Monday, June 13, 2016

በኑሮ ጫና የጎበጠን ህዝብ ዳግም ሊሸከመው የማይችለውን የዋጋ ሸክም መጫን አይጥ በበደለ ዳዋውን ማቃጠል ይሆናል፡፡

በአይጥ በደል ዳዋው አይቃጠል !
(አርኪቴክት – ዮሐንስ መኮንን)
ከዚህ ቀደም በ40/60 ጉዳይ ላይ ግላዊ ትዝብቴን አካፍዬ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሰሞኑን የታተመው ካፒታል ጋዜጣ ስጋቴን ወደ አደባባይ አምጥቶታል፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት፣ ንግድ ባንክ እና የሥራና ከተማ ልማት መሥሪያ ቤቶች በጋራ ባደረጉት ‹‹ጥናት›› በመገንባት ላይ ያሉት 40/60 ቤቶች ቀድሞ ከኅብረተሰቡ ጋር ውል ከተገባባቸው የካሬ ሜትር ዋጋ ላይ 2,100 (ሁለት ሺህ አንድ መቶ) ብር መጨመር እንዳለበት ደርሰንበታል እያሉ ነው፡፡ ይኸውም የካሬ ሜትሩን ዋጋ በአማካይ 3,150 ብር የነበረውን ወደ 5,250 ብር አካባቢ ያሳድገዋል፡፡ በግርድፉ ካየነው ጭማሪው ከ66% በላይ ይሆናል፡፡
በማንኛውም ግንባታ ወቅት የዋጋ መዋዠቅ የሚጠበቅ ሲሆን እስካሁን የተለመደው የዋጋ ለውጥ 10% የማይበልጥ ሲሆን መሥሪያ ቤቶቹ ‹‹በጥናት አገኘነው›› ያሉት የ66 በመቶ ጭማሪ ግን ያልተለመደ እና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥ የዋጋ ጭማሪው በከንቲባው ጽ/ቤት ከጸደቀ በኋላ በይፋ የሚገለጽ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ !
የግንባታ ቁሳቁስ፣ የሠራተኛ፣ የመሬት፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የሕንጻ ዲዛይን ዋጋ መናር የጭማሪው ምክንያት ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡
በግንባታ ላይ ካሉት ከ38,000 በላይ ቤቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተገነቡ ያሉት 3% ብቻ መሆናቸው የዋጋ ጭማሪውን ምክንያታዊነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፡፡ ምክንያቱም ለዋጋ ጭማሪው ቀዳሚ ምክንያት የሚሆነው የግንባታዎቹ መዘግየት በዋንኛነት የሥራ ተቋራጮችን መዝረክረክ፣ የአማከሪዎችን የዓቅም ውሱንነት እና የመንግስትን የማስፈጸም ብቃት ማነስ የመጣ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ የመጣውን የዋጋ ንረት ህዝቡን ለማሸከም የቀረበው ሃሳብ በድጋሚ በከፍተኛ ጥንቃቄ መጤን ይገባዋል እላለሁ፡፡ በኑሮ ጫና የጎበጠን ህዝብ ዳግም ሊሸከመው የማይችለውን የዋጋ ሸክም መጫን አይጥ በበደለ ዳዋውን ማቃጠል ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment