Wednesday, June 8, 2016

ዶክተር መረራ ጉዲናን እናሸልም


ዶክተር መረራ ጉዲናን እናሸልም!
ዶክተር መረራ ጉዲና በ1947 ቶኬ በሚባል ከአምቦ ከተማ 35 ኪሎ ሜትሮች የሚርቅ መንደር ውስጥ የተወለዱ ሲሆን፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዛው በተወለዱበት መንደር፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ አስከትለውም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ቢጀምሩም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው ለሰባት ዓመታት ታስረው ከቆዩ በኋላ ከእስር መልስ ያቋረጡትን ትምህርት በመቀጠል በ1978 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና ዓለማቀፍ ግንኙነት የትምህርት መስክ አግኝተዋል፡፡ በማስከተልም ግብፅ አገር በሚገኘው አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካይሮ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ማስተርሳቸውን)፤ እንዲሁም የሶስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲያቸውን) በኔዘርላንድስ ከሚገኝው ‘Institute of Social Studies’ የትምህርት ተቋም አግኝተዋል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሲሰሩ በመመመረቂያ ጽሑፍነት የጻፉት ‘Ethiopia: Competing Ethnic Nationalism and the Quest for Democracy: 1960-2000’ በተለያዩ ምሁራን በምርጥ ፅሁፍነት ምንግዜም ይጠቀሳል፡፡
ከሰባት ዓመታት እስር በኋላ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት በማግኝታቸው ተመርጠው 1979 ጀምሮ ዶክተር መረራ ጉዲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካል ሳይንስ የትምህርት ክፍል መምህርት ሆነው ሲያገለግሉ፣ ካሳተሟቸው አራት መፅሃፍት ማለትም፡-
1.Ethiopia: Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy: 1960-2000
2.Ethiopia: from Autocracy to Revolutionary Democracy: 1960’s – 2011
3.የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች እና
4.የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ሕልሞች፡ የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ
በተጨማሪ በተለያዩ ዓለምአቀፍ ‹ኮንፈረንሶች› ላይ በመገኘት የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችንና ልምዳቸውን ለዓለም ህዝብ አካፍለዋል፡፡ ከሰላሳ በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችንም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ዦርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ ካሳተሟቸው ጽሁፎች ከፊሉን => www.aau.edu.et/css/merera-gudina በመመልከት ማየት ይችላሉ፡፡
መምህሩ መረራ!
ተማሪዎቻቸው እንደሚናገሩት መምህር በነበሩበት ወቅት ቢሯቸው ለሁሉም ተማሪ ክፍትና ማንኛውም ተማሪ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስቶ ምክር መጠየቅ የሚያስችለው ቤተሰባዊ መንፈስ ነበራቸው ይላሉ፡፡ አንዳንድ ተማሪዎቻቸው እንደሚሉት “ከሌሎች መምህራን በተለየ እሳቸው የቢሯቸውን በር ከፍተው በመቀመጥ ይታወቃሉ” ብለው ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ ችሎታቸውንም ሲናገሩ፣ “ሲያስተምሩ፣ የጥናት ፅሁፎችን ሲያማክሩ፣ ሙያዊ አስተያየቶችን ሲሰጡና በተለያዩ መድረኮች ንግግር ሲያደርጉ አፍ የሚያስከፍቱ ምሁር ናቸው” ይሏቸዋል፡፡ እሳቸውም “በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምን ያህል ጊዜ አስተምረዋል?” ተብሎ ለሚሰነዘርላቸው ጥያቄ በኩራት “እሱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፣ ለ28 ዓመት ፖለቲካል ሳይንስ አስተምሬያለው” ብለው ይመልሳሉ፡፡ በሶስት የተለያዩ ጊዜያትም የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ሆነው መስራታቸው ሳይዘነጋ፡፡ በአንድ ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በመምህርነት ህይወታቸው ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለሀገር አበርክቻለው ስለሚሉት ትልቅ ነገር ሲናገሩ፣
«ሰው ስለራሱ ባይናገር ይመረጣል፡፡ የሆኖ ሆኖ ሁለት መፅሐፍት አሳትሜአለሁ፡፡ በተደጋጋሚ በሀገር ውስጥና በውጭ አገር ሌክቸሮችና አለማቀፍ ስብሰባዎች ላይ ተካፍዬ ሃሳቤን ገልጫለሁ፡፡ ፖለቲካንና ሃገሪቷን በሚመለከት ጉዳዮች በዓለም ታላላቅ በሆኑት እነ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ሲኤን ኤን፣ ቪኦኤ እና በመሳሰሉት ላይ አስተያየቶችና ቃለምልልሶችን በስፋት ስሰጥ ነበር፡፡ በአሜሪካና አውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎችም ሌክቸር የማድረጉ አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ አካዳሚውንም ፖለቲካውንም በሚዛናዊነት ለማስኬድ ሞክሬአለው፡፡» ብለው ነበር፡፡
ስለምን ስለ ዶክተር መረራ ጉዲና ማንሳት አስፈለገን?
ለአገርና ለሕዝብ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባር ያከናወኑ ሰዎችን በየዓመቱ ዕውቅና የሚሰጠው ‹የበጎ ሰው ሽልማት› አራተኛው መርሐ ግብር ግንቦት 24 ቀን 2008 በይፋ መጀመርን ተከትሎ የሽልማት መርሃ ግብሩ ከዘረዘራቸው ዘርፎች መካከል መምህርነት በአንደኝነት ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን፣ መስፈርቶቹም:
-ለአገራችን ኢትዮጵያ መልካም የሚሰሩ፣
-ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በብቃትና በልዕልና የሚወጡ፣
-የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጭ ተግባር የፈጸሙና የሚፈጽሙ፣
-በብዙ ሰዎች የማይደፈርን ተግባር በተነሳሽነት የከወኑ፣
-ለድጋፍ ፈላጊ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ትኩረት በመስጠት ሃገራዊ ኃላፊነት ወስደው የሠሩ[…]ኢትዮጵያውያን መሆን ይኖርባቸዋል ይላል፡፡
በመሆኑም ከላይ እንደጠቀስነው ዶ/ር መረራ ጉዲና የላቀ ሁለገብ የሆነ ችሎታና እውቀት ያላቸው ሰው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እንደ መምህር ሰላሳ ለሚጠጉ ዓመታት ያስተማሩ፣ እንደ ምሁር እጅግ ብዙ ጽሁፎችን የጻፉ፣ እንደ ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን ካሉበት አሳዛኝ ሁኔታ መውጣት ይኖርባቸዋል በማለት ሕይወታቸውን በሙሉ ለሕዝብ የለገሱ ሰው ናቸው መረራ፡፡ በመሆኑም ‹የበጎ ሰው ሽልማት› አራተኛው መርሐ ግብር ተገቢውን መስፈርት በማሟላት ዶ/ር መረራ እጩ መሆን የሚችሉ አገር ወዳድ፣ ቀናኢ፣ ብሎም ለፃነትና ለዲሞክራሲ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ብቁ ዜጋ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ይህ የፌስቡክ ገፅም ስለሳቸው የሚወራበት፣ ድምፅ የሚሰበሰብበት፣ ተማሪዎቻቸው ስለ እርሳቸው የሚጽፉበትና ምስክርነት የሚሰጡበት እንዲሆን በማሳብ የተከፈተ ገፅ ሲሆን፣ ለዚህ መልካም ዓላማ የእርስዎ ድምፅ ዋጋ አለውና፤ የእጩ በጎ ሰዎች ጥቆማ ከግንቦት 24 ጠዋት 12፡00 ሰዓት እስከ ሰኔ 24 ማታ 12፡00 ድረስ የሚከናወን በመሆኑ ዶ/ር መረራ ጉዲናን፡
በስልክ፡ 0915445555
በቫይበር፡ 0915445555
በግንባር በመቅረብ፡ ለም ሆቴል ማትያስ ሕንጻ ቢሮ ቁ. 408
በፖስታ፡ 150035
በብሎግ፡ www.daneilkibret.com
በኢሜይል፡ begosew2008@gmail.com
ለሽልማቱ በመጠቆም እኒህን ታላቅ ሰው ተሸላሚ እናድርግ፡፡

No comments:

Post a Comment