Thursday, March 9, 2017

አብዮተኞቹ በታሪክ ውስጥ – በጥበቡ በለጠ ሳተናው




የካቲት ወር በኢትዮጵያ ውስጥ ባለታሪክ ነው። የየካቲት አብዮት እየተባለ በታሪክ ውስጥ ይነገራል። ያ አብዮት 43 አመት ሆነው። ያ አብዮትን የሚያስታውሱ መጻሕፍትም ከ43 በላይ ሆነዋል። የካቲት ወር ማለቂያው ላይ ሆነን ወደ ኋላ ሄደን የኢትጵያን አብዮት በጥቂቱ እናስታውሰው። የኛ ታሪክ ነው። ያለቅንበት፣ የደማንበት፣ ብዙ ሰው የተሰደደበት፣ ምስቅልቅል የተጀመረበት ወር ነው። እናም ትንሽ ብንጫወትስ?
በኢትዮጵያ ውስጥ 1966 ዓ.ም “አብዮት ፈነዳ” ተባለ። የፈነዳው አብዮት አዲስ ስርዓት እንዲመሠረት የሚጠይቅ ነው። ሦስት ሺ ዓመታት ያህል በስልጣን ላይ ቆይቷል የተባለው ሰለሞናዊው የንግስና ዘመን ተገረሠሠ ተባለ። የመጨረሻው የሰለሞናዊ አገዛዝ መሪ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከመንበረ ስልጣናቸው ወረዱ። ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር (ደርግ) የሀገሪቱን አመራር ያዘው። ወጣቱ ደግሞ መሬት ለአራሹ ብሎ ዘምሮ ያመጣው ለውጥ በደርግ ወታደሮች ተቀማሁ ብሎ በኢሕአፓ ሥር ተደራጅቶ ከከተማ እስከ ጫካ ድረስ የትጥቅ ትግል ውስጥ ገባ። ሌሎችም ፓርቲዎች ደርግን ለመዋጋት ተፈጠሩ። በዘር፣ በሃይማኖት እና ኅብረ ብሔራዊ ሆነው የተደራጁ ፓርቲዎች መጡ። 17 ዓመታት አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ ለመሆን የማያቋርጥ ጦርነት ተከፈተ። ኢትዮጵያዊያኖች በአያሌው ደማቸው ፈሰሰ። ህይወት ጠፋ። ለውጥ በመምጣቱ ምክንያት ትውልድ ረገፈ። የመጣው ለውጥ በተደራጀ መልኩ ባለመያዙ የትውልድ ሰቆቃ ታይቶበት እንዳለፈ ፀሐፍት ያስረዳሉ።

ለመሆኑ አብዮት የት እና መቼ መቀጣጠል ጀመረ ተብሎ መጠየቁ አይቀርም። የኢትዮጵያ አብዮት መቀጣጠል የጀመረው በስነ-ጽሁፍ ውስጥ እንደሆነ የሚያስረዱ አያሌ መዛግብት አሉ። እነዚህ አብዮታዊ ሥነ-ጽሁፎች መውጣት የጀመሩት ደግሞ 1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እንደሆነም ይጠቀሳል።

አብዮት አቀጣጣዩ ትውልድ ብቅ ያለው ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ ት/ቤት ገብቶ የተማረው ነው። በ1930ዎቹ አጋማሽ ውስጥ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የሰጡበት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜም ወደ ተማሪ ቤት የገቡት ልጆች አያሌ ድጋፍ እያገኙ መማር ጀመሩ። እነዚህ ትውልዶች በ1950ዎቹ ውስጥ ትምህርታቸውን እያጠናቀቁ በልዩ ልዩ የሙያ መስክ ውስጥ መሰማራት ጀመሩ። እጅግ የካበተ የሥነ-ጽሁፍ ችሎታ ያላቸው ደራሲያን የተፈጠሩበት ዘመን ሆነ። በስዕል፣ በሙዚቃ፣ በጋዜጠኝነት እና በሁሉም የሙያ መስኰች ጥሩ እውቀት ያላቸው ወጣቶች ብቅ አሉ።

በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ የአብዮት አቀጣጣይ ሆነው ብቅ ካሉት ፀሐፍት መካከል አንዱ ፀጋዬ ገ/መድህን ነው። ፀጋዬ አንድ የቆየን ታሪክ በከፍተኛ ሁኔታ ቀየረው። ይህም የአፄ ቴዎድሮስን የህይወት ታሪክ ነው። ከፀጋዬ በፊት የነበሩት አያሌ ፀሐፍት አፄ ቴዎድሮስን የሳሏቸው ጨካኝ፣ ብዙ ሰው የገደሉ፣ ትዕግስት የሌላቸው እና ብዙ ጥፋት ሰርተው ያለፉ ንጉስ መሆናቸውን ይገልፁ ነበር። በ1940ዎቹ መጨረሻ ግን ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሃዋርያት “ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማ” የተሰኘ ቴአትር ፃፉ። ይሄ ቴአትር ቴዎድሮስ ራዕይ የነበራቸው ጠንካራ ንጉስ መሆናቸውን አሳየ። ከዚህ በኋላ ደግሞ ፀጋዬ ገ/መድህን ቴዎድሮስ ፍፁም ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ኢትዮጵያን በአንድነትና በስልጣኔ ሊያራምዱ ቆርጠው የተነሱ፣ የለውጥ ሐዋርያ የሆኑ የጀግንነት ተምሳሌት ናቸው በሚል ቴዎድሮስን ሰማየ ሰማያት አድርጐ አቀረባቸው።

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የቴዎድሮስ ታሪክ እምብዛም አይነገርም ነበር። ምክንያቱም ቴዎድሮስ ከሰለሞናዊያን ነገስታት የዘር ሐረግ የላቸውም። ከሽፍትነት ተነስተው አሸንፈው ንጉስ የሆኑ ናቸው። ስለዚህ በዘር ሐረግ ስልጣን በሚተላለፍበት ዓለም ቴዎድሮስ ጥሩ ምሳሌ አይደሉም። ሽፍታ ሀገር መምራት ይችላል የሚል ትርጓሜ ያሰጣል። አንድ ሰው ጫካ ገብቶ (ሸፍቶ) ከተዋጋ እንደ ቴዎድሮስ መንግስት መሆን ይችላል። ስለዚህ በዘመነ አፄ ኃይለሥላሴ ቴዎድሮስን ማቆለጳጰስ ስርዓቱን እንደመቃወም ሁሉ የሚቆጠርበት ሁኔታም ይታያል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ፀጋዬ የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ለትውልድ ሁሉ አርአያ እንደሚሆን አድርጐ የፃፈው።

ፀጋዬ በአፄ ቴዎድሮስ በኩል ትግልን፣ ፅናትን፣ ሀገርን መውደድ፣ ለሀገርም መስዋዕት መሆንን ሁሉ አስተማረበት። በወቅቱ አዲስ አስተሳሰብ በትውልድ ውስጥ የሚዘራ አፃፃፍ ነው። ቴዎድሮስን ብሔራዊ አርማ የማድረግ አቀራረብ ተጀመረ። አፄ ቴዎድሮስ የትግል መማሪያ ሆኑ።

ልክ እንደ ፀጋዬ ገ/መድህን ሁሉ ብርሃኑ ዘሪሁንም ቴዎድሮስን ብሔራዊ አርማ አድርጐ ፃፋቸው። የብርሃኑ ቴአትር “የቴዎድሮስ ዕንባ” ይሰኛል። ብርሃኑም በራሱ ውብ የአፃፃፍ ቴክኒኩ ታላቁን አፄ ቴዎድሮስ የጀግኖች ሁሉ ቁንጮ አድርጐ አቀረበው። ቴዎድሮስ ሰዎችን ይቀጡ የነበሩት ጨካኝ ስለሆኑ ሳይሆን ሀገራቸውን በጣም ስለሚወዱ ነው። በሀገር ላይ ጥፋት የሰራን ሰው አማላጅ የላቸውም፤ ይቀጣሉ፤ ይገድላሉ። እነዚህ ላይ አትኩሮ ታላቁ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ፃፈ።

ከነ ፀጋዬ በፊት በነበሩት ፀሐፍት እንደ ሽፍታ እና ጨካኝ መሪ ይታዩ የነበሩት ቴዎድሮስ፣ አሁን ርህራሄያቸው እና አዛኝነታቸው እንዲሁም አርቆ አሳቢነታቸው እየተገለጠ መታየት ጀመረ። ለምሳሌ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ መጥተው፣ የሸዋን መንግስት ከጣሉ በኋላ የ12 ዓመት ልጅ የነበሩትን የንጉስ ልጅ (ምኒልክን) ማርከው አልገደሏቸውም። የጠላቶቼ ልጅ ነው ብለው አላሰቃዪዋቸውም። ከቴዎድሮስ በፊት የነበሩት ነገሰታት ልጆቻቸው ስልጣናቸውን እንዳይወርሷቸው ሁሉ ይጠነቀቁ ነበር። ቴዎድሮስ ግን የጠላቶቼ ልጅ ነው ብሎ ሳያስብ ምኒልክን ወደ ጐንደር ወስዶት እንደ ራሱ ልጅ በስርዓት አሳደገው። “ወደፊት ኢትዮጵያን የምትመራ አንተ ነህ” ብሎ አስተማረው። ስለዚህ ቴዎድሮስ ጨካኝ መሪ ሳይሆን ልበ ቀና ሆኖ ኢትዮጵያን የሚወድ ነው እያሉ እነ ፀጋዬ ገ/መድህን ፃፉ።

ይሄን የአፃፃፍ መንገዳቸውን የበለጠ ተወዳጅ ያደረገ ደራሲ ደግሞ ብቅ አለ። አቤ ጉበኛ ነው። ስለ አፄ ቴዎድሮስ ማንነት የምርጦች ምርጥ የሚሰኝ መጽሐፍ በ1950ዎቹ ውስጥ አሳተመ። የመጽሐፉ ርዕስ አንድ ለእናቱ ይሰኛል። ታሪካዊ ልቦለድ ነው። የቴዎድሮስን ማንነት ከውልደት እስከ ፍፃሜ ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ ነው። የአቤ ጉበኛ አፃፃፍ ቀላል እና ማራኪ በመሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ቴዎድሮስ እንዲሸሸግ አደረገ። ‘ቴዎድሮሳዊነት’ እንደ ፍልስፍና ብቅ አለ። ታግሎ ማሸነፍ፣ ተደራጅቶ መነሳት፣ አለመፍራት፣ ወዘተን ማስተማሪያ ሆነ። ቴዎድሮሳዊነት የለውጥ ማቀንቀኛ ሆኖ ወጣ!
ይህን የእነ ፀጋዬ ገ/መድህንን፣ የእነ ብርሃኑ ዘሪሁንን፣ የእነ አቤ ጉበኛን እንዲሁም የደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያት አፃፃፍን መሠረት አድርጐ ታላቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ በዚያን ዘመን አንድ ሰፊ መጣጥፍ (ሂስ) ፃፈ። ጽሁፉ የሚያተኩረው ቴዎድሮስ ከ100 ዓመት በኋላ በእነ ፀጋዬ ገ/መድህን አማካይነት እንደገና መወለዱን ነው። እነዚህ ደራሲያን ያልታየውን ቴዎድሮስ ፈጠሩት እያለ አቆለጳጰሳቸው።
የለውጥ ማቀጣጠያ ጀግና ተፈጠረ። ቴዎድሮስ ፍልስፍና ሆኖ መታገያ ማታገያ እየሆነ መጣ። በዚሁ ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብዕሮች ስለ የለውጥ ማቀጣጠያ ቀለም መትፋት ጀመሩ። ዮሐንስ አድማሱ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው)፣ ኢብሳ ጉተማ፣ ታምሩ ፈይሣ፣ አበበ ወርቄ፣ ይልማ ከበደ እና ሌሎችም በርካታ ገጣሚያን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አብዮት አቀጣጣይ ግጥሞችን መፃፍ ጀመሩ። ዘመኑም ከ1953 ዓ.ም በኋላ ነው።
“የዩኒቨርሲቲ ቀን” ተብሎ በተሰየመው ዕለት የግጥም “ናዳዎች” መቅረብ ጀመሩ። ግጥሞቹ በዘመኑ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚነሱትን ልዩ ልዩ ችግሮች እያነሱ የሚያቀጣጥሉ ናቸው። ግጥሞቹ ሲነበቡ በተማሪው ዘንድ ከፍተኛ የጭብጨባ እና የድጋፍ ድምፅ ይሰነዘር ነበር። ለምሳሌ በ1953 ዓ.ም ታመሩ ፈይሳ የተባለ የዩኒቨርሲቲ ገጣሚ ለተማሪዎች ያቀረበው ግጥም ከዳር እስከ ዳር እንዳነቃነቀ እማኞች ያስረዳሉ። የታምሩ ግጥም “ደሃው ይናገራል” የሚል ርዕስ ነበራት። እንዲህም ትላለች፤
ግማሽ ጋሬ እንጀራ እጐሰጉስና
አንድ አቦሬ ውሃ አደሽ አደርግና
ሣር እመደቤ ላይ እጐዘጉዝና
ድሪቶ ደርቤ እፈነደስና
ተመስገን እላለሁ ኑሮ ተገኘና
ጮማና ፍሪዳ የት ነው የማውቀው
እንዲሁ አሸር ባሸር ሆዴን አመሰው
የእግዜር ፍጡር ነው ትላላችሁ ወይ
ምስጥ የበላው ዝግባ መስዬ ስታይ
ይህችም ኑሮ ሆና በጉንፋን አሳቦ
ከዚሁ ገላዬ፣ ከዚሁ አካላቴ፣ ከዝችው አቅም
ልክ እንቧይ ያህላሉ ቁንጫና፣ ትኋን፣ ቅማል በእኔ ደም!
እያለ ታምሩ ገጠመ። የለውጥ ቋፍ ላይ የነበረው ተማሪ ደስታውን አስተጋባ። ኢብሳ ጉተማ የተባለ ገጣሚም በይዘቷ ለየት ያለች ግጥም አቀረበ። ርዕሷ “ኢትዮጵያዊ ማን ነው?” የሚል ነበር። አንዳንድ ሰዎች ግጥማ ዘመን አይሽሬ ናት። ኢብሳ ጉተማ ግን ዘመን ሽሮት የአንድ ፓርቲ አባል ሆነ እያሉ ይገልፃሉ። የግጥሟ ከፊል ገፅታ እንዲህ ይላል።
ያገር ፍቅር መንፈስ ያደረበት ሁሉ
ማንነቱን ሳያውቅ በመንቀዋለሉ
ማነኝ ብሏችኋል መልሱን ቶሎ በሉ፣
እናንተ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ ማን ነው?
ከሆዱ ያበጠ ቦርጫም መኰንን ነው?
ወይስ ኰሰስ ያለው መናጢ ድሃ ነው?
ላቡን አንጠፍጥፎ ከመሬት ተታግሎ
ካገኘውም ሰብል ለጌቶች አካፍሎ
ለራሱ ከእጅ ወደ አፍ የሚያስቀረው ነው?
በሉ እስቲ ንገሩኝ ኢትዮጵያዊ ማን ነው?
የመንግስቱ ደም ስር የህዝቡ አከርካሪ
በመከራ ጊዜያት አደጋ ከማሪ
በሰላም ወራት ሌሎችን አኩሪ
ገበሬው ነው ወይ የመታው ሐሩር?
ኢትዮጵያ ለእናንተ የማናት ሀገር?
ወሎዬ ነው አማራው ትግሬ ነው ጉራጌ?
ወላይታ ነው ኰንታው አኙዋኩ ነው ጉጂው?
ጭንቅ ብሎኛል ኢትዮጵያዊ ማን ነው?
ወጣት ሽማግሌው አገር ሲጠየቅ
አንዱ ጐጃም ነኝ ሲል ሌላው በጌምድር
አንዱ ኤርትራ ሲል ሌላው ተጉለት
አንዱ መንዝ ነኝ ሲል ሌላው ጋሙ ጐፋ
ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ ብፈልገው ጠፋ።
እስቲ አዋቂዎች እናንተ ንገሩኝ
እኔን ያስጨነቀው ኢትዮጵያዊ ማን ነው?
ኢብሳ ጉተማ እንዲህ ያለ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ ነበር። ይህ ኢትዮጵያዊነቱ በ1950ዎቹ መግቢያ ላይ እየተንተገተገ ፈልቶ ነበር። ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያም በዚህ ግጥም ውስጥ ትታያለች። ግን በዘመኗ አብዮት አቀጣጣይ ግጥም ነበረች። ሀሳቧ ዘላለማዊ ነው።
በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከተነሱት አብዮት አቀጣጣይ ትውልዶች አንዱ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ነው። ዛሬም ድረስ በስደት የሚንከራተተው ይህ ገጣሚ በ1954 ዓ.ም ትንታግ እና የሚቀጣጠል ግጥም ፅፎ በትውልድ ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ሆኖ እየኖረ ነው። ኃይሉ “በረከተ መርግም” የተሰኘ ረጅም ግጥም ፅፏል። በዚህ ግጥም ውስጥ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የፈለሰፉ ጠቢባንን የርግማን ናዳ ያወርድባቸዋል። እርግማኑ የሚያተኩረው ለሰው ልጅ ጥቅም የማይሰጥ ፍልስፍና ድራሹ ይጥፋ እያለ ነው። ግጥሙ ረጅም ነው። በጣም ጠቂቱ ይህን ይመስላል፤
ሆኖም ምስጢሩ፣ ባይገባንም ለአያሌ ዘመናት
በአንክሮ ምጥቀት፤ ስናየው የኖርነው
ሲነድ ሲቃጠል፣ የሚስቅ እሣት ነው
ርግጥ ነው ክብሯን እውነት ነው ክብሯት
እኔ በበኩሌ አልወድም ነበረ ሰውን ያህል ፍጡር
ዳዊትና ዳርዊን ያፀደቁለትን ያንን ትልቁን ትል
መወረፍ መጣቆስ
ከምን ልጀምር፣ ከየትስ ልነሳ
በየግንባሩ ላይ ለጥፎ ለመኖር የትዝብት ወቀሳ
አዎን የተዛባን መንፈስ ያጐበጠ ኑሮ
የገለማን ህይወት፣ ምክንያቱ ሆነው ካስገኙ በዓለም
ተራው ምን አደረገ ሊቆቹን ነው መርገም።
እያለ የእርግማን አይነት ያወርዳል። የቀረው ሳይንቲሰት፣ የቀረው ፈላስፋ የለም። ኃይሉ ትልቅ ባለቅኔ ነበር። ደርግ ሲመጣ የተሰደደ እስከ ዛሬ አልተመለሰም። ወጥቶ የቀረው ባለቅኔያችን ነው። መቼ ይሆን የሚመጣው?
ሌላኛው አብዮት አቀጣጣይ ገጣሚ ዳኛቸው ወርቁ ነው። ዛሬ በህይወት የሌለው ዳኛቸው ከፍተኛ የሥነ-ጽሑፍ ችሎታ ያለው ምሁር ነው። የበርካታ መፃህፍት ደራሲ የሆነው ይህ ከያኒ በ1954 ዓ.ም “እምቧ በሉ ሰዎች” የሚሰኝ ረጅም ግጥም ጽፏል። 33 ገፅ የሆነው ይህ ግጥም ህዝብን የመቀስቀስ እና የማነሳሳት ባህሪ በስፋት አለው። “የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ካልተማርክ፣ ካላወክ፣ ካልተመራመርክ…. እንደ ከብቶቹ እምቧ በል” እያለ በሁለት በኩል በተሳለ የግጥም ቢለዋ ያስፈራራል። እናም ለእውቀት ተነስ! ወደ ኋላ አትበል ይላል፤
በድሎት ላሽቀን
መስራትም ማሰራት
ሁሉንም ካቃተን፣
ምነው ምናለበት
የፍጥፍጥ ሄደን
ያሮጌ ዓለም ህዝቦች
ብሎ ሰው ቢያውቀን
ሰው ሁሉ ሰልጥኖ ስልጣኔ ሲረክስ
ሌላ ዓለም ፈልጐ ባየር ላይ ሲፈስ
ደስታ አይደለም ወይ ለታሪክ መቅረት
እንደኛ ደንቆሮ ሆኖ መገኘት
እነዚህ ገጣሚያን በወጣትነት ያፍላ ዘመናቸው ለውጥ እያቀጣጠሉ የመጡ ናቸው። ዛሬ ወደ አሜሪካን ሀገር የሸሹት የሕግ ባለሙያው አበበ ወርቄም በ1958 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ምላሴን ተውልኝ የሚልየዴሞክራሲ ጥያቄ ያነገበች ግጥም ፅፈዋል።
ከ1953 ነበልባል ከሆነው ትውልድ ውስጥ ጐልቶ የሚጠቀሰው ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ነው። የእርሱም ግጥሞች ኢትዮጵያን ለመቀየር ቆስቋሽ የሆኑ ጠንካራ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያነሱ ናቸው። እንዲህ እያለ ጉዞው ቀጠለ። መሬት ለአራሹ መጣ። የተማሪ አመፅ መጣ። የሰራተኛው፣ የጦር ኃይሉ አመፅ… እያለ ቀጠለ።
“አትነሳም ወይ አትነሳም ወይ
ይህች ባንዲራ ያንተ አይደለችም ወይ”
ተባለ።
ፋኖ ተሰማራ
ፋኖ ተሰማራ
እንደ ሆቺ ሜኒ
እንደቼኩ ቬራ
አብዮት ተቀጣጥሎ ምርጥ የኢትዮጵያን ወጣት ልጆች ፈጅቶ ሄደ። የካቲት እንዲህ አይነት ታሪክ አላት። ብዙዎች ስለ የካቲት ጽፈዋል።

Related posts:


No comments:

Post a Comment