Saturday, March 11, 2017

ድርቁ መቶ ሺዎችን አፈናቅሏል፤ ከ250 ሺ በላይ ህፃናት ትምህርት አቋርጠዋል

   


ድርቁን ተከትሎ አስከፊ ረሀብ ሊከሰት እንደሚችል ተመድ አስጠንቅቋል
መንግሥት የእርዳታ ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም
እስከ 15 ሺህ ብር ይሸጡ የነበሩ ከብቶች፣ 500 ብር ድረስ እየተሸጡ ነው
Addis Admass
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የድርቅ አደጋ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን ከሩብ ሚሊዮን በላይ ህፃናት ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ውጪ ማድረጉንም የተባበሩት መንግስታት የእርዳታና የሰብአዊ ድጋፍ ድርጅት (UNOCHA) ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው የኦሮሚያ ክልል፣ ቦረና ዞን ያሉ አርሶ አደሮች በህይወት የተረፉ ከብቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ እየሸጡ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ድርቅ ባጠቃቸው የቦረና አካባቢዎች በጉዳዩ ላይ ጥናት በማድረግ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በደህናው ጊዜ እስከ 15 ሺህ ብር ይሸጡ የነበሩ በሬዎች፤ በአሁን ወቅት ከ500 እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጡ ሲሆን ከ500 እስከ 1 ሺህ 500 ብር ይሸጡ የነበሩ በጎችና ፍየሎች ደግሞ በ80 እና በ90 ብር እየተሸጡ ነው ተብሏል፡፡
ከብቶቹ በአብዛኛው በአካላዊ ቁመናቸው የተጎዱ በመሆኑ፣ ፈላጊ ስለሌላቸው አርብቶ አደሮቹ በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ባለሙያዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡፡፡
የከብቶች ሞትም እንደቀጠለ መሆኑን የጠቆሙት አጥኚዎች በተለይ የመጠጥ ውሃ ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን ገልፀው፤ መንግስት በቦቴ ውሃ እያቀረበ ቢሆንም በበቂ መጠን አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
ወቅታዊ ሪፖርቱን ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ፤ በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የሚሊዮኖችን ህይወት አደጋ ላይ ለጣለው ድርቅ መንግስትና የእርዳታ ለጋሽ ተቋማት ውሃና ምግብ በማቅረብ እየተረባረቡ ቢሆንም ከአደጋው አስከፊነት አንፃር በቂ አይደለም ብሏል፡፡
በድርቁ ምክንያት 228 ሺህ ህፃናት ትምህርት ማቋረጣቸውን ይፋ ያደረገው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህ ውስጥ 183 ሺህ 090 የሶማሌ ክልል ህፃናት ሲሆኑ 44 ሺህ 571 የሚሆኑት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ በድርቁ ምክንያት 141 ት/ቤቶች፣ በሶማሌ ክልል 437 ት/ቤቶች በድምሩ 578 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ምግብና ውሃ ፍለጋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባወራዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን የጠቆመው የተመድ የእርዳታና ሰብአዊ ድጋፍ ድርጅት ሪፖርቱ፤ ከተፈናቀሉት ውስጥ 163 ሺህ ያህሉ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ እነዚህን ተፈናቃይ ህፃናት ለ75 ቀናት ሊመመገብ 5.9 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡
በእርዳታ አሰጣት ደንብ ለአንድ ሰው በቀን ውስጥ 5 ሊትር ውሃ መቅረብ ያለበት ቢሆንም በአሁን ወቅት ለአንድ ሰው በቀን እየቀረበ ያለው በአማካይ 2.1 ሊትር ውሃ መሆኑን የተመድ ሪፖርት ጠቁሞ፤ የውሃ ክፍፍሉም ፍትሃዊ አለመሆኑንና ከወረዳ ወረዳ እንደሚለያይ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ለ5.6 ሚሊዮን የተረጂዎች 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ እንደሚያስፈልግና ይህ እርዳታ በአፋጣኝ ካልተገኘ ሁኔታው ወደ አስከፊ ረሃብ ሊቀየር እንደሚችል አሳስቧል፡፡
ተመድ መንግስት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን የእርዳታ ርብርብ እያደረጉ ነው ቢልም መንግስት በበኩሉ፤ ለድርቁ አደጋ የእርዳታ ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪካን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርቱ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በድርቅ በተጎዱ፣ ከሠሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት፣ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የእርዳታ ርብርብ እንደሚፈልጉ አስታውቆ፤ አለማቀፉ ማህበረሠብ እጁን እንዲዘረጋ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

No comments:

Post a Comment