Monday, June 20, 2016

የዐማራ ሕዝብ ትግል በሕይወት ለመኖር የሚደረግ ግብግብ ነው!

ዐማራ ሕዝብ ትግል በሕይወት ለመኖር የሚደረግ ግብግብ ነው! Muluken Tesfaw
የዐማራው ሕዝብ የተጋረጠበት አደጋ የሚቆጫቸውና ተቆርቋሪነት ያላቸው ነበልባል ወጣቶች በቁጥርም በጥራትም ከትናት ይልቅ ዛሬ ብዙ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች መገንዘብ የሚኖርባቸው ጥቂት ነጥቦች አሉ፤ የዐማራ ወጣቶች አያውቁትም የሚል እምነት ባይኖረኝም ቅሉ ሐሳቤን ግን ማጋራት እሻለሁ፡፡
እንደሚታወቀው አገራችን ዐማራውን ጠላት አድርገው የተነሱ ኃይሎች የዐማራውን ለማጥፋት አገሪቱንም እያጠፏት ነው፤ ዕውነት ለመናገር ኢትዮጵያ በካርታ ላይ እንጅ በተጨባጭ የትግራይ ብሔርተኞች የሕዝባችን አንድነትና አብሮነት ንደውታል፡፡ በዚህ ዙሪያ ወደ ፊት በካርታ አብረን ሆነን የተለያየ አገር ዜጎች እንዴት እንደሆንን በተጨባጭ ከማስረጃዎች ጋር እመለስበታለሁ፡፡
የዐማራ ወጣቶች መገንዘብ ያለብን ነገር ትግላችን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ በሰለጠነው ዓለም ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚቃወሙና የሚደግፉ ሰዎችን ሰምታችሁ ታውቁ ይሆናል፡፡ ‹‹በቂ ለመኪናዎቻችን የሚሆን ዘይት የለንም፤ ዋጋውም ንሯል›› ብለው የሚቃወሙ ሰዎችን ሰምታችሁ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ‹‹የውሻ ባለቤቶች ውሻዎቻቸውን በሚገባ አልያዟቸውም›› የሚል ተቃውሞ በምዕራባውያን አገር ለምትኖሩ ሰዎች እንግዳ አይሆንም፡፡
አንድ ወዳጄ ያየውን ነገር ሲነግረኝ በጣም ተገረምኩ፡፡ በስዊድን ስቶክሆልም የመኪና መንገድ ላይ አንዲት ድመት ወድቃ ትገኛለች፡፡ መኪና ቆሞ መንገዶች ሁሉ ተዘጋግተው ከሉንድ ዩንቨርሲቲ የታወቁ ሐኪሞች መጥተው በድመቷ ላይ የደረሰውን አደጋ ለማጣራት ርብርብ አደረጉ፡፡ የከተማው አስተዳደርም ችግሩን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ቃል መግባቱን በአገሪቱ የሚታተሙ ጋዜጦች ሁሉ አትተውት ነበር አሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት አንድ ዐማራ በማንም ጠባብ ቡድን ቢገደል የዚችን ድመት ያክል ክብር የሚሰጠው አካል የለም፡፡ አንድ ዐማራ ሳይሆን በሺህዎች ሲያልቁ ገዳዮች ሹመት ሽልማት ይሰጣሉ እንጅ እንዴት እንደሞቱ ማንም አይጠይቅም፡፡ ዐማራ መሆን በራሱ በዘር የሚተላለፍ ወንጀል እንደሆነ ማንም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡
ስለዚህ ዐማሮች ለመኪናዎቻቸው የሚሆን ዘይት ይሰጠን ብለው አይጮኹም፤ ምክንያቱም መኪና ያለው በትግራይ ጠባብ ብሔርተኞች እጅ ብቻ ነውና፡፡ የዐማራ ሕዝብ ትግል በሕይወት የመኖር እና ያለመኖር ግብግብ ነው፡፡ በአንድነት ስም ዐይናቸውን የሸፈኑ ‹‹ተርመጥማጮች›› ከዚህ በኋላ ዐማራውን ከጥፋት ለመታደግ ባያግዙ እንኳ አፋቸውን መለጎም አለባቸው፡፡
ሌሎች ነጥቦችን በቀጣይ እመለስባቸዋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment