Monday, October 31, 2016

የዘረኝነት ወረርሽን ከአመት አመት እየተባባሰ፣ አገሪቱ እየተንሸራተተች ናት። (ቆንጂት ስጦታው)


የዘረኝነት ወረርሽን ከአመት አመት እየተባባሰ፣ አገሪቱ እየተንሸራተተች ናት። (ቆንጂት ስጦታው)
የዘረኝነት ወረርሽኝ፣ ተስፋ አስቆራጭና አስፈሪ የጨለማ ጉዞ የሚሆነው፤ ነገሩ ያን ያህል ውስብስብ ጉዳይ ስለሆነ አይደለም። የዘኝነትን አባዜ በቀላሉ አሽቀንጥረን ለማስወገድ አልቻልንም አስገራሚ ነገር ነው። ጭራሽ፣ በዝምድና የሚገናኙ መሆን አለመሆናቸው የማይታወቁ ሰዎችን (የአንድ ብሔረሰብ ተወላጆችን) በጅምላ እንፈርጃለን። ይሄም አልበቃም። ጭራሽ፣ ከመቶ ዓመት በፊት፣ … ከአምስት መቶ ዓመት በፊት፣ ከሚሌኒዬም በፊት የነበረ ንጉስና አልጋ ወራሽ፣ ወይም ደጃዝማቾችና ፊታውራሪ፣ አልያም ሰባኪና ፀሃፊ፣ ሽፍታና ዘራፊ… እየጠቀስን፣ አሁን በሕይወት ያሉ ሰዎችን፣ የጥፋትና የበደል ወራሽ እንዲሆኑ በዘር እየፈርጅንና እያቧደንን፣ አገሩን ቀውጢ ስናደርግ ይታያችሁ? እብደቱ፣ በሽታውና ወረርሽኙ የዚህን ያህል ከፍቷል።
 
ኢትዮጵያ በብዙ አይነት የጥፋት ፈተናዎች ውስጥ፣ ህልውናዋን ሙሉ ለሙሉ ሳታጣ ያለፈች አገር ብትሆንም፣ የበርካታ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ዝንባሌን ስትታዘቡ፣ የበርካታ ምሁራንና ዜጎች አዝማሚያ ስትመለከቱ… ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ፣ የዚህች አገር ነገር፣ተስፋ ያስቆርጣል። ከአመት አመት፣ የዘረኝነት ወረርሽኙ እየባሰበት፣ አገሪቱ ወደለየለት የጥፋት አዘቅት እንዳትሰምጥ አትሰጉም? በእርግጥ፣ አልፎ አልፎ፣ የዘረኝነት በሽታው፣ ለአፍታ ጋብ ሲልለት… እሳቱም ትንሽ ሲበርድለት እያየን፣ የእፎይታና የተስፋ ስሜት እናገኛለን። ግን፣ እፎይታው ብዙም አይቆይም።
 
እንደገና በሽታው ያገረሸበታል። ማገርሸት ብቻ አይደለም። ከእያንዳንዱ እፎይታ በኋላ፣ ወረርሽኙ ባገረሸ ቁጥር፣ ከቀድሞው እጅጉን ብሶበት እናገኘዋለን። ተስፋ አስቆራጩና አስፈሪው ነገር ደግሞ ምን መሰላችሁ? የዘረኝነት ወረርሽኙን ለማስቆም የሚያስችል፣ አስተማማኝ መላ ምን እንደሆነ በግልፅ ጎልቶ አለመታየቱ ነው። ዙሪያው ሁሉ በጨለማ የተዋጠ ጉዞ ይመስላል። (ቆንጂት ስጦታው)

No comments:

Post a Comment