መጀመሪያ ራሳችን እንመርምር:: ዘመኑ ስልጡን መሆኑን እናገናዝብ::ከሆያሆየ ወጥተን ሰከን እንበል::ሃገር ማለት ምን ማለት ነው? ጨቋኙስ ማነው የሚለውን እንለይ::በጭፍን ተንደርድረን ጨቋኝ አገዛዞች በሃገር እና በሕዝብ ላይ ተንሰራፍተው የሚሰሩትን ወንጀል ይዘን አንድ ግኡዝ አካል (ሓገር) ማጣጣል እና ማንቋሸሸ ከሞራል አኳያ ባዶነትን ያሳያል::በሃገርችን ለረዥም ዘመናት የነበሩ ጦረኞች በጋራ ተነስተው ጠላትን ሲዋጉ ድል ሲያደርጉ የነበሩት ሃገር ስለተነካ እንጂ የጨቋኞች ወንበር ስለተደፈረ አልነበረም::በቅርብ ጊዜ እንኳን በምስራቁ ጦርነት እና በሰሜኑ የባድመ ጦርነት ቀፎው እንደተነካ ንብ ሆ ብሎ የወጣው እና ያለቀው ወጣት ለእናት ሃገሩ ያለው ፍቅር እንጂ የወንድማማጮቹን የደርግን እና ወያኔን ስልጣን ለመጠበቅ አልነበረም::
በኢትዮጵያ ውስጥ ለሕዝብ የሚበጅ አንድም መሪ እስከዛሬ አልተፈጠረም::የአፄዎቹም ስርዓት ይሁን ደርግወወያኔ በሕዝብ ላይ እንዳሾፉ አልፈዋል;እያሾፉም ይገኛሉ::ኢትዮጵያ ግን እንደ ሃገር ልጆቿን ሰብስባ እስካሁን በመደጋገፍ በስሯ አድርጋ ይዛለች::ሁሉም ስለ ኢትዮጵያ ስለ ሃገር አንድ ሆኖ ቢከፋም ቢለማም እየጮኸ ይገኛል::ኢትዮጵያ ገዳይ አይደለችም ኢትዮጵያ አሳሪ አይደለችም ኢትዮጵያ ገራፊ ዘራፊ አይደለችም ወ.ዘ.ተ. ገራፊው ገዳዩ ዘራፊው አሳዳጁ በየስርዓቱ ራሳቸው እያፈራረቁ ሕዝብ በመንከስ ላይ የሚገኙት የገዢ መደቦች ናቸው::ሃገር እንደ ሃገር ሕዝብ እንደ ሕዝብ በልጥላው ላይ የፈጠረው አሊያም የደረተው አደጋ የለም::የሁሉ ችግሮች መነሻ እና መድረሻ ጬቋኝ እና አምባገነን አረመኔ አገዛዞች እና መሪዎቹ ናቸው::
አሁንም ከቻልን ረጋ እንበል::እውነታውን ትተን ከእውነታው ወጥተን ኢትዮጵያን ብናዋርድ ብናቋሽሽ ምም የሚገኝ ትርፍ የለም::አምባግነን ታግለን ጨቋኝ መደቦችን ደምሥእን በሃገሪቱ ላይ ለሕዝብ የሚበጅ አገዛዝ ብንመሰርት ግን ትልቅ ድል መሆኑ ልንገነዘብ ይገባል::ካልሆነ አያት ቅድመአያት ሞቶ እና ቆስሎ ያቆያትን አገር እንደወንጀለኛ አየሳልን የምንጓዝ ከሆነ መንገዳችን ሁሉ እንደተጣመመ ሰሚ ጆሮ እንደተደፈን እየለፈለፍን እንሄዳለን::የሕዝብን ፍላጎት እና ትኩሳት እንለካ ::በደፈናው በጭፍን ጨቋኞችን መቃወም ሲገባን ሃገርን የምናጣጥል ከሆነ የጨቋኞችን እድሜ ከማስረዘም ውጪ ምንም አናመጣም ይህን እውነት ልንውጥ ግድ ይለናል::ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ባንድ ጎን – ጨቋኝ የገዢ መደቦች በሌላ ጎን – በፍጹም አይገናኙም::ኢትዮጲያዊነት ሲበርድህ የምትደርበው፣ ሲሞቅህ ደሞ የምታወልቀው ጃኬት አይደለም!
No comments:
Post a Comment