Friday, October 21, 2016

የጎንደር የስራ ማቆም አድማ በአመርቂ ሁኔታ ተጠናቀቀ


የጎንደር የስራ ማቆም አድማ በአመርቂ ሁኔታ ተጠናቀቀ
የጎንደር ህዝብ ከሶስት ቀናት በፊት የጀመረውን የስራ ማቆም አድማ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁ ተነገረ፡፡ በከፍተኛ ወታደራዊ ጫና ውስጥ ሆኖ አድማውን ሲያከናውን የዘለቀው የከተማዋ ነዋሪ፣ የአድማው ዓላማም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በጽኑ መቃወም እንደሆነም ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ከፍተኛ ህዝባዊ እምቢተኝነት ሲያስተናግድ የከረመው ጎንደር ከተማ፣ በተለይ የተለያዩ አድማዎችን በማድረግ ስርዓቱን ሲፈትን ቆይቷል፡፡
የሶስት ቀናቱን አድማ ተከትሎም በርከት ያሉ አጋዚ ወታደሮች በአድማው ምክንያት የተዘጉትን የከተማዋን የንግድ መደብሮች ለማስከፈት ኃይል የተቀላቀለበት እርምጅ እስከመውሰድ የዘለቀ ሙከራ ማድረጋቸውን የሚገልጹት የአድማው ተሳታፊ ነዋሪዎች፣ የወታደሮቹ ጫና ከባድ ቢሆንም አድማውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ወቅቶች በሌሎች የትግል ስልቶች እንደሚከሰቱ ከወዲሁ የተናገሩት የከተማዋ ናዋሪዎች፣ ወደፊት በምን ዓይነት የትግል ስልት ብቅ እንደሚሉ በየጊዜው እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሀገሪቱ እየተካሔደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመግታት ተብሎ ይፋ መደረጉን እንደሚያምኑ የሚገልጹት እነዚሁ ነዋሪዎች፣ የተጀመረው ህዝባዊ ትግልም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል፡፡

No comments:

Post a Comment