የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ከሱዳን ጋር በሚዋሰንበት ድንበር ላይ እየታፈኑ የሚወሰዱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታፍነው የተወሰዱ ዜጎች ለማስመለስ፣ ከዚህ በኋላም ይህ ድርጊት እንዳይደገም ከደቡብ ሱዳን ሲናር ግዛት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገለጸ፡፡
ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አህመድ ናስርን ባለፈው ሳምንት ሰኔ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ተክተው የተሾሙት አቶ አሻድሊ ሀሰን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፌዴራል መንግሥት ከሱዳን መንግሥት ጋር ከሚያካሂደው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተጨማሪም፣ የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት ከሱዳን ሲናር ግዛት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ለሪፖርተር ጨምረው እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ሚያዝያ 2008 ዓ.ም. የተወሰዱት 24 ዜጎች በዚህ ሳምንት ወደ አገራቸው ይመለሳሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት የተወሰዱ ዘጠኝ ዜጎችን በቀጣይነት ለማስመለስ ንግግር እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ካሉት ሦስት ዞኖች (አሶሳ ካማሽንና መተከል) መካከል ትልቁ መተከል ዞን ነው፡፡ መተከል ዞን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚካሄድበት ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ዞኑ ለእርሻ ሥራም አመቺ በመሆኑ የበርካታ ኢንቨስተሮችን ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ የመተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ፣ አሜድላ ቀበሌ ከሱዳን ሲናር ግዛት ጋር ይዋሰናል፡፡ በተለይ የደቡብ ሱዳን ሲናር ግዛት ውስጥ የሚገኘው ዲንደር ፓርክ ከቤንሻንጉልና ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰነው ቦታ ላይ የሚገኘው ለም መሬት ለዚህ ችግር መንስዔ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
አቶ አሻድሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ አካባቢ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበት ቦታ በግልጽ ባለመከለሉ ለችግር ምክንያት እየሆነ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ወገን በዚህ አካባቢ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ የሲናር ግዛትም ይኼ አካባቢ የኛ ነው የሚል አቋም የሚንፀባረቅ በመሆኑ፣ በአካባቢው በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ላይ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን አቶ አሻድሊ ይናገራሉ፡፡
‹‹ነገር ግን ሁለቱን አገሮችም ሆነ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልንና ሲናር ግዛትን የማያግባቡ ጉዳዮች የሉም፡፡ ይኼ ችግር እንዲፈጠር በአመራር ደረጃ የተሰጠ መመርያ የለም፡፡ ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ ችግሩ እየተከሰተ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፤›› በማለት አቶ አሻድሊ ገልጸዋል፡፡
ይኼንን ችግር ለመፍታት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከሲናር ግዛት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑንና፣ ከዚህ ቀደም በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ 24 ዜጎች ለመመለስ መግባባት ላይ መደረሱንም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ታፍነው የተወሰዱ ዘጠኝ ዜጎችንና ንብረቶቻቸውን ለማስመለስ ከወዲሁ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ አሻድሊ አስረድተዋል፡፡
የቤንሻንጉል ጉሙዝና የአማራ ክልል ከሱዳን ጋር ሰፊ መሬት የሚዋሰን ሲሆን፣ በድንበር አካባቢ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ እንደቆዩ ይታወቃል፡፡
No comments:
Post a Comment