Monday, October 31, 2016

የውጭ ሃገር ባንኮች በብድር ማቅረብ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ተገለጸ – ኢሳት


የውጭ ሃገር ባንኮች በብድር ማቅረብ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ተገለጸ – ኢሳት
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማገዝ ወደ ሃገሪቱ የገቡ የውጭ ሃገር ባንኮች በብድር ማቅረብ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ተገለጸ።
የደቡብ አፍሪካ፣ የቱርክ፣ የኬንያና፣ የአውሮፓ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማገዝ ይችሉ ዘንድ በቅርቡ በብሄራዊ ባንክ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ይታወሳል።
ስታንዳርድ የተሰኘ የደቡብ አፍሪካ ባንክ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያካሄደ ያለውን ስራ ለመደገፍ የ100 ሚሊዮን ዶላር (ከ2 ቢሊዮን ብር) በላይ ብድር ማቅረቡን ይፋ እንዳደረገ አፍሪካ ቢዝነስ የተሰኘ መጽሄት ዘግቧል።
የአለም ባንክ በበኩሉ የሃገሪቱ አጠቃላይ የብድር መጠን ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ ከሃገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት 55 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንደያዘ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት አጋጥሞት ያለውን ይህንኑ የውጭ ብድር እዳ ለመቀነስ የፖሊሲ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፈው አመት ብቻ ሃገሪቱ ወደ አራት ቢሊዮን የሚደርስ የብድር ስምምነትን የፈጸመች ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የብድር መጠንም ከ36 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ለመረዳት ተችሏል።
የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ በባንክ ስራ እንዲሰማራ ፈቃድን ካገኘ በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለብድር ሲያቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን አፍሪካ ቢዝነስ በዘገባ አስፍሯል።
ይሁንና ባንኩ ያቀረበው ብድር ምን ያህል ወለድ እንደሚከፈልበትና የመክፈያ ጊዜ መጠኑ ያልተገለጸ ሲሆን፣ ሌሎች የውጭ ሃገር ባንኮችም ለተለያዩ መንግስታዊ ፕሮጄክቶች ብድር እያቀረቡ መሆናቸው ታውቋል።
ይሁንና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ሃገሪቱ ከመጠን ያለፈ ዕዳ ውስጥ መግባቷ ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል አሳስበዋል።
መንግስት ለብድር የሚከፍለው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን ችግር ከማባባስ በተጨማሪ ለሃገሪቱ የዋጋ ግሽበት አስተዋጽዖ ማድረጉን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፈው አመት ብቻ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር መውሰዱ ታውቋል።

No comments:

Post a Comment