Tuesday, June 14, 2016

የአቶ ስብሃት ነጋ የሙስና መረብ

የአቶ ስብሃት ነጋ የሙስና መረብ ሲጋለጥ የህወሐት/ኢህአዴግ አመራር ያለ ሙስና መኖር የማይችል ድርጅት ከሆነ ውሎ አድረዋል፡፡ ሙስና ካለ አድልዎ፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን እንዲጎዳ በማድረግ ህዝቡ እርስ በራሱ ፍቅርና አንድነት እንዳይኖረው በማድረግ ነው ሥልጣኑን ማስቀጠል የሚችለው ህወሐት/ኢህአዴግ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ህወሓት/ኢህአደግ ሙስና የጀመረው የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ አሉ፡፡ ይኸውም አመራሩ ለትግል ሲነሳ ለህዝብ ብሎ እንደተነሳ በሂደት ግን የመንግሥትን ሥልጣን ከያዘ በኋላ ነው የተበላሸው የሚል ነው መነሻቸው፡፡ ይህ አመለካከት ግን ፍፁም የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ሁለት ነገሮች ለያይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ 1. ህዝቡና ከአብራኩ የወጣ ተራው ታጋይ በአንድ በኩል፣ 2. አመራሩ በሌላ በኩል፡፡ የትግራይ ህዝብ የኢኮኖሚ፣ የባህልና የፖለቲካ ጭቆና ሲበረታው ጨቋኞችን ሲታገል ቆይቷል፡፡ የዚህ ህዝብ ረዥም የትግል ውጤት በ1966 ዓ/ም ወደ ላቀ የትግል መድረክ ብቅ ማለት ጀመረ:: የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮዽያ ህዝቦች ጋር በመሆን ትግሉን በተደራጀ መንገድ ለማስቀጠል ታጥቆ ተነሳ፡፡ በዚሁ ወቅት ጥቂት ሙሁራን የህዝቡን ለለውጥ መነሳትን በመገንዘብ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንቅስቃሴውን ለመምራት የተሰባሰቡ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች አሁን የህወሐት/ኢህአዴግ አመራሮች ብለን የምንጠራቸው ማለታችን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ትግሉን ወደ ፈለጉት መንገድ ለመምራት መጀመርያ ማገብት ብለው መሰረቱ:: ቀጥለው በረሃ ከወጡ በኋላ ህወሐት/ኢሀአዴግ ብለው ራሳቸውን ሰየሙ፡፡ ህዝቡ ስለነዚህ ሰዎች ደባ የሚያውቀው አልነበረም፡፡ እንደአማልክት በመመልከት ልጆቹን እያለበሰና እየመረቀ ለትግል፣ ለመስዋእትና መላክ ጀመረ፡ ፡ ተራ ታጋዩም የወላጆቹን ቃል በማክበር እስከ መጨረሻ የደም ጠብታ ተዋግቶ ደርግን ለመደምሰስ በቃ፡፡ በዚያን ጊዜ አመራሩ ህዝቡና ተራው ታጋይ በቀላሉ ሊለየው የሚችል ሴራ መፈፀም አመራሩ አይችልም ነበር፡፡ ይፈጽማቸው የነበሩ ሴራዎች በተራቀቀ ዘዴ፣በድብቅ መኖሩ አሁን አሁን ታጋዮች ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ህዝቡና ታጋዩ ከአመራሩ ጋር መለያየት የጀመረው ከትጥቅ ትግል በኋላ ነው፡፡ ይህ ግን ለህዝቡና ለተራው ታጋይ ነው እንጂ የአመራሩ ቁንጮ ከጥዋቱ የወላጆቻቸውን ሥልጣን በተወሰነ ደረጃ አሻሽለው ለመውረስ የተነሱ ናቸው፡፡ ወደ ዝርዝር ነግር ከመግባታችን በፊት አንዳንድ ለዚሁ አባባል የሚያጠናክሩ የድርጅቱ አሰራሮች ማየት ይቻላል፡፡ በህወሐት ታሪክ አመራሩን ተጠያቂ ማድረግ ፍፁም የማይታሰብ ነበር፡፡አሁንም ነው፡፡ እንደውም አመራሩን በሚመለከት ጥያቄ የሚያነሳ ታጋይ ድርጅቱን ለመበተን የተላከ የደርግ ሰላይ ነው ተብሎ እርስቤት ይገባል፡፡ የድርጅቱ ንብረት፣ገንዘብ የሚታወቀውና የሚንቀሳቀሰው በግለሰቦች ብቻ ነበር፡፡ እንኳንና ተራው ታጋይ ሁሉም የማ/ዊ ኮሚቴው አባላትም የማወቅና የመጠየቅ መብት እንዳልነበራቸው ሁኔታውን የሚያውቁት ታጋዮች ይናገራሉ፡፡ የድርጅቱ ሀብት የግላቸው እንደሆነ አድርገው የሚያንቀሳቅሱት በጣም ጥቂት የድርጅቱ አመራርችና የነሱ ጥቂት ታማኝ ታጋዮች ብቻ እንደነበሩ በሁኔታው መረጃ የነበራቸው ታጋዮች ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የህወሐት ሀብት በአገር ውስጥና (በሜዳ) በውጭ አገር የሚገኝ የሚመራው ስብሀት ነጋ ብቻ ነበር፡፡ ከውጭ ለሚሰበሰብ ገንዘብ ተዋናይ የነበሩ አቶ ሥዩም መስፍን እና አቶ ብርሃነ ገ/ክርስተስ ነበሩ፡፡ ይህም ሆኖ ካዝናው በስብሃት ነጋ እጅ ነበር፡፡ ደርግ ተደምስሶ ህወሐት/ኢህአዴግ ሥልጣን ለመያዙ 1 ዓመት ሲቀረው ማለትም በ1982 ዓ/ም አቶ መለስ ዜናዊም መረጃ ነበረው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቶ መለስ በስብሃት ነጋ እጅ ያለ የድርጅቱ ሃብት ሊያውቅ ችለዋል፡፡ ደርግ ተደምስሶ አዲስ አበባ ከተገባ በኋላ ግን የድርጅቱ ሀብት ጠቅልሎ በስብሃት ነጋ እጅ ወደቀ፡፡ ህወሐት ቢዘያን ጊዜ ነው በበረሃ የነበረ ንብረትና በውጭ ባንኮች የነበረ ገንዘቡ አሰባስቦ አገር ውስጥ ያስገባው፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያካበተው ብዙ ነዳጅና መድኃኒት ራሱ ላቋቋመው መንግሥት ሽጦ ብዙ ሚሊዮን ገንዘብ ሰበሰበ፡፡ብዙ ተሽከርካሪዎች ለአገር ውስጥና ለሱዳን ተሸጡ፡፡ በሳውዲ ዓረቢያ፣ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካና በኢጣልያ የነበሩ ቤቶች በዶላር እና በፓውንድ ተሸጡ፡ ፡ተገዝተው በንግድ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ መርከቦችም ተሽጠው ብዙ ዶላር ተሰበሰበ፡፡ በ1977 ዓ/ም በድርቅ ምክንያት የተሰበሰበ፡ዶላርም በህወሐት ካዝና ነበር፡፡ለዕርዳታ ተብለው ይሰጡ የነበሩ እንደ ፊኖ ዱቄት፣ስኳር፣ዘይት፣ፋፋ፣ሩዝ፣ስንዴ፣ፎሰሊያ፣ዓሣ፣የዱቄት ወተት በሱዳን በኩል ለድርጅቱ ገቢ ሆነዋል ይባል እንጂ ለሱዳን ቱጃሮችና ወታደሮች ተቸብችበዋል፡፡በዚህ ምክንያት የተሸጡ በቢልዮን የሚቆጠሩ፤ ዶላር፣ፓውንድ፣ብር፣ዳችማርክ፣የሳውዲ ራያል፣ተሰብስበው ነበር፡ ፡በተጨማሪም ኢህአዴግ መላው ኢትዮዽያ በተቆጣጠረበት ወቅት በባንኮች የተገኙ ብርና ዶላር ተዘርፈዋል፡፡እጅግ ብዙ ተሽከርካሪዎችም ተቸብችበዋል፡፡ ሌላው የገንዘብ ምንጭ የነበረው ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ከሚገኝ ኢትዮዽያዊ ዜጋ ለድርጅቱ ማጠናከርያ ተብሎ ይሰበሰብ የነበረ ገንዘብና ወርቅ ነበር፡፡ ከዚህ ሌላም ለአካል ጉዳተኞች፣ለድርቅ በማረት በኩል፣ከድርጅቱ ዲሞብላይዝድ ለሆኑ ታጋዮች ማቋቋምያ ተብሎ ብዙ ገንዘብ ይሰበሰብ ነበር፡፡ይህ ሁሉ ሀብት በስብሀት ነጋ ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ይህንን የስብሃት ነጋ ካዝና ኦዲት ሊደረግ አይችልም፡፡በባንክም አይቀመጥም፡፡ልክ በቀድሞ ጊዜ መሳፍንቶች ገንዘባቸው በእንስራ ያስቀምጡት እንደነበር ዓይነት ነው፡፡ይህ ሀብት አቶ ስብሃት ነጋ ለፈለገው ሰው በፈለገው መጠን አውጥቶ ቢሰጥ ጠያቂ የለውም፡፡የግሉ ሀብት ከሚሆን ውሎ አድሮዋል፡፡ የመንግሥት ይሁኑ የድርጅቱ የፋይናንስና መስተዳድር አካላት አያውቁትም፤አይቆጣጠሩትም፡፡ አቶ ስብሃት ነጋ ያ ሁላ ገንዘብና ንብረት ምን ለነማን ሰጠው ? የተዘረፈውን ሀብት አያያዝ በተመለከተ፦ ንብረቱና ገንዘቡ በ55 ሳጥኖች ውስጥ የተቀመጡ ሲሆኑ፦ የአንድ ሣጥን ቁመት 160 ሳንትሜትር፣ጎኑ 120 ሳንትሜትር ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ለትእምት ማቋቋምያ እንደተሰጠ ነው የሚነገረው፡፡ይህ እንደዋና ማጭበርበሪያ ስልት ተጠቅመው ነው ህዝቡን ለማታለል የሚከጅሉት፡፡ በእርግጥ ከዚህ በጣም ብዙ ቢልዮን የሚገመት ንብረትና ገንዘብ የተወሰነ ለትእምት ማቋቋምያ እንደተሰጠ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ በአቶ ስብሃት ነጋ ካዝና የቀረው ይበዛል፡፡ በአቶ ስብሃት ነጋ ካዝና የተደበቀው ብር፣ዶላርና ፓውንድ ከንብረት ደግሞ ወርቅና፣አልማዝ፣ ሰዓቶች ምን አደረገው ነው ጥያቄው? ይህንን የህዝብ ሀብት ከስብሃት ነጋ እጅ እንዳለ እና በመተባበር ደረጃም የሚታወቁ አመራሮች፦ 1. አቶ መለስ ዜናዊ፣ 2. አቶ ተክለወይኒ አሰፋ (የማረት ስራ አስኪያጅ)፣ በሳውዲው ንጉስ የሚመሰል፣ 3. አቶ ብርሃነ ገ\ክርስተስ፣ 4. አቶ ወንድ ወሰን ከበደ (ድሮ በህወሐት አሁን በብኢዴን ያለና ከበአዴን ቢሊዮኖሮች ከሆኑ አንዱ በሚስቱ ስም )፣ ይህ ካዝና በልዩ ሁኔታና በጣም ታማኞችና በቁርጥ ቀን ልጆች የሚጠበቅ ነው፡፡ ካዝናውም በቦሌ ክፍለ ከተማ ይገኝ ነበር፡፡ ታማኞቹ እነማን ናቸው? 1. እንድርያስ፦ ይህ ወጣት የአቶ ስብሃት ነጋ የአክስቱ ልጅ ነው፡፡ ትውልድ ቦታው ዓድዋ፣ 2. ታጋይ ሲሳይ ኃ\ሥላሴ፦ ለብዙ ጊዜ የስብሃት ነጋ ሽፌርና አጃቢ የነበረ፣ 3. ወይዘሮ አበራሽ ነጋ፦ የአቶ ስብሃት ነጋ እህት፣ እነዚህ ሰዎች የአቶ ስብሃት ነጋ ታማኞች ሁነው ለብዙ ጊዜ ከህዝብ የተመዘበረውን ሀብት ጠባቂዎች ናቸው፡ ሁኔታው እንዲህ እንዳለ አቶ ስብሃት ነጋ በወጣት ሲሳይ ኃ\ሥላሴ ላይ መጠራጠር ይጀምራል፡፡ ይህንን ጥርጣሬ ወጣት ሲሳይን በማስወገድ እንደሚፈታ አቶ ስብሃት ነጋ ያምናል፡፡ በመሆኑም አቶ ስብሃት ነጋ አንድ ስልት ዘየደ፡፡እሱም ሲሳይ የኮ\ል መዓርግ ተሰጥቶት የክፍለ ጦር አዛዥ ሆኖ እንደሚመደብ፤ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ቤት እንደሚሰራለትና የመሬት ካርታ እንዲቀበል በማድረግ ጅማ ወደ ነበረች ክፍለጦር በአንድ ኮብራ መኪና እና በሁለት ወጣቶች አንዱ ክላሽ ኮቭ አንዱ ደግሞ ሽጉጥ የታጠቁ እንደወሰዱትና ከዛ በኋላ ሲሳይ የውኃ ሽታ ሆኖ እንደቀረ፡፡ወቅቱ ህወሐት\ኢህአዴግና ኦነግ እየተዋጉ በነበረበት ወቅት ስለነበረ እንደምክንያት በኦነግ ተገደለ ተብሎ እንዲወራ ተደረገ፡፡ አቶ ስብሃት ነጋ በወጣት ሲሳይ ላይ ጥርጣሬ በማሳደር እርምጃ ለመውሰድ ከገፋፉት አንዷ ወይሮ አበራሽ ነጋ ናት፡፡ አቶ ስብሃትን እንዲህ ትለው ነበር “እነዚህ ወጣቶች እንዴት ስታምናቸው ነው ይህን ያህል ምስጢር እንዲጠብቁ ያደረግከው?” ትለው ነበር፡፡አቶ ስብሃትም ከዚህ ተነስቶ ነው በወጣት ሲሳይ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የወሰነው፡፡ ወጣት ሲሳይ ከተወገደ በኋላ ወይዘሮ አበራሽ የሁሉም ሳጥኖች የመቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጣት፡፡ በስብሃት ነጋ ሽፌር እና አጃቢ በነበረ ሲሳይ እና በእንድሪያስ መካከል ጥልቅ የሆነ ፍቅርና መቀራረብ ይስተዋል ነበር፡፡ እንድሪያስ የሁሉም ሣጥኖች ቁልፍ ከእጁ አይለዩም፡፡ አቶ ስብሃት ገንዘብ ማውጣት በፈለገበት ወቅት ወጣት እንድሪያስ በጆንያ ሞልቶ በኮብራ መኪናው ጭኖ ይኸው ይለዋል፡፡ አቶ ስብሃትም ገንዘቡን ይዞ ወደ ፈለገበት ቦታና ለሚፈልጋቸው ሰዎች ይሳጣቸዋል። እንድሪያስ ገንዘቡ ለማን እንደተሰጠ አያውቅም፡፡ ሥራው በጆንያ ሞልቶ ማስረከብና በሣጥን ውስጥ ያለው ሀብት መጠበቅ ብቻ ነው ፡፡ እንድሪያስ ሰዓቶች እና ወርቅም በጥቂት በጥቂት እየቀነሰ ለአቶ ስብሃት ያስረክባል፡፡ አቶ ስብሃት ወስዶ ለማን እንደሚሸጠው ለጊዜው ከእግዚአብሔር ውጭ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ ይህ እንዲህ እያለ እንድሪያስ አንድ ወቅት ለሥራ ምክንያት በሚል ዓድዋ ይላካል፡፡ ከዓድዋ እንደተመለሰ በቦሌ ክ\ከተማ በሚገኝ 5 ክፍል ያለበት አፓርታማ ውስጥ የነበሩ ሳጥኖችና ካርቶኖች የሚበዙ ተነስተው ያገኛቸዋል፡፡ የወይዘሮ አበራሽ ፊት ሲመለከትም ከወትሮው የተቀየረ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ የአቶ ስብሃት አቀራረብም እንዲሁ ለየት አለበት፡፡ እንድሪያስ የወጣት ሲሳይ መሰወር ስጋት ነበረው፡፡ የሲሳይ መጥፋት ለበጎ አለመሆኑን እየተረዳ ከመጣ ቆይቷል፡፡ አንድ ቀን ስብሃት፣የስብሃት ሽፌርና አጃቢው እንድሪያስ ወደ አበራሽ ቤት ጎራ ብለው ሲጫወቱ፡ ፡ አበራሽ ለእንድርያስ ያሰበችለት መስላ ስብሃትን መውቀስ ጀመረች፡፡ እንዲህም አለች “እኔ የሚገርመኝ ስብሃት ጭቁኖችን ነፃ ለማውጣት ነው የታገልኩና እየታገልኩት ያለሁት ትላለህ!” አለችው፡፡ አቶ ስብሃት ሐሳቡን እንድታብራራለት ፈልጎ “ታድያ ምን ጎደለ?” አላት፡፡ ወይዘሮ አበራሽ በመቀጠል “እኔ አይመስለኝም እንዳውም ጨቋኝ ነህ ለዚህ ማሳያ ብዬ የማቀርበው እንድርያስን ነው፤ እሱ ከ25 ዓመታት በላይ ካንተ ጋር ላይና ታች ብሎ በታማኝነት የተሰጠውን ኃላፊነት የተወጣና እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን አንተ ግን አንድ ነገር እንኳ ለሞራል ብለህ የሠራህለት ነገር የለም” ትለዋለች፡፡ አቶ ስብሃት “ተግሳጹ ጥሩ ነው እቀበለዋሎህ ታድያ ምን ብናደርግለት ነው የሚሻለው?” ወይዘሮ አበራሽ “እኔ መሆን ያለበት የምለው፤ ለመኖሪያ የሚያገለግለው ቤት ስራለት፣ ለሥራ የሚያገለግለው ደግሞ መኪና ገዝተህ ስጠው። ራሱ በራሱ ያስተዳድር” አለችው፡ ፡ እንድሪያስ የወይዘሮ አበራሽ ሐሳብ ሰምቶ በጣም ከመደሰቱም በላይ ንግግርዋን በጥሞናና በፈካ ፊት ይከታተለው ነበር፡፡ እንድሪያስ ድራማው ያ ሁላ ሀብት አበራሽ እሷና ወንድሟ አቶ ስብሃት ለመጠቅለል ብላ የዘየደችው ዘዴ መሆኑን አልተረዳም፡፡ እንደተባለው እንድሪያስ ወድያው 25 ሰው የመጫን ዓቅም ያላት ኮስተር መኪና አቶ ስብሃት እንዲገዛለት በማድረግ ሰጠው፤ለቤት መስሪይም 200,000.00 ብር ተሰጠው፡፡ በዚህ ከሣጥኖች ጥበቃ ተባረረ፡፡ ወይዘሮ አበራሽ ለሁሉም ሳጥኖች የመቆጣጠር ብቃት ተጎናጸፈች፡፡ እንድሪያስ ከቦታው እንደተነሳ በቦሌ ክ\ከተማ 5 ክፍል የነበረበት አፓርትመንት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ሀብት ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ እንዲቀየር ተደረገ፡፡ አፓርትሜንቱ ወይዘሮ አበራሽ ነጋ ከቤተሰቦችዋ ለመኖርያዋ አደረገችው፡፡ አንድ ጊዜ እንድርያስን ለምሳ ተጋብዞ አበራሽ ቤት ሲሄድ ሁኔታው ተቀያይሮ፤ እዛ ተከዝነው የነበሩ የገንዘብና የወርቅ ሀብት የሉም፡፡ እንድሪያስ ሁኔታውን በአግራሞት ከመመልከት ሌላ አማራጭ አልነበረውም፡፡ አይቶ እንዳላየ ዝም አለ፡፡ ይህ ሁኔታ አቶ መለስም ሰምቶት አቶ ስብሃትን አነጋግሮ አልሆነለትም፡፡ ለሁለቱም አደጋ በመሆኑ አቶ መለስ ሊገፋበት አልቻለም፡፡አቶ መለስ ይህንን ካነሳ አቶ ስብሃት የጎላጉል ህንፃ ጉዳይ ስለሚያነሳበት ፡፡ ታድያ ገንዘቡ የት ገባ? እስከ አሁን በአገር ውስጥ በአቶ ስብሃት ነጋ የሚታወቅ የንግድ ተቋም ይሁን በባንክ ገንዘብ የለም፡ ፡ አቶ ስብሃት ገንዘቡና ንብረቱ የሚያንቀሳቅሰው ወደ ቤተሰቡና የሱን ታማኞች በመስጠት ነው፡፡ ከነዚህ የተደበቁ በብሊዮን የሚገመቱ ንብረት እና ጥሬ ገንዘብ የተወሰኑ እነ ማን እጅ እንዳሉ እናቀርባለን፡፡ 1. አድማስ ዩኒቨርስቲ ኮለጅ፦ አድማስ ዩኒቨርስቲ ኮለጅ በዚህ በተመዘበረ ገንዘብ ከተቋቋሙት ተቋማት አንዱ ነው፡፡ የተቋሙ ባለቤት አቶ ይብራህ ይባላሉ፡፡ የአቶ ስብሃት የአክስት ልጅ ነው። አቶ ይብራህ ማለት፡ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ አቶ ይብራህ በኢትዮዽያ ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመዝገብ ቤት ክለርክ ሆኖ ሲሰራ የወር ደመወዙ 450 ነበር፡፡ ይህ ሰው ያለ አንድ መነሻ ካፒታል በአዲስ አበባ በሁለት ቦታዎች አድማስ በሚል ስም ኮለጅ ከፈተ፡፡ቀጥሎም ኮለጁ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ አድጎ አሁን በኢትየዽያ 16 ካምፓሶች እንዳሉት ይታወቃል። በመቀለም አዲስ ካምፓስ እያሰራ ይገኛል፡፡ከዚህም አልፎ በሶማሊላንድ አንድ ካምፓስ ከፈተ፡፡በሃርጌሳም እንዲሁ፡፡ የዚህ መነሻ ካፒታል ከአቶ ስብሃት ነጋ የምዝበራ ገንዘብ የተገኘ መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ 2. አቶ ገ\እግዚአብሔር አምባዬ፡ በትግራይ ክልል የእንትጮ ከተማ ተወላጅ ነው፡፡ ይህ ሰው በአምቼ ለወር 25,000.00 ብር እየተከፈለው ይሰራ ነበር፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ በአንድ ዓመት ብቻ ከ200 የደረቅና የፈሳሽ ኤሮትራክ የኢጣልያ መኪኖች ገዛ፤ብዙ ህንጻዎች ገንብተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አቶ ገ\እግዚአብሔር አምባዬ በአምበሳ ባንክ 70 ሚልዮን አክስዮን አለው፡፡የዚህ ሰውዬ የሀብቱ ምንጭም ያለ ጥርጥር የአቶ ስብሃት ነጋ የዘረፋ ገንዘብ ነው፡፡ አቶ ገ\እግዚአብሔር አምባዬ በሙስና ከበለፀጉ ዜጎች አንዱ መሆናቸው ተነቅቶበት ሊታሰር ሲፈለግ፤አቶ ስብሃት ነጋና አቶ አርከበ ዑቁባይ እንዲሸሽ ሁኔታዎችን አመቻችተው ጀርመን ገባ፡፡ አሁን ከጀርመን ወደ አሜሪካ በመሄድ እዛው እየኖረ ይገኛል:: በባንክ ያለው ገንዘቡና መኪኖቹ ያለ አንዳች ችግር በመንቀሳቀስ ትርፍ እየሰበሰቡለት ይገኛሉ፡፡ 3. ዶክተር ነጋ ፦ይህ ሰው ትክክለኛ ዶክተር አይደለም ያለው፡፡ የውሸት ዶክተር ነው፡፡ ይህ ሰው ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ በድለላ ሥራ ተሰማርቶ ነበር፡፡ ድለላውም የወንጀል ሥራ ነበር፡ ፡ ይህ ሰው የስብሃት የቅርብ ዘመድ ነው፡፡ በመሆኑም የስብሃት የስርቆት አማካሪ ሆኖ አገልግለዋል፡፡ስብሃት ነጋ ካከማቸው ወርቅና አልማዝ ከመርካቶና ፕያሳ ነጋዴዎች እየተገናኘ ተሽጠው በቢልዮን የሚገመት ገንዘብ እንዲሰበሰብ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ይህ ካደረገ በኋላ አቶ ስብሃት ነጋ ከመዘበረው ገንዘብ ወድያው 50 ኤሮትራክ መኪና በስሙ ገዛ፣ በልጆቹ ደግሞ 250 ኤሮትራክ መኪኖች ገዛ፤ እያንዳንዳቸው 400 ኩንታል የመጫን አቅም ያላቸው ናቸው፡፡በአንበሳ ባንክ 70 ሚሊዮን አክስዮን አለዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በከዛንችስ እና በሌሎች የአዲስ አበባ ክ\ከተሞች ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች አሉት፡፡ ዶክተር ነጋ በደርግ ጊዜም ይሁን በኢህአዴግ ምንም ዓይነት የንግድ ሥራ ያልነበረው ሰው ነበር፡፡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ሊደርስ የቻለው በስብሃት ነጋ ከተመዘበሩ የህዝብ ሀብት አማክኝነት ነው፡፡ 4. ኮ/ል በላይ ነጋ፦ የአቶ ስብሃት ነጋ ወንድም ናቸው፡፡ እኝህ ሰውዬ በደርግ በደረሰባቸው መግረፍት ምክንያት አሜሪካ ሄደው በሕክምና ላይ ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ደርግን አሸንፎ አዲስ አበባ ሲገባ እሳቸውም ኢትዮዽያ ገቡ፡፡ በዚሁ ጊዜ ሥራ አልነበራቸውም፡፡ወድያው ከአሜሪካ እንደመጡ ያለ ምንም ውድድር የትእምት አማካሪ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ በመቀጠልም ከወንድማቸው ባገኙት የህዝብ ገንዘብ በአዲስ አበባ፣መቀለና ዓድዋ ፈቆች በማሰራት የዘመናዊ ፎቅ ባለቤት ለመሆን በቁ፡ ፡በጋምቤላም ሰፊ የእርሻ ቦታ በስመ ኢንቨስትመንት ዘርፈው በትራክተሮች በማሳረስ በስርቆት ላይ ስርቆት በመጨመር ቢሊዮነር ሆነኖዋል፡፡በቃሊቲም ትልቅ ኩባንያ አላቸው፡፡ እሳቸው አሁን በህይወት የሉም፡፡ የሳቸው ሀብት ወራሽ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ ናት፡፡ 5. ወይዘሮ አበራሽ ፦ ላደረገችው ውለታ በአዲስ አበባ ሦስት የመኖሪያ ቤቶች አሰርታ እያከራየች ብዙ ገንዘብ በመሰብሰብ ተጠምዳ ትገኛለች፡፡ አቶ ስብሃት ነጋና ሌሎች አመራሮች የታገሉት ቤተሰቡን ለመጥቀም ኖረዋል? ከህዝብና ከአገር ወዳጅ ባለ ሀብቶች ለድርቅ፣ትግሉን ለማጠናከርና ለአካል ጉዳተኞች ወዘተ… ተብሎ የተሰበሰበ ሀብት ለአቶ ስብሃት ነጋና ቤተሰቡ ጥቅም ሲሰራጭ፤ትግሉ ገና ከጅምሩ ለህዝብ ብለው እንዳልተነሱ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ አመራሩ ለሥልጣን ብሎ ከጅምሩ ራሱን ከመስዋእት እያራቀ፤ሌሎች የድሆች ልጆች በተሰውለት እሱና ቤተሰቡ ካለፉት መሳፍንት ወላጆቹ የተሻለ ኑሮ ለመኖር የመንግሥትን ስልጣን ተቆጣጥሮ እንደሆነ በማሰብ ይንቀሳቀስ እንደነበር ያመለክታል፡፡

No comments:

Post a Comment