Saturday, June 18, 2016

ከሰላምና የአንድነት የቤተ ክርስቲያን ስብስብ የተላለፈ መልዕክት

“የምእመናን ብሶት የማያዳምጥ አስተዳደርና የተዘጋ በር አንድ ነው።” የሐዋርያት ሥራ ምእራፍ 6: ቁጥር 1-6፤ ቲቶ ምእራፍ 1: ቁጥር 7-9
በመላው ዓለም በስደት ለምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ምዕመናን እና ምዕመናት በሙሉ፣ እንዲሁም የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሥራ አመራር አባላት በያላችሁበት፤
ይህ ጽሑፍ የቀረበላችሁ ቤተ ክርስቲያናችንን ከወያኔ ጥፋት እንድትታደጓትና እንድታድኗት በማሰብ የቀረበ የይግባኝ ጩኸት ነው።የወያኔው መንግሥት ገና ከጅምሩ ጠላት አድርጎ ለማጥፋት የተነሣሳው የኦርቶዶክስ እምነትና አማራን መሆኑን በ1968 ዓ. ም. ባወጣው ማንፌስቶው ያወጣውን የአደባባይ ምሥጢር ሌላው ባለሥልጣናቸው ስብሐት ነጋ በ2006 ዓ. ም. የሁለቱ ሲኖዶስ የእርቅ ድርድር ሲያፈርስ “ይህንን ሃሳብ ያነሣው ሰው መሰቀል አለበት ከማለትም ኦርቶዶክስና አማራን ድባቅ መትተናል” በማለት ለአሜሪካን ድምፅ ራዲዮ የሰጠውን የመጠይቅ ቃለ ምልልስ በድህረ ገጾች መመልከት ይችላሉ። በዚህም ዓላማው መሠረት በነሐሴ ወር 1983 ዓ. ም. ፓትርያርክ መርቆርዮስን ሳይታመሙ ታመዋል በማለት ከመንበራቸው አባሮ ከጎጡ አባ ጳውሎስን ፓትርያርክ አድርጎ ሹሟል። በዚህም መሠረት ገፍቶ ከሀገር ካስወጣቸው በኋላ በስደት ሕጋዊውን ሲኖዶስ መሥርተው ለስደተኛው የተስፋ አባት ሆነው ይገኛሉ።
፩፦ ሕጋዊው ሲኖዶስ ሲቋቋም ወያኔ በለመደው ከፋፍለህ ግዛ በስደት ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አማንያን
  1. የስደተኛው ሲኖዶስ አብያተ ክርስቲያን አማኞች
  2. የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ አብያተ ክርስቲያን አማኞች
  3. ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት አማኖች። በዚህ መልክ እነሆ ለአለፉት 24 ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተንሰራፍቶ ይኖራል።
፪፦ የሴረኛው (የጎጠኛው) ቡድን በመባል የሚታወቀው የጳጳሳት የካህናትና የቦርድ ሊቃነመናብርት ቅንብር ፓትርያርኩንና የሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ አቡነ መልከጼዴቅን ለማጣላትና ሲኖዶሱን ለማፍረስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነበር። የዚህ ቡድን ቀንደኛ አባላት፦
  1. አቡነ ኤልያስ
  2. አቡነ ሚካኤል
  3. አቡነ ዲሜጥሮስ
  4. አቡነ ሉቃስ
  5. አቡነ ሳዊሮስ
  6. ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳ
  7. አባ ጽጌድንግል ደገፋው
  8. አባ ገብረስላሴ (አባ ታደስ)
  9. ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊ
  10. አቶ ፍሬሰው ገድለ
  11. ዶ/ር አምባቸው ወረታ
  12. ዶ/ር ነጋ ዓለማየሁ
  13. ዶ/ር ሰሎሞን አበበ
  14. አቶ ምርጫው ስንሻው
ይህ ስብስብ ለሲኖዶሱ ሰላም ማጣት ዋና ተጠያቂ ሲሆን በዋናነት የቦርድ አመራር ነን የሚሉት አንዴ የሲኖዶስ ድጋፍ ሰጪ፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የማህበር ማደራጃ መምሪያ በሚል የሕግ መሰረት የሌለው ቡድን ሲሆን ፈቃዱን አገኘን የሚሉት ከዋና ጸኃፊውና ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ነው። በተጨማሪ ለሲኖዶሱ ቋሚ ኮሚቴ ከአምስቱ ሶስቱ ከዚህ ቡድን ውስጥ ናቸው።ወያኔ የላከላቸውንም የደህንነት አባልና ጋዜጠኛ በላስቬጋስ ከተማ አስቀምጠው የወንጌል መምህራኑን በዩቲዩብ ሲያሰድቡ ከርመዋል።
ዶ/ር ነጋ ዓለማየሁ ተሽሎክልኮ በመመረጥ ሊቀመንበር የሆነው ከአቡነ መልከጼዴቅ ጋር የጋብቻ ዝምድና ስላለው ወደ ሥልጣን ላይ ለመውጣት አልተቸገረም፤ ከወጣም በኋላ የሚከተሉትን ጥፋቶች ፈጽሟል፦
  1. ቤተ ክርስቲያኑን ያገለገሉትን የወንጌል አገልጋይ ካህናት በማሳሰር አባሯል
  2. ደክመው የሠሩት ሊቀ ጳጳስ ከሚኖሩበትና ከሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን አባሮ ከፍርድ ቤት ውሎ አውሏቸዋል
  3. ቅዱስ ፓትርያርኩ ዘጠኝ ጳጳሳት የሾሙበትን ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ ከማድረጉም በላይ ስማቸው በቅዳሴ እንዳይጠራ አግዷል
  4. ሃያ አምስተኛው የሲመት በዓላቸው በ2007 ዓ. ም. ሲከበር እሱም ሆነ የቦርድ አባላቱ አልተገኙም።
  5. የቤተ ክርስቲያኑን ሕገ ደንብ በመለወጥ ቤተ ክርስቲያኑን ያለ ጳጳስና ያለ ፓትርያርክ የግል ከማድረጉም በላይ የሥልጣን ዘመኑንም ከሶስት ወድ አማስት ዓመት ከፍ አድርጓል።
  6. በዓል ሲያከብርም ህብረተሰቡ እንዳይጠይቀው አቡነ መልከጼዴቅን ወይም በተራ ቁጥር ፪ ላይ የተቀሱትን ጳጳሳት በበአሉ ተገኝተው እንዲባርኩ ያደርጋል።
  7. ፍሬሰው ገድሉ የተባለውን ሰባኪ በ2006 ዓ. ም. የሲኖዶስ ስብሰባ ልኮ ቃለ ጉባዔ ጸሐፊ በማስደረግ ቃለ ጉባዔውን አሰርቆ በማስወሰድ በሐምሌ ወር 2005 ዓ. ም. ከአቡነ ሳሙኤል ጋር ተጀምሮ የነበረውን እርቅ አፍርሶ በፍርድ ቤት ሞግቷቸዋል።
ፍሬሰው ገድሉ
  1. ለዶር ነጋ ተባባሪ በመሆን በ2006 ዓ. ም. የሲኖዶስ ቃለ ጉባዔ ሰርቆ ወስዶ በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ ለህብረተሰቡ የተሳሳተ መረጃ ሰጥቷል። ይህም በድምጽ የተቀረጸ መረጃ በድህረ ገጽች ላይ ወጥቷል።
  2. በህዳር 2007 ዓ. ም. ትዳሩን አፍርሶ እስከ ዛሬ ይቀድሳል ይባርካል።
  3. በዲሲ ገብርኤል ያሉ ምዕመናን ሰምተው ቅዳሴ አብረው የሚቀድሱትን አቡነ ኤልያስን ትዳር ያፈረሰ ካህን እንዲቀድስ ማድረግዎ ተገቢ አይደለም ቢሏቸው ሀሰት ነው በማለት ሰድበው ያባረሯቸው ቢሆንም አባ ሰላማ የተባለው ድረ ገጽ የካቲት 1 ቀን 2008 ዓ ም. በጽሑፍ ለቆታል።
  4. አቡነ ኤልያስ በታኅሣስ ወር ይህንኑ ካህን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ኮሚቴ አስመራጭ እና ፀሐፊ እንዲሆን ያደረጉት ከግለሰቡ ጋር ባላቸው ቅርበትና ቁርኝት መሆኑን አመልካች ስለሆነ ወደ ምርጫ ከመኬዱ በፊት ይህ ኮሚቴ በውል ሊመረመር ይገባል።በሕዝብ ሀብትና ጉልበት ሊቀለድ አይገባም። የፍሬሰው ገድሉም ከኮሚቴው ሊወገድ ይገባል ተብሎ የተጠየቀ ቢሆንም ሰሚ አልተገኘም።
  5. በሚያዝይ ወር 2008 ዓ/ም በካህናት ጉባኤ ላይ አቡነ ዲሜጥሮስ የስብከተ ወንጌል የበላይ ጠባቂ ይህንን ግለሰብ የስብከተ ወንጌል ኃላፊና ጸኃፊ አድርገውታል።
  6. በግንቦት 2008 የሲኖዶስ ስብሰባም አንደኛው ቃለ ጉባኤ ጸኃፊ በመሆን ተመርጧል። ስለዚህ የሲኖዶሱ ሚስጢር ለወያኔ በቀላሉ እንደሚደርሰው አንጠራጠርም።
፫፦ በሰሜን ካሮላይና ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ሰሎሞን የወያኔ አንድ ለአምስት አደራጅ መሆኑን በድረ ገጽ ማስረጃው የተገለጠው፡-
  1. ካህኑን ከሥራ ከማገዱም በላይ እንደክርስቲያን የቤተክርስቲያኑ አባል ሆነው እንዳይገለገሉ ማድረጉን ምዕመናን ሲቃወሙ ካህኑንም ምዕማናኑንም አባሮ እነሱም ለሁለት ዓመታት በበረዶ ላይ ቆመው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ጉዳያቸውን ወደፍትሕ ወስደው ዳኝነት እየጠበቁ ይገኛሉ
  2. ሊቀጳጳሱ ጉዳዩን ለማጣራትና ለመሸምገል ቢሄዱ ከቤተ ክርስቲያን አላስገባም በማለቱ እበረዶ ላይ ለግማሽ ቀን ውለው ተመልሰዋል።
  3. በዓል ሲያከብርም ተባባሪዎቹን የሴረኛውን ቡድን ሊቀ ጳጳሳት እየጋበዘ በዓል ባከበረ ቁጥር የሚነሣውን እርቀ ሰላም በዓሉ እስኪከበር አደርጋለሁ ይልና ክሳቸውን ካላነሱ እያለ የላከውን የወያኔ ተልዕኮ እያጠናከረ ከዚህ ደርሷል።
፬፦ በሲያትል ዋሽንግተን ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን
  1. ሊቀ ጳጳሱ አባ ሉቃስ
  2. ካህኑ አባ ገብረ ሥላሴ (አባ ታደሰ) ምዕመናኑ መከራውን አይቶ የሠራውን ቤተ ክርስቲያን ከምዕመናኑ ፈቃድ ውጪ ምዕመናኑን የተስማማ በማስመሰል አቡነ መልከጼዴቅን ፈቃድ ጠይቀው ገዳም ሆኗል በማለት ያላግባብ ከመደረጉም በላይ የቤተ ክርስቲያኑን አባላት በማባረር አቤቱታ ቢያቀርቡም ሲኖዶሱ ውሳኔ ሳይሰጣቸው አራት ዓመታት አልፈዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን
ሀ.   የወንጌል መምሕራኑን በማባረር የወንጌል ትምህርት እንዳይሰጥ አድርገዋል።
ለ.    የሰሞነኛ መነኮሳት ብቻ መሰብሰቢያ አድርገውት ባለትዳር ቀሳውስትን ገዳም ስለሆነ አንቀበልም በማለት የግል መገልገያቸው አድርገውታል።
ሐ.   የወያኔው ሲኖዶስ ከ2007 -2016 ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ሲከፍቱ እነዚህ አባቶች በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ሌላ እንዳይከፈት ከመከልከላቸው ቋሚ ሲኖድስ ፈቃድ የተከፈተውን የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህኑም ምዕመናኑንም አውግዣለሁ በማለት ሌላው የወያኔ ተልዕኮ ፈጻሚ ሆነዋል።
መ.    በጥቅምት 2008 ዓ. ም. የሲኖዶስ ስብሰባ ከካህናት ጋር ዕርቅ ቢደረግም የምዕመናኡንን ችግር ይፈታሉ ተብለው የተላኩት ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ምዕመናኑን እንደሰው ባለመቁጠር የተነሣውን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ አውግዘው ተመልሰዋል።
ሠ.   በመስከረም ወር 2008 ዓ. ም. የመድኃኔ ዓለምን በዓል ለማክበር በሲያትል የተገኙት ፓትርያርክ መርቆሪዎስ ወደ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲሄዱና ምዕመናኑ እንዲባርኩ ተጠይቆ ለመሄድ ሲዘጋጁ አባ ገብረ ሥላሴ (አባ ታደሰ) እምቢ በማለት ፓትርያርኩ ተከልክለው ተመልሰዋል።
፭፦ በዳላስ ሚካኤል ከተማ የሚገኘው ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊ
  1. በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ባደረገው ሠርግ ላይ ከስደተኛው ሲኖዶስ አምስት ጳጳሳት ተገኝተው እያለ በውግዘት የተለዩትን የአዲስ አበባ ሲኖዶስ ሊቀ ጳጳስ በድንግል ማርያም ተገኝተው የሰርጉን በዓል እንዲፈጽሙለት ቢጠይቅም የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር በመከልከሉ ፀሎቱን ባይመሩም ከጳጳሳቱ ጋር ሆነው ቅዳሴውን ተጋርተዋል።
  2. በሎስ አንጀለስ ቅድስት ማርያም በሳምንቱ እኒህኑ ጳጳስ ይዞ ሄዶ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ጽጌ ድንግል በቅዳሴው ስማቸውን አንስተው ከመቀደሳቸው ባሻገር ከቅዳሴ በኋላም በአውደ ምህረት በማወደስ ሲያስተዋውቁ ውለዋል።
  3. በአቡነ ኤልያስ አጃቢነት ከካሊፎርኒያ ወደ ዳላስ በመውሰድም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጸም የዳላስ ሚካኤል የአስተዳደር ቦርድ አግዷል። የወያኔን ተልእኮ ይዘው የመጡት አባት ከዳላስ ወደ ሚኒሶታ በመሄድ የገለልተኛው መድኃኔዓለምን ቤተክርስቲያን ለማስገበር ምእመናኑን ለመደለል ቢሞክሩም እምቢ ሲላቸው ሕዝቡን ከሁለት ከፍለው ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተው መድኃኔ ዓለም የቀረውን ያላግባብ አውግዘው ሲሄዱ ምዕመናኑም ውግዘቱ አላግባብ ስለሆነ ወፈ-ግዝት ብለው አልፈውታል።
  4. ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊ የቴክሳስ ሊቀጳጳስ አቡነ ዮሐንስን ለዳላስ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን እውቅና እንዳይሰጡ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ እውቅና እንዲያገኙ እንቅፋት በመሆናንና ያለ በቂ ማስረጃ ሲኖዶስ ቀርቦ በማስከልከሉ ሊቀ ጳጳሱ ሲኖዶሱ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ካህናቱን ጠይቀው አጣርተው እውቅና ቢሰጡም ከጳጳሱ በላይ እራሱን አስቀምጦ መታዘዝን ያላወቀ ካህን መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በጥቅምቱ 2008 ዓ. ም. የሲኖዶስ ጉባኤም በሙሉ ድምጽ ተፈቅዶም እንኳን ቋሚ ሲኖዶስ እስካሁን ደብዳቤ ለዳላስ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን እንዳለከ ተረጋግጧል። ይህ እንግዲህ የሴረኛው ቡድን ውጤት ነው።
፮፦ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ አባ ጽጌ ድንግልና ዋና ጸሐፊው ቀሲስ አንዱዓለም በተሰጣቸው ሥልጣን በመጠቀም የሴረኛውን ቡድን አጠናክረው አሰባስበዋል። ለዚህም ነው ዋና ጸሐፊው ለእነዚህ ባለሥልጣናት የስልጣን ዘመን እንዲራዘምላቸው በመጠየቃቸው ለ3 ዓመት የጥፋት ዘመን የተራዘመላቸው።
  • ቅዱስ ፓትርያርኩ በግንቦት 2007 ዓ. ም. እንደራሴያቸውን ሲሾሙ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጁ አዘጋጅነት በሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ፊርማ ያላግባብ ታግደዋል። በእርሳቸው አዘጋጅነት በቀረበው የሲኖዶሱ ደንብ ውስጥ አንቀጽ 10 ቁጥር 10 የተጠቀሰው “አንድ ፓትርያርክ በእርጅና ወይም በጤና ችግር ምክንያት ሐዋርያዊ ተልዕኮውን በሚገባ ማከናውን ባይችል መንበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባዔ በሚሰይመው እንደራሴ የኃላፊነት ሥራው ይከናወናል” የሚል በደብዳቤው ላይ ጠቅሰዋል። ከ24 ዓመት በፊት ወያኔ ከመንበራቸው ሲያወርዳቸው ታመዋል ብሎ ነበር። ታዲያስ እነዚህ የወያነኔን ተልዕኮ የቀጠሉ አስመስሏቸዋል እንጂ ፓትርያርኩ ሹመቱን ለመስጠት ብቁ መሆናቸውን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን።
ይህ የምዕመናኑ ስብሰብ ከ2004-2008 ዓ. ም. ባለ ጊዜ ውስጥ እንደ ዓላማ ባስቀመጥነው መርሆ መሠረት፣
  1. የቅዱስ ፓትርያርኩን ክብርና ማዕረግ ለማስጠበቅ፣
  2. የሲኖዶሱ አንድነት መከበር እንዲኖርና አባቶች እርስ በርሳቸው፤ ካህኑም ለአባቶች፣ ምዕመናኑም መጀመሪያ ለካህኑ ከዚያም ለጳጳሳቱ አክብሮት ሲሰጥ ነው ቤተ ክርስቲያን ጸንታ የምትኖረው፣
  3. በየቤተክርስቲያኑ የተፈጠረውን ችግርና መፍትሔ በማጥናት በጥቅምት 2007 ዓ. ም. ለሲኖዶሱ ጥናት ቢያቀርብም የተመለከተው ግን የለም።
  4. የሲኖዶሱን ረቂቅ ደንብ እንደ ምዕመናንነታችን በስደት ለሚኖሩትና ለሚወለዱት ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ አስተዳደራዊ መዋቅር በማጥናት ለጥቅምቱ 2007 ዓ. ም. የሲኖዶስ ስብሰባ ብናቀርብ የወያኔ ተልዕኮ ያነገቡት የቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ እንቢ በማለት ጥናቱን ከቅርጫት ውስጥ ጥለውታል።
  5. እነሱ ያጠኑት ሕገ ደንብ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ፈላጭ ቆራጭነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በድብቅ በሎስ አንጀለስ በተደረገው ስብሰባ በረቂቅ ደንቡ ላይ ያልነበረ የታከለውን አንቀጽ 10 ቁጥር 10ን ተጠቅመው በዋና ጸሐፊው ፊርማ በተዘጋጀ ደብዳቤ የቅዱስነታቸውን የእንደራሴ ሹመት አግደዋል። አንድን መንፈሳዊ አባት ቀርቶ በዓለማዊ አሰራርም ቢሆን አንድ የሀገር መሪ ወይም የድርጀት ሥራ አስኪያጅ በሰጠው ውስኔ የበታቹ አይታገድም። ለዚህ ነው እነዚህን ካህናት የወያኔ አስፈጻሚ ናቸው ብለን እንድንናገር ያስገደደን።
  6. ይህንኑ በመገንዘብ ይህ ስብስብ መጀመሪያ በህዳር ወር በኋላም በየካቲት ወር 2007 ዓ. ም. ለቋሚ ሲኖዶስ፤ ከዛም ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ. ም. ደግሞ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እነዚህ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ባለሥልጣናት እንዲቀየሩ ጠይቆ ነበር። እንደውም ይባስ ተብሎ ለ3 ዓመት የጥፋት ጊዜ ተጨመረላቸው።
  7. በጥር ወር 2008 ዓ. ም. በሎስ አንጀለስ የጥምቀት በዓል የቅድስት ማርያም ቦርድ ሊቀመንበር በአባቶች መሀከል ፍቅርና ሰላም እንደሌለ ይሄ አርአያነቱ ከነሱ መምጣት እንዳለበት ጠቅሰው በመድረክ ላይ መሆን አለበት ብለው ሲገልጹ አቡነ ሚካኤልና አባ ጽጌድንግል በመሀከላቸው ምንም ችግር እንደሌለ ሲገልጹ በምዕመናኑ የተወሰደባቸው ትዝብት ክብራቸውን ዝቅ እንዳደረጉት የተገነዘቡት አይመስልም። ለምን እንደሚዋሹም አይገባንም። ፍቅርና ሰላም ሳይኖር የሚቀርበው ጸሎት ለቅስፈት እንጂ ለድኅነት እንደማይሆን ማንም ነፍስ ያወቀ ፍጡር ይረዳዋል፣ እባካችሁ ቅዱስ ሥጋ-ወደሙን ለመፈተት ስትዘጋጁ ለምዕመናኑ በምትወረውሩለት ቃለ እግዚአብሔር መጀመሪያ ቁጣው የሚያርፈው በእናንተ ነውና ሰላምና ፍቅርን ፍጠሩ እንላለን።
  8. በጥቅምቱ 2008 ዓ. ም. የሲኖዶስ ስብሰባ ተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ለመሾም በአቡነ ኤልያስ የሚመራ አስመራጭ ኮሚቴ ከተመረጠ እና ከስብሰባውም በኋላ አቡነ ኤልያስ በሲኖዶሱ ስብሰባ ከደንቡ መጽደቅ በፊት ምርጫው ሊደረግ አይገባም ሲሉ ስለተሰማ ይህ ስብስም በስልክ ሲያነጋግራቸው ደብዳቤ ጻፉልኝ እንዲዘገይ አደርጋለሁ በማለታቸው ጥር13 .ቀን 2008 ዓ. ም. በተጻፈ ደብዳቤ ምርጫ ከመስጠታቸው በፊት ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበን ምርጫው እንዲዘገይ ጠይቀን ነበር። ደብዳቤ ከተላከላቸው በኋላ ስልካቸውን ዘግተው መልስ አልሰጡንም።
መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ/ም “በመላው አለም በስደት ለምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምእመናን በሙሉ” በሚል ርእስ ያወጣነውን መግለጫ በድህረገጽ ላይ ከተጻፈ በኋላ ሲኖዶሱ በአግባቡ መልስ መስጠት ሲገባው በሕዝብ ግንኙነቱ አማካይነት ከድረገጾቹ እንዲነሱ አድርገዋል። በድጋሚ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ/ም “በህግ አምላክ” የሚለውን ሁለተኛ መግለጫ በድረገጾቹ እንዳይወጣ ከፍተኛ ዘመቻ ተደርጓል። ሆኖም ጽሁፉን ያወጡ ድረገጾችን እያመሰገንን የሕዝብ አገልጋይነታቸውን የዘነጉት ድረገጾች ራሳቸውን መልሰው እንዲመለከቱ እንጠይቃለን። እንዲህ አይነቱ ሸፍጥ ከመንፈሳዊ አባቶች የሚጠበቅ አይደለም። ከመግለጫው በስተግርጌ የተሰጠውን የሕዝብ አስተያየት ደግመው በመመልከት እንዲማሩበት እንጠይቃለን።
ከዚህ ሁሉ ትግል በኋላ ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ/ም ( በሜይ 30 ቀን 2016 ዓ/ም)  በወጣው መግለጫ የሚከተለው ታትቷል። “በመቀጠልም የኢጲስ ቆጶሳትን ሹመት በተመለከተ ስምንት ቆሞሳት ተመርጠው የተዘጋጁ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ሰኔ 19/2016 በኦክላንድ መካነ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በዓለ ሲመት እንዲሆን ተወስኗል። የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በዶክተር አምባቸውና አቶ ዘውገ በተባሉ ሰዎች በሚመሩ ሁለት የተለያዩ ቡድኖች ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ግን እነዚህን ሁለት ቡድኖች ሐሳባቸውን ከደብዳቤያቸው ይዘት መርምሮ የማይመለከታቸው መሆኑን በመገንዘብ በሹመቱ ቀጥሎበታል።”
1.ለአገልግሎታቸው ደሞዝ የሚከፍል
2. በአመት ሁለት ጊዜ ለሲኖዶስ ስብሰባ የመጓጓዣ የአውሮፕልን ክፍያ፤ የሆቴልና የድግስ፤ ከመቶ ሺህ ብር በላይ እያወጣ የሚያስተናግዳቸውን ምእመናን አያገባውም ብሎ በድህረ ገጽ ለሕዝብ መበተን “እማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” የሚለውን የአገራችንን ብሂል እንዲያጠኑትና እራሳቸውን እንዲያዩ እንጠይቃለን። በተጨማሪ በቀዳሚው መግለጫችን እንደገለጽነው በተለያየ ምክንያት ሀገረ ስብከታቸውን ያጡ ጳጳሳት ሀገረ ስብከት ሳይሰጣቸው አዲሶቹን በመሾም ምእመናኑን አላግባብ የወጪ ጫና ማሸከም አግባብ እንዳልሆነ እንገልጻለን።
ምዕመናን ሆይ!
ሁላችሁም በያላችሁበት ከአስተዳደር ጋር በመመካከር የተሻለ ሃሳብ ሊቀርብ ይችላል ብለን ስለምናስብ መልዕክታችንን ስናቀርብ አባቶችም እኛ ለመጭው ትውልድ ሥርዓት ትተውለት እንዲሄዱ እንጂ ለእኛ የጎደለብን ኖሮ አለመሆኑን በቅንነት እንዲመለከቱት ስንጠይቅ በጥፋት ጎዳና ላይ ላላችሁት ግን እንድትታረሙ ለማስጠንቀቅም መሆኑን እንድትረዱልን በአክብሮት እንገልጻለን።
ኃያሉ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፣ ለሀገራችንም ሰላሙን ይስጥልን!
የሰላምና የአንድነት የቤተ ክርስቲያን ስብስብ

No comments:

Post a Comment