Monday, June 20, 2016

“ቤተሰቤንና ጠበቃየን እንዳይ ካልተደረገ በርሃብ አድማየ እቀጥላለሁ ቀጣይ ቀጠሮ ሬሳየ ሊመጣ ይችላል” – አግባው ሰጠኝ


ምግብ ከቀመሰ ሰባት ቀናት አለፉ። ጉዳቱ በአካሉ ላይ በግልጽ ይታያል፤ ከስቱዋል፤ ጥቁር ብሎዋል። ሲራመድ ጎንበስ ብሎ ነው። ያልበላው አንጀቱ ታጥፎ መሰለኝ። ይህ ሰው አግባው ሰጠኝ ነው፣ ከግንቦት 17/2008 ዓ.ም ጀምሮ ቂሊንጦ ጨለማ ቤት የታሰረው አግባው።
ይህ ሰው “ሰው ራበኝ! የህግ ባለሙያ ይየኝ!” ሲል ቆይቱዋል። ሆኖም ዛሬ ፍርድ ቤት እስኪመጣ ሰው ናፍቆት ቆየ። ዛሬ በተዳከመ መንፈስ ፈገግታውን አስቀድሞ ፍርድ ቤት ለተገኙ ሰዎች ሰላምታ አቅርቦዋል።
አግባው ሰጠኝ በእነ ጌታቸው መኮንን መዝገብ የሽብር ተከሳሽ ነው። ዛሬ ለፍርድ ቤት ሲናገር እንደተደመጠው ተከሳሹ በማንነቱ (አማራ በመሆኔ ነው ይላል) በደል እየተፈጸመበት ነው። የእስር ቤቱ ተወካይ “የፖለቲካ እስረኛ ነኝ በማለቱ ቅጣት” እንደተላለፈበት ቢናገርም፣ አግባው ግን “ዘረኛ ብለኸናል ብላችሁ ነው የምታንገላቱኝ፤ ይህ ግን ሀቅ ነው” ሲል ችሎት ፊት ተናግሮዋል።
አግባው ሰውነቱ ተዳክሞዋል። ችሎቱን ሲከታተልም ቀና ብሎ ለመቆም ሲቸገር ተመልክቻለሁ። እሱ ግን አሁንም ቤተሰቤንና ጠበቃየን እንዳይ ካልተደረገ በርሃብ አድማየ እቀጥላለሁ ይላል። “ቀጣይ ቀጠሮ ሬሳየ ሊመጣ ይችላል” ሲል ተድምጦዋል።
ልብ ያለው ልብ ይበል!

No comments:

Post a Comment