት ይመሳሰላል። ግን በምንም መልኩ አንድ አይደለም። ባገራችን የባርያ ሥርዐት እንዳልነበረ ሁሉ፣ በማርክስ የተዋረድ እርከን ተከታዩ የነበረው የጉልተኛ ባላባት ሥርዐትም ከቶ አልነበረም።
[27] . የአፍሪቃን ቅኝ ገዚዎች የተካችው አሜሪቃ በቀዝቃዛ ጦርነትና በዐረብ-እስራኤል ግጭት ሰበብ ከሺ ዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ መጨረሻ ላይ ጀምሮ የነበራት መምርያ ከድሮው ከአውሮጳውያንን መርህ ብዙም የማይለይ እንደነበር የሚቀጥለው ክሲንጀር ለአሜሪቃ መንግሥት ያቀረበው ዘገባ የተወሰነም ቢሆን ጠቃሚ ፍንጭ ይሰጣል። “ኢትዮጵያ ሰላም ካገኘች፣ ሕዝቧ ሠራተኛና ታትሪ ሰለሆነ፣ በዓለም ብድር ዕዳም እንደሌሎቹ የሦስተኛ ዓለም አገሮች ተዘፍቃ የማታውቅና የኰራች አገር በመሆኗ አንድ ቀን አድጋ ራሷን የቻለች አገር ትሆናለች። ዕድል አግኝታ በዘመናዊ ሥልጣኔ ቢትገፋ፣ የሚትቻል አገር አይደለችም። ስለዚህ ከንጉሥ ኀይሌ ሥላሴ በኋላ ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት ሰላም እንዳያገኝና፣ አገሪቷም እንደዐረብ አገሮች ተከፋፍላና ተነጣጥላ ካልተበታተነች በስተቀር፣ ለወደፊቱ በቀይ ባሕር ላይ አሜሪቃ የሚትጫወተው ሚና እንዳይመነምን እንዳያድጉ ማደናቀፍ ከሚገባቸው በቀይ ባሕር አዋሳኝ ታዳጊ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆን አለባት። የቀይ ባሕር ወተት የሆነውን የዐረብን ነዳጅ በነፃ አለቀረጥ ማለብ የምንችለው፣ መንግሥታችን ኢትዮጵያን ከጎረቤቷ ከሱማሌ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ክፍለ ሀገሮቿን ራሳቸውን በሰሜንና በደቡብ ከፋፍሎ፣ የደከመውን ወገን በመርዳት፣ ያላመፀውን ጐሣ በማነሣሣት፣ ከዳር ድንበሯ ዘላለም ሁከትና ጦርነት እንዳይለያት በማድረግ፣ ፀረ-መንግሥት ተዋጊዎችን በሲአይኤ በማደራጀት በአገሪቷ ሰላም በመንሣት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንካራና ብርቱ ቢሆንም ቅሉ፣ በሥልጣን ፍላጎቱ ደካማ ጐን አለው። አንዱ በሌላው ላይ መንገሥ ዋና ምኞቱ ነው። በታሪካቸው ደሞክራሲያዊ መንግሥት መሥርተው አያውቁም። ከጥንት ጀምሮም ቢሆን አንዱ ንጉሥ ሌላውን በመግደል ሥልጣን መቀማትና ማመፅ ባህላቸው፣ ልማዳቸውና ታሪካቸዉም ነውና፣ እኛ ያሳደግነው ውሻም ቢሆን ሊነክሰን ቢሞክር በማስገልበጥ፣ ላንዲት ዘመን እንኳ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሰላም ሳይኖር፣ ሰሜናዊና ደቡባዊ፣ እንዲሁም ኤርትራ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ እየተባባሉ እርስ በርሳቸው ሳይስማሙ ለረጅም ጊዜ ከኖሩ፣ ቀይ ባሕር ለአሜሪቃ መንግሥት ጠቃሚ በር ሁኖ ይኖራል። ሱማሌና ኢትዮጵያ ሰላም ሁነው አንድ ቀን ከተባበሩ፣ የአሜሪቃ ታላቅነትና ብልፅግና በቀይ ባሕርና በዓለም ላይ አይኖርም። ኢትዮጵያና ሱማሌ እማዶ ካሉት የዐረብ አገሮች ጋር በቀይ ባሕር ጥቅም ላይ ተስማምተው ቢዋዋሉ፣ የአሜሪቃና የአውሮጳ ሕዝብ “ቡፋሎ” ፍለጋ ወደጫካ መሄድ ካልሆነ በስተቀር፣ ጥበባችንን እንኳን ሽጠንና ለውጠን ለመኖር እንችልም። ሊቃውንቶቻችን ወደአፍሪቃ ሲፈልሱ ከሩቁ ማየትና መገንዘብ የኛ ተራ እንደሚሆን አንርሳ።” (ይኸ አሳብ በዶክተር ሔንሪ ክሲንጀር “የቀይ ባሕር ለጦር ሰልት ያለው ጥቅም” በማለት ለመንግሥታቸው ያቀረቡት ጥናት ሲሆን የአሜሪቃ መንግሥት የፓለቲካ መርህ መሆኑን በየጊዜው የወሰዳቸው ርምጃ ይደግፈዋል።)
[28] . በቅኝ ግዛት ባሉት አገሮች ያገሩ ተወላጅ ሕዝብ ወደፈለገበት አካባቢ ሄዶ ለመኖርና ለመሥራት ከፈለገ ልዩ መታወቂያ ያስፈልገዋል።
[29] . እዚህ መነሣት የሚገባው የኦሮሞ ምሁራን ነን ባዮች ዘውገኞች በየቦታው የሚነዙት ስብከት ነው። በቅርቡ ደግሞ እንደነሊቀማእምራን ጌታሁን [ላጲሶ] ድሌቦ የመሰሉት ዐይነቶች ወደዚህ እምነት እንደገቡ ኢሳት በተባለው የብዙኃን መገናኛ በሰጡት አሳፋሪ ቃለመጠይቅ መገንዘብ ይቻላል [Getahun Lapiso Interview on ESAT Radio October 15, 2015]።
No comments:
Post a Comment