Thursday, June 9, 2016

አገዛዙ አለኝ የሚለውን ህገ መንግስት በተግባር ቀዶ ጥሎታል!!! – ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ


አገዛዙ አለኝ የሚለውን ህገ መንግስት በተግባር ቀዶ ጥሎታል!!! – ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ 
አገዛዙ ራሱ ያፀደቀው ህገ መንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በህግ በተደነገገው ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ህይወቱን አያጣም በማለት ቢደነግግም ለአንድ ቀንም እንኳ ህግን አክብሮ የማያወቀው ህወሃት/ኢህአዴግ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዜጎችን በጠራራ ፀሀይ መግደሉን ዋና ስራው አድርጎታል፡፡ በተመሳሳይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 21 በጥበቃ ላይ ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰባዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት እንዳላቸውና ከትዳር ጓደኞቻቸውና ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው ከሃኪሞቻቸውና ከህግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት እንዳላቸው ቢገልፅም አገዛዙ በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን የመፃፍ፣ የመናገርና የመደራጀት መብታቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው ብቻ በየእስር ቤቱ ያጎራቸው ዜጎች በአስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ያለምንም ክስ ከአምስት ወራት በላይ ማዕከላዊ በሚባለው የዜጎች ማሰቃያ ጣቢያ ቆይቷል፡፡
እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ የሰሜን ጎንደር አስተባባሪ አቶ አግባው ሰጠኝ እና ከእሱ ጋር በአንድ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች በማንነታቸው ብቻ በደል እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት ቢናገሩም አገዛዙ ከማስተካከል ይልቅ ለምን ተናገራችሁ በማለት በጨለማ ክፍል ወስጥ አሰሯቸው ይገኛል፡፡ አመፅ አነሳስታችኋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ምክትል ሊቀመንበሩን አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮችና አባላት በቀጠሯቸው እንዳይቀርቡ ከመደረጉም በላይ የእስረኞችን ስነ ልቦና በሚጎዳ ሁኔታ ልብሶቻቸውን ተቀምተው በባዶ እግራቸውና በወስጥ ልብሶቻቸው ፍርድ ቤት ለመቅረብ ተገደዋል፡፡
በቂሊንጦ ማጎሪያ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች አግባው ሰጠኝ ፣ዮናታን ተስፋዬ፤ ፍቅረማሪያም አስማማውና ብርሃኑ ተክለያሬድ በአሁኑ ሰዓት በጨለማ ክፍል ውስጥ ታስረው የሚገኙ ሲሆን በቅርብ ዘመዶቻቸውና በጠበቆቻቸው እንዳይጎበኙ ተደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ አገዛዙ የራሱን ዜጎች በመግደልና በማሰር በስልጣን ለመቆየት መወሰኑን ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የፈፀመው ወንጀል ያረጋግጣል፡፡ ስለሆነም ከዚህ አስከፊ አገዛዝ ተላቀን ህዝባዊ አስተዳደር መገንባት የምንችለው ሁላችንም ለመታሰርና ለመሞት ቆርጠን ስንነሳ ብቻ መሆኑን ተገንዝበን ትግላችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም
Minilik Salsawi's photo.

No comments:

Post a Comment